top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር (በሳምሶን ሃይለጊዮረጊስ)


በሙያዬ የህክምናና የስነ-መለኮት ዶክተር ነኝ፡፡ ስለእነዚህ ሶስት የጊዜው ቃላት አፈጻጸም የምረዳውን እንደ ባለአደራ ላካፍል ወደድሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለሃገራችን የፈጣሪ የምህረት ምልክት ናቸው፤ የአመራር መርሃቸው የሆኑት እነዚህ ሶስት እሴቶች የፈጣሪም እሴቶች ናቸው፡፡ ዶ/ር ዐብይ በሰኔ 16, 2010ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የኔልሰን ማንዴላ ምስል የታተመበትን ከነቴራ ለብሰው ስለ ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የደስታ ሲቃና ድንጋጤን በውስጤ ፈጥሯል፡፡ ደስታው እነዚህ ሶስት እሴቶች ሃገራችን አሁን ላለችበት ቀውስ ፍቱን መድሃኒቶች በመሆናቸው ሲሆን ድንጋጤው አፈጻጸሙ የሚጠይቀውን ዋጋና ቁርጠኝነት ሳስብ ቃል-አባይ እንዳያስብላቸው ሰጋሁ፡፡

ይቅርታ ጥፋቱን ያመነን አካል ለጥፋቱ ተመጣጣኝ ዋጋ ሳናስከፍል ነጻ የምናወጣበት ብርቅዬ ስርዓት ነው፡፡ ይቅርታ የፈሪ ሳይሆን የጠቢብ እርምጃ ነው፡፡ የይቅርታም ተቃራኒ በዋነኝነት በቀል ሳይሆን ፍትህ/ፍርድ ነው፡፡ በቀል ከፍትህ ስርዓት ውጭ በበደለኛ ላይ የሚቃጣ እርምጃ ነው፡፡ በቀል የአምባገነን መሪዎች፤ ፍትህ የመልካም አስተዳደር፤ ይቅርታና ፍትህን አቻችሎ ማስኬድ ደግሞ የእጅግ መልካም አስተዳደር መለያዎች ናቸው፡፡ ፈጣሪ እርስ በርሳቸው የሚገጫጩ የሚመስሉ (ነገር ግን የሚደጋገፉ) ሁለት ባህርያት አሉት--ይቅርታና ፍርድ/ፍትህ፡፡ ፈጣሪ ጥፋተኛ የሆነን አካል አንዳንዴ በነጻ ይለቃል (ይቅር ይላል)፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተመጣጣኝ ዋጋ ያስከፍለዋል (በጽድቅ/በትክክል ይፈርድበታል)፡፡ ወሳኙ የበደለኛው ምላሽና የፈጣሪ ነጻ ፍቃድ ናቸው፡፡

የማስተካከል እርምጃው ሊለያይ ቢችልም ከይቅርታ ጣራ በላይ የሚባል በደል ግን አይኖርም፡፡ ይቅርታ ነገር እንዳይባባስ ተፈርቶ በድፍኑ/በጥቅሉ የሚተገበር ሳይሆን የአውጫጪኝ መልክ አለው፤ አለበለዚያ የጥላቻው/ጥፋቱ የማገርሸት እድል ከፍተኛ ሲሆን አስተማሪነቱም አናሳ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጅማሬው ጥፋተኛውንና አውራ ጥፋቱን እንዲሁም የጥፋቱን መንስኤዎች በማወቅ ሊሆን ይገባል፡፡ የሂደቱ ጅምር (በደልን መግለጥ) ከበደለኛው፣ ከተበደለው ወይንም ከፍትህ አካላት ሊነሳ ይችላል፡፡ ይቅርታው ሙሉ እንዲሆን ግን ህሊናው ወቅሶትም ሆነ በማስረጃ ተወቅሶ ከበደለው አካል አራት እርምጃዎች ይጠበቃሉ--1) ጥፋትን ማመን 2) መጸጸት/ማዘን 3) የበደሉትን አካል ምህረት መጠየቅ 4) አቅም በፈቀደ የማስተካከል እርምጃ መውሰድ፡፡

