የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ጥቂት ስለ ሸምሱ አማን (በኢዱና አህመድ)

ሸምሱ እና ጓደኞቹ የመስቃን ማህበረሰብ የፈለጋቸውን መልካም ነገሮች ሊያገኝ የሚችለው እነእርሱ በተከተሉት መንገድ ማለትም ከላይኛው ጉራጌ ፍላጎት ጋር በተጣጣመ መልኩ ሲፈጸም ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል።
እኔም ሆንኩ ብዙሃኑ የመስቃን ተወላጅ በሚባል መልኩ የመስቃን ማህበረሰብ የአስተዳደሪያዊ ችገሮቹ ከተቀረፉለት ከተቀሩት የጉራጌ የማህበረሰቦች ክፍሎች የሚኖረው ግኑኝነት እንደተጠበቀ ይቆያል ወይም ከቀድሞው በተሻለ መልኩ ግንኙነቱ የጠነከረና የተሻለ ይሆናል የሚል አመለካከት እና አቋም አለን ብዬ በድፍረት እናገራለሁ።
በእርግጥ ሸመሱ አማን ጉራጌ ዞን ውስጥ ባለው የስራ ዘርፍ በመስቃን ማህበረሰብ ኮታ መስቃን ማህበረሰብን በመወከል እየሰራ እንደሆን እሙን ነው። ለምን ከብዙሃኑ የማህበረሰብ፣ እንዲሁም የህዘቡን አደራ ተቀብለው በወረዳ እና በከተማ ዘርፍ ከሚሰሩ አመራሮች በተጨማሪም ለማህበረሰብና አካባቢው ለውጥ ከሚተጉ ምሁራን በተለየ መልኩ ወይም የተለየ አቋም ያዘ ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ ወይም እውነታውን እርሱ እና እርሱዎቹ ቢመልሱት ደህና ይሆናል።
ማህበረሰባች እና አካባቢያችንን በተመለከተ የሸመሱ አማን መንገድ ከእኔ ፍላጎት በእጅጉ የተቃረነ ነው። ነገር ግን የሁለታችንም ታርጌት ወይም መዳረሻ አንድ ነው ብዬ አስባለሁ። አዎን… የእኔም ሆነ የብዙሃኑ እኔዎቹ ፍላጎት ለተበደለው ወገናችን ለአስተዳደሪያዊ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ሲሆን የሸምሱ አማን ከእኔውና እኔዎቹ ተመሳሳይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
በእዚህ ጽሁፍ እኔ በዋነኝነት ለማጉላት የፈለኩት ጊዜን እና አመለካከትን ነው። ሁሉም ባይባልም እንኳን ሰዎች እንደ ጊዜው እና እንደሁኔታቸው አመለካከታቸው ተለዋዋጭ ስለ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል ሸምሱ አማን በሆነ ወቅት (ካልተሳሳትኩ) ከጉራጌ ዞን ባለስጣናት እና ከመዋቅሩ በተቃረነ መልኩ በሶሻል ሚድያው ትችቱን ሲገልፅ እንዲሁም አመለካከቱን ሲያጸባርቅ እንደነበር ሁላችንም የምናውቅ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በመንግስት ሹመት ጉራጌ ዞን ውስጥ መስራት ሲጀምር በፊት ሲያራምድ ከነበረበት የአቋም ደረጃ ላይ አልተገኘም። ለምን? ለሚለው የውስጡን… የሸሸገውን… እርሱው ስለሚያውቅ ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ከሆነ ምላሽ ቢሰጥ እጅጉን ደስ ይለኛል። የሸመሱ አማን ከሌላው ጋር ያለው የአመለካከት ልዩነት እንዳለ ሆኖ በተሰጠው የዞን የስራ ዘርፍ ላይ ሆኖ እራሱን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ አደገኛ ወይም የመስቃን ማህበረሰብን ሁሉ ሊያስከፋ እና ሊያስቆጣ የሚችል አጀንዳ እንዳይፈጸም ሲከላለክ እና ሲያከላክል እንደነበር በማስረጃ አውቃለሁ። ለዚሁም ነው እላይ እንደ ተወላጅ መዳረሻችን ወይም ታርጌታችን አንድ ነው ያለኩት።
ሌላው... ወዳጆቼ የማህበረሰባችንን ስም ለማጉላት እና ለመጠገን በተጨማሪም የአስተዳደሪያዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በተደረጉት የሁለት አስርት የሁሉም ተወላጅ የተሳትፎ ጥረቶች ውስጥ ስንቶቻችሁ ናችሁ አሁን ላይ ሸምሱ አማን እያራመደ ያለው አቋም ውስጥ ያልነበራችሁት? ወይም በግልጽ ቋንቋ የላይኛዎቹን ካልያዝን የአቀድነው አይሳካልንም በሚል ስንኩል ሃሳብ በፍቅር ከንፋችሁ ስትላላሱ እንደነበራችሁ እና ከናንተ በተለየ መልኩ ሃሳባቸውን የሚያራምዱ ወይም መስቃን ብቻ የሚል ጠንካራ አቋም በያዙት ላይ ጠጠር ወርዋሪ አሰማርታችሁ እንደ ነበር ፀሃይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ስለዚህ አመለካከት እንደጊዜው እና እንደ ሁኔታችን ተለዋጭ ስለመሆኑ እናንተው ህያው ምስክር ናችሁ። በእርግጥ የመስቃን ማህበረሰብ ጉዳይን በተመለከተ አንድ አይነትና ቋሚ አቋም የነበራቸው በግሌ ሶስት ሰዎችን አውቃለሁ። አቋማቸው ቋሚ እና “ቤበች ኤበች” ነው። ከሌላው ማህበረሰብ ጋር የነበራቸው ይፋ እና ይፋ ያልሆነ ግኑኝነት የራሴ የሚሉትን መብት ባስጠበቀ መልኩ ብቻ ነበር። ይሆናልም።
ወደ መደምደሚያው ስመጣ… በእርግጥ ግለሰቦች የፈለጉትነ አመለካከት የማራመድ መብት ህጉ ቢያጎናጽፋቸውም የወከላቸው ማህበረሰብን ፍላጎት ማከበር እና ማስፈጸም እንዳለባቸው የሚታወቅ ነው። ከዚህ አንጻር ሸምሱ አማን እርሱ ብቻ ለተረዳው እና ያመነበትን ጉዳይ ማህበረሰብ ላይ ለመጫን መሞከሩ ከማህበረሰብ እቅድ እና ፍላጎት አንጻር ትልቅ ስህተት ነበር። ይሁንና ዛሬ የብዙሃኑ እቅድና ፍላጎት አሸናፊ ሆኖ በአላህ እገዛ ምስራቅ ጉራጌ ዞን ተመስርቷል። እርሱ ተሸናፊ ነው። ህዝብ ግን አሸናፊ ነው። ህዝብ ይቅርም ባይ ነው። በተጨማሪም በፖለቲካው አለም የሃሳብ ፍጭት የተለመደ ሲሆን ጥሩ የማይሆነው የሃሳብ ፍጭቱ ከተቋጨ በዃላ ግለሰባዊ አቋም ያራመድን እንደሆነ ነው።
ቸር እንሰንበት!!
ኢዱና አህመድ ኡስማን