የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
“ድሮን እየኖሩ ትውልዱን ወደኋላ እየመለሱ መስዋዕት የሚያደርጉ ፖለቲከኞች ጡረታ ሊወጡ ይገባል”አቶ ሙሳ አደም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

በድሮ አስተሳሰብ እየኖሩ በአዲሱ ኃይል ጉልበት፤ ዕጣ ፋንታ፤ የወደፊት ራዕይ ላይ በመጫወት መስዋዕትነት የሚያስከፍሉት ፖለቲከኞች ጡረታ መውጣት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ገለጹ። የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ የዓለም ፖለቲካ በጣም ተለዋዋጭ ነው። ትናንት የነበረው የፖለቲካ አረዳድ ዛሬ አይሠራም፤ የለምም። በእኛ አገር ፖለቲካ ትናንት የሁልጊዜ ውሎ ነው። ገና ኃይለስላሴና ምኒልክ ዘመንን ያልተሻገረ ፖለቲከኛ ይዘን ቀጥለናል። ይህ ሁኔታ አገርን ስለማያሻግር እነዚህ ፖለቲከኞች ጡረታ ሊወጡ ይገባል። በምትኩ የሚሠራ ኃይል ወንበሩን መረከብ አለበት። እነዚህ አካላት በጊዜያቸው ወቅቱ የሚጠይቀውን መንገድ ሂደው ብዙ ሠርተዋል፤ ለአገርም ያበረከቱት ነገር አለ። ይሁንና ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› አባባላቸው ዛሬም ቀጥሏል። ይህ ደግሞ ወጣቱን እንዳይሠራና አገሩን እነርሱ በሠሩት ላይ ጨምሮ እንዳያሻግር እንቅ ፋት ሆነውበታል ብለዋል። ሀገራዊ ፖለቲካውና ፖለቲከኛው እንዲሻሻል ከተፈለገ እነዚህ ዘመናቸው ያበቃ ፖለቲከኞች ለተተኪው ወንበር መለቀቅ እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል። የቀድሞ ሀገራዊ የፖለቲካ አካሄድ መልካምም መጥፎም ታሪኮች እንደነበሩት የሚያነሱት አቶ ሙሳ፤ በዘመናቸው የነበረው የፖለቲካ አረዳድ ይህንን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋልና አድርገውት አልፈዋል። አገርንም ለዛሬው ትውልድ ሠርተውለታል። ሆኖም ያንን ታሪክ አድርገን እንጂ ኑሯችን አድርገን መቀጠል የለብንም። ታሪኩ እንደ ታሪክነቱ ይነበብ፤ ይታወቅ፤ እውነታውን ሁሉም ይረዳው፤ ነገር ግን በዚያ ታሪክ እንድንኖር ሊፈረድብን አይገባም ብለዋል። ትውልዱ ነገው እንዲበላሽ መፍቀድ የለበትም የሚሉት ሰብሳቢው፤ ዛሬ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። በዛሬው አካሄድ የዛሬው ትውልድ መሠራት አለበት። ነገን እያነሱ ትውልዱን ወደትናንት መውሰዱና ማበጣበጡ አገርን ወደኋላ ከመመለስ አይተናነስም። በተለይ ፖለቲከኛው የትናንቱን ለትናንት በመተው ዛሬ በራሱ መንገድ እንዲሻገር እና ለውጥ እንዲመጣ ለተተኪዎች ቦታውን መልቀቅ እንደሚኖርበት አመልክተዋል። አገሪቱ በርከት ያሉ በእውቀት መምራትና መሥራት የሚችሉ ወጣት ፖለቲከኞች አሏት፤ እነዚህን ወደ ሥራ ማስገባት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ሙሳ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለፉት ዓመታትን የምንኖርበት ሊሆን አይገባምና ተሠርታ ያለቀችውን ኢትዮጵያን እንዲሠሩ ለትውልዱ እንፍቀድ ብለዋል። የቀደሙት የትናንት ፖለቲከኞች ሌላ ሰው እንዲመጣባቸው አይፈልጉም፤ ወጣት ፖለቲከኛን ማየት ያማቸዋል ያሉት አቶ ሙሳ ፤ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ፖለቲከኛም ሆነ ፖለቲካው እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ ወጣቱን የእሳት እራት እንጂ ባለተስፋ አላደረጉትም ብለዋል። የመሥራት ባህልን እንዲያዳብር እንዳልረዱትም አመልክተዋል። እንደ አቶ ሙሳ ገለጻ፤ የተማረና የተመራመረ፤ የተሻለውን ለአገር ለማምጣት የሚጥር፤ ጉልበት ያለው ሯጭ ፖለቲከኛ አገር ያስፈልጋታል። እንደውም ‹‹ የተማረ ይግደለኝ›› እንደሚባለው የአገር ፖለቲካ መፈጠር የሚጀምረው ፖለቲከኛውም ፖለቲካውም በእውቀትና በአዲስ አስተሳሰብ ሲቃኝ ብቻ ነው። ስለሆነም የወቅቱን የፖለቲካ ጽንሰሃሳብ ያልተረዱ ሰዎች እየመሩ ግራ ከሚያጋቡ ጡረታ መውጣቱ ለነሱም ለሀገርም እንደሚበጅ ጠቁመዋል። ፓርቲ የሚባለውም በዘመድ ተሰባስቦ የሚመሰረት ነው። ይህ ደግሞ አገር ለመምራት ሳይሆን ቤተሰብ ለማስተዳደር ብቻ የሚያስብ የሚያደርገው ተግባር ነው። እናም መሰረታዊ የፓርቲ ቁመና ያለው በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ፓርቲ ከሌለ ፖለቲካም ፖለቲከኛም ሊፈጠር አይችልም። ሁለቱም ያለመኖራቸው መንስኤ ነው አሁን ለአገር ፈተናና ዋጋ ማስከፈል ያበቃው ብለዋል። ፓርቲው እንደ ፓርቲ የሚሠራው ሥራ የለም። ህዝቡም ከፓርቲው የሚጠብቀውን እያገኘ አይደለም። ስለዚህም ህዝብ ከመጠቀም ይልቅ በችግር ውስጥ ተዘፍቆ ዓመታትን ዋጋ እየከፈለ እንዲኖር መደረጉንም አመልክተዋል። ዘመኑን ያልዋጀ፤ አገርን ከፍ ለማድረግ በማያስችል ጉዳይ ላይ መስዋዕት እየከፈልን ነው የሚሉት አቶ ሙሳ፤ ትውልዱን በማደንቆር የተካኑ ፖለቲከኞች ጡረታ ይውጡና አዳዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብና እውቀቱ ያላቸው አካላት ወንበሩን ይረከቡ ብለዋል። ሀገራዊ የፖለቲካ አካሂዶች በመርህ፤ በፖሊሲ ላይ የተመሰረቱና ከአገርና ከህዝብ ጥቅም አንጻር የተቃኙ መሆን መቻልም አለባቸው። በዚህ ላይም በስፋት መሥራት መጀመር አለብን ሲሉም ተናግረዋል። አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2012