ፍቅር ከሁኔታ/ማንነት ጋር ባልተያያዘ አንድን አካል መቀበልና የሚጠቅምም እንደሆነ እውቅና መስጠት ነው፡፡ ፍቅር የሌሎች ጥገኛ መሆንን ተረድቶ ያነእነርሱ አይሆንልኝም በሚል “ልዩ አቅማቸውን” ለጋራ ጥቅም የማዋል ክህሎት ነው፡፡ ፍቅር በይቅርታ ያለቀን የቀደመን በደል ረስቶ ለተሻለ ፍሬ ሁለተኛ እድል መስጠት ነው፡፡ ፍቅር ክፉን በመልካም ማሸነፍ ነው፡፡ “በፍቅር መጣብኝ በማልወደው መንገድ!” የሚባል አባባል አለ፡፡ ትርጓሜውም በሃይል የመጣብንን ወገን አንዳንዴ እናሸንፈው ይሆናል፤ በፍቅር የሚመጣብን ግን ሁልጊዜ ያሸንፈናል፡፡ የደርግና ኢህአዲግ ታላላቅ ሰራዊቶች ያላንበረከከውን የኤርትራን መንግስት የዶ/ር ዐብይ የፍቅር እርምጃ ጥላቻን ገፎ ገንዘብ አድርጎታል፡፡

መደመር ወይም አንድነት አንድ-መሆንነት (uniformity) ሳያሆን አላስፈላጊ ልዩነቶችን በማስወገድና የልዩ ልዩነትን ውበት በመቀበል ለጋራ አላማ እንደ አንድ ሰው መውጣት ነው፡፡ ልዩ ልዩነታችንን (diversity) ወደአንድነት (unity) ካልመራነው ብቸኛው ተለዋጭ መንገድ መለያየት (division) ይሆናል፡፡ በመደመር የምንሰራው በተናጥል ከምንሰራው ድምር እጅጉን ይልቃል--ይህም እምቅ አቅም (synergy) ተብሎ ይጠራል፡፡ የታላላቅ መንግስታትና ኩባንያዎች የስኬት ሚስጥር መደመራቸው ነው፡፡ ለዚህም አሜሪካ፣ ታላቋ ብሪታንና ጀርመን መልካም ተምሳሌቶቻችን ናቸው፡፡ በብሔሮች/ክልሎች፣ ተፎካካሪ/አሸባሪ ፓርቲዎች እንዲሁም በጎረቤት ሃገሮች መሃከል አብሮነትን/መደመርን ስንሻ አራት የደረጃ እርከኖችን እናስብ፤

1. የፉክክር/መናናቅ (Competition),

2. የመቻቻል (Co-existence),

3. የመደጋገፍ/የመተባበር (Cooperation),

4. የመደመር/ጥምረት (Communion)፡፡

አንድ ጣልያናዊ ወዳጄ በአንድ ወቅት ስለሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ስንጫወት እንዲህ አወጋኝ፤ እኛም በአንድ ወቅት እንደእናንተ በዘራችን እንጠራ፣ እንመካና እንፎካከር ነበር፡፡ በሂደትም የመለያየትን አደጋና የአንድነትን ሃይል በመረዳት የዘር ማንነታችንን ሳንክድ ጣልያናዊ ማንነታችንን ማጉላት ቀጠልን፡፡ የጥምረት/መደመር ብድራት በብዙ ሲገባን ጣልያናዊ ነኝ ማለትም ጠባብነት ሆነብንና አውሮፓዊ ነኝ ማለት ጀምረናል፡፡ አይመጥነንምና ከብሔር ማንነት ያለፈ የድምር መጠሪያን (ለጊዜው ኢትዮጵያዊ በቀጣይም አፍሪካዊ) ልናጎላ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ሊለያዩ የማይችሉና የተጣበቁ መንትዮች ናቸው፡፡ ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ከኤርትራ መንግስት ጋር ለሚኖረን ግንኙነት ሶስት ምሰሶዎች ናቸው፡፡ ከባድመ ባለፈ በሁለቱም ወገን በደልና ግፍ ተፈጽሟል--ከመፈራራትም የተነሳ በብዙ ወጪ የጦር ሃይል ግንባታ ተከናውኗል፡፡ ይህም ታላቅ ማህበራዊ ቀውስን አስከትሏል፡፡ በቅርቡ በሁለቱም መንግስታት የታየው ተግባራዊ የፍቅር እርምጃ ድንቅ ቢሆንም በጋራ በሚሰየም አካል አውራ ጥፋቶችንና መንስኤዎቻቸውን በመመርመር በይቅርታና ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ የበደል እስራት ሊቆረጥና ዶሴው ሊዘጋ ይገባል፡፡ ከዚህ የመሰረት ስራ (ይቅርታ) በኋላ ፍቅር መድረኩን ተረክቦ በመደመር እርከን በእውቀትና መቻቻል አለምን ልናስደምም ይገባል፡፡

