የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ደግነት ለጤንነት ብቻ ሳይሆን ለረዥም እድሜ ይጠቅማል

ደግነት ምን ያስገኛል? ምናልባት ደስ የሚል ስሜት? . . . አዎ በእርግጥም መልካምነት በሕይወታችን ጥሩ ነገሮችን ያስከትላል። ተመራማሪዎች ደግነት ከሚፈጥርልን አወንታዊ ስሜት ባሻገር እድሜያችንንም እንደሚያረዝም ደርሰንበታል ይላሉ።
በእርግጥ ደግነት ስንል ምን ማለታችን ነው? ለምንስ አስፈላጊ ነው? የሚለውን ጥያቄ ተመራማሪዎቹ አንስተው በዝርዝር ለመረዳት ሲነሱ ነገሩ በሰው ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ነገር ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ሆነው ነበሩ።
ምርምሩን የመሩት ዳንኤል ፌስለር በተለይ ሌሎች መልካም ሲያደርጉ የሚመለከቱ ሰዎች እንዴት ደግ ለመስራት ሊነሳሱ እንደሚችሉ በቅርበት በመፈተሽ "ተላላፊ ደግነት" ያሉት ክስተት ማንን በተለይ በአወንታዊ መልኩ እንደሚነካ መርምረዋል።
ተመራማሪው "በአሁኑ ዘመን ደግነት በራቀው ዓለም ውስጥ እንገኛለን" በማለት በዓለም ዙሪያ በፖለቲካ አመለካከትና በሐይማኖት ሰበብ በሰዎች መካከል የሚከሰተው ግጭት እየጨመረ መሆኑን ይናገራሉ።
ደግነት ሌሎችን ለመጥቀም ከሚደረጉ አስተሳሰቦችን፣ ስሜቶችንና እምነቶችን ከሚያንጸባርቁ ተግባራት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ በመግለጽ፤ እነዚህም በውጤታቸው ሌሎችን የሚጠቅሙ ሲሆኑ ሌላ ውጤት ለማምጣት የምንጠቀምበት እንዳልሆነ ተመራማሪው ይናገራሉ።
በተቃራኒው ደግ ወይም መልካም አለመሆን "ሌሎችን ያለመቀበል፣ ለሌሎች ደህንነት ዋጋ ያለመስጠት ማሳያ ነው" ይላሉ።
ይህ በደግነት ላይ የተደረገው ምርምር ያስፈለገው "ደግነት ስለምን በዘመናዊው ዓለም ተጓደለ የሚለውን ለመረዳት" እንደሆነ ለጥናቱ የገንዘብ ድጋፍ የሰጠው ተቋም ባለቤቶች ተናግረዋል።
ተመራማሪው ዳንኤል ፌስለር እንደሚሉት ደግነት ብዙ ገጽታዎች አሉት "የደግነት ተግባር ለሰው ስናደርግና ለእኛም ሲደረግልን በሁሉም መልኩ ለጤናችን ጠቃሚ ነው። አደገኛ የሆነን ውጥረት ወይም ጭንቀትን በማስወገድ በጎ ውጤት አለው" ይላሉ።
ደግነት ወይም መልካምነት ትልልቅ ድርጊቶች በመፈጸም ብቻ የሚገለጹ ሳይሆኑ ቀላል የሚባሉ ንግግሮችና የሰላምታ ልውውጦችም ከዚሁ አንጻር ሊታዩ ይችላሉ።
ለራሳችን ይልቅ ለሌሎች በጎ ማድረግ ቀላል ነው
ብዙም ግድ ባንሰጠውም በመደብር ውስጥ የሚገኙ አስተናጋጆች የሚያሳዩን ፈገግታና የሚሰጡን ሰላምታ በአጠቃላይ ጤናችን ላይ የእራሱ የሆነ አውንታዊ ውጤት እንዳለው ጥናቱ አመልክቷል።
"ለሌሎች መልካም ስለመሆን ማሰብና በደግነት ድርጊቶች ውስጥ መሳተፍ የደም ግፊትን ዝቅ ያደርጋል። በተጨማሪም ድብርትና ጭንቀትን የማከም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።"
በኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ ዶክትር የሆኑት ኬሊ ሃርዲንግ በቅርብ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት መልካምነት የሰውነታችንን በሽታን የመከላከል አቅም ይገነባል፣ የደም ግፊትን ዝቅ በማድረግ ሰዎች በረጅም እድሜ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።
ጠቃሚ ነጥቦች ደግነት ለተሞላበት ሕይወት
የሚሰሙ መስለው መልስ ለመስጠት እራስዎን ከማዘጋጀት ይልቅ በሐቅ ሌሎች የሚሉትን ማድመጥ ይጀምሩ
2. በመጥፎ ሁኔታ ምላሽ ለሚሰጥዎት ሰው በመልካምነት ይመልሱ። (የሚያመነጫጭቅዎትን ሰው ያስቡና ወዳጅነት በተሞላበት ሁኔታ "ቀንህ/ሽ ጥሩ አልነበረም?" ብለው ይጠይቋቸው። በዚህም ውጥረት የተሞላበትን ሁኔታ በቀላሉ ማርገብ ይችላሉ)
3. በሰዎች ሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ነገሮች ሁሉ ችላ መባል፣ አለመፈለግና አለመፈቀር የሰውነትን ክብር የመግፈፍ ያህል ስለሆነ ችላ የተባለን ሰውን ያቅርቡ። ይህን ሲያደርጉ ለሰዎች ዋጋን ይሰጣሉ።
4. ከመልካምነት የራቀ ድርጊት ሲፈጸም ሲገጥምዎ የእርሶ ችግር አለመሆኑን ይረዱ። ለድርጊቱ ምላሽ እንዲሰጡ ሲገፋፉም እራስዎን ይቆጥቡና በጥልቀት ትንፋሽ ወስደው እራስዎን ያርቁ።
ዶክትር ኬሊ "ደግነት በዙሪያችን ያሉ ነገሮችን በመለወጥ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን እንድንፈትሽ ይረዳናል" በማለት "በአብዛኛው ከእራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች መልካም ለመሆን ይቀለናል" ሲሉ አክለዋል።
ለእራሳችንም ሆነ ለሌሎች ደግ መሆንን ለማበረታታት በርካታ መንገዶች አሉ። "በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በቤታችን ውስጥ ደግና ሩህሩህ በመሆን መልካም ውጤትን ለማግኘት እንችላለን" ይላሉ።
በህክምና በኩል ቴክኖሎጂው እየተሻሻለ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የተንከባካቢን ደግነት ያህል ትልቅ ነገርን ግን መፍጠር አይቻለንም ይላሉ ዶክተሯ። በተለይ ደግሞ በአእምሮ ጤናና አካላዊ ጤና መካከል ያለው ትስስር እጅግ ወሳኝነት በመጥቀስ።
ሰዎች ሌሎች የደግነት ተግባርን ሲፈጽሙ ሲመለከቱ ተመሳሳዩን ለመፈጸም ይነሳሳሉ ይላሉ ባለሙያዎች። ስለዚህ የምንፈጽማቸው በጎ ነገሮች በእኛ ድርጊት ላይ ብቻ የሚቆሙ ሳይሆኑ በሌላ ጊዜ ለሌሎች ሰዎች ለሌሎች እንዲፈጸሙ እያገዝን መሆኑን መረዳት ያስፍለጋል።
ግጭቶችና ጥላቻ በተበራከተበት ዓለም የመልካምነት ድርጊቶች ጎልተው ይሰማሉ፤ ያዩ የሰሙ እንዲሁም የተደረገላቸው ጭምር ሳይቀሩ ደግ ማድረግን ይለምዳሉ፤ ለሌሎችም ያስተላልፋሉ።
በአንደኛው የዓለም ክፍል የሚፈጸም የደግነት ተግባር አየርና ባሕሩን አቋርጦ ከአድማስ ባሻገር በመጓዝ በሌላ ቦታ ይሰማል ይፈጸማል። ለዚህ ነው ደግንት/መልካምነት ተላላፊ ነው የሚባለው።
ምንጭ - BBC Amharic