top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጥብቀት – Attachments (በሚስጥረ አደራው)



“ያልበሰለው ፍሬ ከቅርንጫፉ ጋር ተጣብቆ ይቆያል፤ ስላልበሰለ ለተሻለ ነገር  አይመጥንም። የበሰለውና የሚጣፍጠው ግን ከቅርጫፉ እራሱን ያላላል።”


“The immature fruit clings, tightly to the branch Because , not yet ripe, it’s unfit for the palace. When fruits become ripe , sweet, and juicy,they loosen their hold.”- RUMI


ጥብቀት/Attachment/ ሰው ከሰውነቱ በላይ ሌሎች ነገሮች ላይ ሲንጠለጠልና ያለነሱ መኖር እንደማይችል ሲሰማው የሚፈጠር ስሜት ነው። ህልውናችንና እርካታችን ከእኛ ውጪ በሆኑ ነገሮች ሲወሰን፤ በመንፈስ ከነገሩ ጋር ተጣብቀናል ማለት ነው። ይህ ስሜት እንደ ሩሚ ምልከታ እና አገላለጽ የጥሬነት ምልክት ነው። ቅርጫፉ አለም ነው፤ ፍሬዎቹ እኛ። በዙሪያችን ካሉ ነገሮች ጋር ምን ያህል ተጣብቀናል? ምን ያህል ከተጽዕኖ እረቀን በራሳችን መቆም እንችላለን? ነፍሳችን ያለሰንሰለት መቆም ይቻላታል? ከገንዘብ ጋር፤ ከክብር ጋር፤ ከሰዎች ጋር፤ ለራሳችን ካለን አመለካከት ጋር፤ ሌሎች ስለእኛ ካላቸው አመለካከት ጋር፤ ባጠቃላይ ከእኛ ውጪ ከሆኑ ነገሮች ጋር ያለን ቁርኝት ወይም ግንኙነት የነፍሳችንን መብሰል እና ጥሬነት የምንለመለከትበት መንገድ ነው።

ግንዱን ተጣብቆ የሚኖረው ፍሬ እሱ ያልበሰለው፤ ጥሬ የሆነው ነው። ይህ ፍሬ እየበሰለ ሲሄድ ከቅርንጫፉ ጋር ያለውን ቁርኝት እያላላ ይመጣል….ቀስ እያለ …ያለድጋፍ የተንጠለጠለ ይመስል ዘና ብሎ ይቀመጣል። የሰው ልጅ ነጻነት በዚህ ሀሳብ ላይ በእጅጉ ይመሰረታል። እራሳችንን ከብዙ ነገሮች ጋር ባጣበቅንና ፤ ባቆራኘን ቁጥር ደስታችንና እና ሰላማችንን የሚወስኑት ውጫዊ ነገሮች እየበዙ ይመጣሉ። መንፈሳችን እየበሰለ ሲሄድና ብዙ ነገሮችን ከልክ በላይ አጥብቀን መያዙን ስንተው፤ ከአለም ቅርጫፍ ላላ ብለን በተሻለ ነጻነት መኖር እንችላለን (ፍጹም ነጻነት አለ ለማለት ስለሚከብደኝ ነው፤ የተሻለ ለማለት የተገደድኩት)።

በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን፤ ሰው ደስታ እና ሰላሙን የሚቆጣጠረው ውስጡ ባለው የገዛ መንፈሱ አይደለም። ውጫዊ ነገሮች በእጅጉ ስሜታችንን የመቆጣጠር አቅም አላቸው። ማንነትቻችንን ባሉን ነገሮች ወይም በውጫዊ ነገሮች መግለጽ ስንጀምር፤ ክንፋችንን እንሰብራለን። ችግሩን ካነሳም መፍትሄውን መሻታችን አይቀርምና፤ እነሆ ወደመፍትሄ የምታመላክት አንዲት አጭር ታሪክ ላካፍላችሁ።

Letting Go- “you only lose when you cling to”- Buddha

መተው- እራሳችንን ከውጫዊ ከነገሮች ጋር አለማሰር ወይም ደግሞ ከልክ በላይ ነገሮችን አጥብቆ አለመያዝ፤ የጥብቅነት ተቃራኒ ነው። የሰው ልጅ ነጻነት በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው። “መተው” ማለት ከተስፋ መቁረጥ ጋር አያይዘነው ሳይሆን፤ ከህይወት ፍሰት ጋር አብሮ የመፍሰስን ጥበብ ለማስረዳ የምንጠቀምበት መንገድ ነው። አንዳንድ ነገሮች እኛ ባላሰብናቸው መንገድ ሳይሆኑ ሲቀሩ፤ የሚኖረን ምላሽ ምንድን ነው? ይህንን አስተሳሰብ የሚያስረዳ አንድ የዜን ፍልስፍና ታሪክ ላካፍላችሁ (Zen Philosophy)፤