የአፓርታይድ መንግስት በስልጣን ዘመኑ በደቡብ አፍሪካ ህዝብ ያልሰራው ግፍ የለም፡፡ ታላቁ የተሃድሶ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ወደስልጣን ሲመጡ የአፓርታይድ አመራሮችን ለፍርድ የማቅረብ አማራጭ ቢኖራቸውም በይቅርታ፣ ፍቅርና ከአፓርታይድ አመራሮችም በመደመር ሃገሪቷን ከማረጋጋት ባለፈ የአህጉሯ ሃያል አድርገዋታል፡፡ በሃገራችን የቀድሞ ፖለቲካ መሪዎች ብዙ በደል ቢፈጸምም የአፓርታይድ መንግስትን ያህል አልተፈጸመም፤ ምንም ያህል ይቅር ብንላቸው የኔልሰን ማንዴላን ያህል ይቅር አንላቸውም፡፡ በቅርቡ በአንድ የአውሮፓ ሃገር የተዋወቅሁት ኢትዮጵያዊ የታሪክ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዐብይ በቀደመው ስርዓት በደል ያደረሱ ባለስልጣናትን ስለሃገር ሰላምና አንድነት ሲሉ ፈጽመው ይቅር ሊሏቸው ይገባል ሲል የብዙ ሃገሮችን ተሞክሮ በማንሳት ሞያዊ ትንታኔን ሰጠኝ፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ምህረትን የአስተዳደሩ አካል ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ አስደስቶኛል፡፡ “እድሜ ለይቅርታ!” በሚል እሳቤ ወንጀል እንዳይባባስና አድልዎን ለመከላከል የይቅርታ በሮች መቼ፣ ለማንና እንዴት ሊከፈቱ እንደሚገባ ግልጽ መመሪያን ይሻል፡፡ በደል ያደረሱ የኢህአዲግ ባለስልጣናትን በይቅርታ፣ ፍቅርና የመደመር መንፈስ የተሃድሶው አካል ለማድረግ የሚከተሉትን እናስብ፡-

1. ትናንት በነፍሳቸው ተወራርደው በብዙ ዋጋ መክፈል ለጋራ ጥቅም የጋራ ጠላትን (ደርግን) መጣላቸው

2. የቀደመው የአመራር ስርዓት በራሱ የአሰራር ክፍተቶች እንዳሉበት መገንዘብ

3. በስልጣናቸው ዘመን ጥፋታቸው እየታወቀ ቀጣይነት ያለው ጠንካራና ግልጽ ተቃውሞ (ከቤተ እምነቶችም ጭምር) አለማሰማታችን

4. የተሰራው ወንጀል መጠነሰፊ፣ ውስብስብና ለፍርድ ሂደትም አታካች ስለሚሆን

5. ለጀመርነው የተሃድሶ ጉዞ ስለሚያስፈልጉን (ሊቀነሱ ስለማይገባ) 6) ጥፋቱ በቆይታ ብዙ ስርና ቅርንጫፍ ስላወጣ ወደዘር፣ ክልልና ፓርቲ ግጭት ሊያመራ ስለሚችል፡፡

ወንጀለኞች (የቀድሞ የአመራር አካላትም ቢሆኑ) “ለጥፋታቸው መረጃ (information) ቢኖረንም በቂ ማስረጃ (evidence) እስኪኖረን ብቻ ነው በነጻነት የሚመላለሱት” በሚል አቋም የምንጸና ከሆነ ይህ ይቅርታ ሳይሆን ተለዋጭ/አማራጭ የፍትህ አካሄድ ነው፡፡ ይህ በራሱ ክፉ ባይሆንም ከኔልሰን ማንዴላ ፍጹም ይቅርታ አይተካከልም፡፡ ለብዙ በደላቸው ይቅርታ/ምህረት ሳይሆን መጠነሰፊ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የሚያስቡ የቀድሞ አመራር አካላትም የአልሞት-ባይ ተጋዳይ እርምጃዎችን ቢወስዱ ብዙ ሊገርመን አይገባም፡፡ በቀል ጣራ የለውምና ይህ ደግሞ ወደትውልድ የሚሻገር ጥላቻን ያስከትላል፡፡

ሰዎች በፈጣሪ ፊት በደላቸውን ዘርዝረው በሃዘንና ጸጸት የሚቀርቡበት ብቸኛ ምክንያት የይቅርታ/ምህረት ተስፋ ስላለ ነው፡፡ ጥፋታቸውን አምነው የማስተካከያ እርምጃ ለሚወስዱ አካላት የይቅርታ/ምህረት ተስፋ በጊዜ ገደብ እንዳለ ልናረጋግጥላቸው ይገባል፡፡ ዶ/ር ዐብይ ለይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ካስፈለገ ህይወታቸውን ለመሰዋት የጨከኑ ታላቅ መሪ መሆንዎን እንኳን ህዝብና ፈጣሪ ሰይጣንም ሳይቀር ይመሰክራል፡፡ በሰሞኑ ከተበሰረው ነዳጅና ጋዝ ግኝት እንዲሁም ከአስተዋይ የኤርትራ አመራሮች ከተበረከተው የነጻ ወደብ የፍቅር ምላሽ ባለፈ የይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር አቋምዎ ህዳሴያችንን እውንና ፈጣን እንደሚያደርገው አምናለሁ፡፡ እነዚህ ለይቅርታና ፍቅር የተዘረጉ እጆች ከቅርብና ሩቅ ብዙ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችንና መንግስታትን ለትብብርና መደመር እንደሚጠሩ አስባለሁ፡፡ ትንንሽ ስኬት አይመጥንዎትምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎ የብረት ማዕድን በሃገራችን ማውጣት እንደሚሆን እተማመናለሁ፡፡ ዶ/ር ዐብይ የሚከተለውን በቅርብ ይፋ ቢያደርጉ እመኛለሁ

በተለያዩ የሃላፊነት እርከኖች ተሰይመው (በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ቢሆኑም ባይሆኑም) በደልን የፈጸሙና የማይገባን ሃብት የሰበሰቡ ጥፋታቸውን ዘርዝረው፣ ተጸጽተውና ይቅርታ ጠይቀው የማስተካከል እርምጃ ለሚወስዱ (ለምሳሌ በሃገር ውስጥና በውጭ አላግባብ ያከማቹትን ሃብት መመለስ) ለአንድ ወር ብቻ የሚዘልቅ ሙሉ ይቅርታ መንግስት ያደርጋል፡፡ የምህረት ደጁ ከተዘጋ በኋላ (ከወር በኋላ) በደለኝነታቸው የሚረጋገጥ አካላት በፍትህ ስርዓቱ መሰረት ሙሉ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ ይህም እድል በቀጣይ በንግድ፣ በሃይማኖትና ልዩ ልዩ ተቋማትም ለተሰማሩ ሃላፊዎች ይሰጣል፡፡ የይቅርታውም ጥያቄ በሚመለከተው አካል ተቀባይነትን ሲያገኝ ከፌደራል እስከ ወረዳ የሚዘልቅ የይቅርታና ጥላቻን የመቅበር ስነ-ስርዓት ይከናወናል፡፡

ለዚህ ታላቅና ታሪካዊ ጅምር እኔም ተደምሬአለሁ!!


ሳምሶን ሃይለጊዮረጊስ


39 views0 comments

Comentarios


bottom of page