በድሮ ግዜ በእስያ ያሉ አዳኞች ጦጣን የመያዝ አንድ ጥበብ ነበራቸው። ይህ ጥበብም እንደሚከተለው ነው፤ አዳኞቹ ኮኮናት የተሰኘውን ፍፌ ( ክብ ተልቅ ያለ ፍሬ ነው) ከላዩ ላይ ቀዳዳ ያበጁለትና ውስጡ ያለውን ንጥረ ነገር ያፈሱታል፤ ቀጥሎ በውስጡ ሌላ ጣፋጭ ነገር ይከቱበታል። በመጨረሻ ይህንን ፍሬ ይወስዱና በቀላሉ እንዳይወድቅ አድርገው ዛፍ ላይ ይሰቅሉታል። እንግዲህ አንድ ጦጣ ሲመጣ፤ ይህንን ፍሬ ያየዋል፤ በውስጡ ያለውን ጣፋጭ ነገር ለመውሰድ እጁን ወደውስጥ ይሰዳል። ቀዳድው ጠበብ ያለ ስለሆነ፤ የጦጣው እጅ ፍሬውን ሲይዝ  መዳፉ ወደ ቡጢነት ስለሚቀየር በገባበት መልኩ ለመውጣት ይከብደዋል። ጣፋጩን ፍሬ ካልለቀቀ በቀር ፤ እጁ በጭብጥ መልኩ ከኮኮናቱ ሊወጣ አይቻለውም። ጦጣው በዚህ ሁኔታ የያዘውን አልለቅም ብሎ ሲታገል፤ አዳኙ ይመጣና ይይዘዋል።

የእኛም ህይወት ከዚህ ጦጣ እምብዛም አይርቅም። ጭብጥ አድርገን የምንይዛቸው ብዙ ነገሮች ናቸው፤ ወደፊት እንዳንሄድ እና ነጻ እንዳንሆን የሚያደርጉን። ነጻነትን ከመንፈግ አልፈው ወደ ሀዘን የሚከቱን እኒህ አጥብቀን የምንጨብታቸው ነገሮች ናቸው። አንዳንዴ የጨበጥነው አልሳብ ሲል መልቀቅን መማር ይኖርብናል። ያለዚህ ነገር መኖር አልችልም ባልን ቁጥር፤ ልክ እንደ ጦጣው እራሳችንን ለባሰ ሀዘን እያጋለጥን ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ እኮ በመተው ውስጥ ብዙ ማግኘት አለ ( ፈረንጆች Letting go ይሉታል)። ነጻነታችንን የምንፈልግ ከሆነ ተጣብቀን ከኖርንባቸው ቅርንጫፎች እራሳችንን ማላላት ግድ ይለናል። እውነት ነው ነጻነት ብስለትን ይጠይቃል። እራሳችንን ከሌሎች ነገሮች ተጽዕኖ ማራቅ ቀላል ነገር ሆኖ አይደለም የምናወራው። ነገር ግን በስተመጨረሻ የእያንዳንዳችን ጥረት ሀሴት የሚሰጠንን ነገር ማድረግ አይደለምን (reducing Suffering)?

የሰው ልጅ እራሱ ከሚፈጥራቸው የመንፈስ ካቴናዎች ነጻ ወጥቶ የመኖር አቅም አለው።ሰውን ሰው የሚያደርገው ውስጡ ያለው መንፈስ ብቻ ስለሆነ።ሀዘኑ ሁሉ የሚመጣው “ያለዚህ ነገር መኖር አልችልም” ማለት ስንጀምር ነው። ነፍሳችን እንደ ጦጣው እጅ ከተጨበጠች፤ በቀላሉ የማትወጣበት ማነቆ ውስጥ ትገባለች። እናም የነፍሳችንን መብሰልና ጥሬ መሆን፤ ከነገሮች ጋር ያለንን ጥብቅ ቁርኝት በማየት እንዲሁም እንደጦጣው እለቃለው አልለቅም በምንላቸው ነገሮች ተመርኩዘን ማውቅ ይቻለናል።


ሚስጥረ አደራው

34 views0 comments
bottom of page