top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጭብጨባ! የድንቁርናና የአንባገነንነት ሽፋን (ዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ )


ሰው ልብ የሚፈነቅል ደስታ ሲሰማው ስሜቱን በእልልታ፣ በጭብጨባ፣ በፈንጠዝያ… እንደአውዱ ይገልፃል፡፡ እልልታ በአብዛኛው ከመንፈሳዊ አክብሮትና አድናቆት ጋር የተያያዘ ነው፤ ለታቦት እልል ይባላል፡፡ አዋቂ/ጠንቋይ አውልያው ወርዶ ሲፈርድም እልል ይባላል፡፡ ጭብጨባ ደግሞ ከእልልታ ይልቅ ሰዋዊ (አለማዊ) ነው፡፡ ለምናደንቀው ሰው እናጨበጭባለን ደጋግመን፡፡

መቼም በዚህ ዘመን ከቀበሌ እስከ ፓርላማ በየደረጃው እንደሚካሄዱ የፖለቲካና የአስተዳደር ስብሰባዎችና ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ ግድም እንደሚከናወኑ የፊልም ምረቃዎች ጭብጨባ የሚበዛባቸው መድረኮች በሀገራችን መጥቀስ ያዳግታል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የጭብጨባው መብዛት አይደለም፤ ጭብጨባው ተፈጥሯዊ ትርጉሙን ማጣቱ ነው፡፡

የዛሬ ሃያ አመት ግድም ብሔራዊ ትያትር አንድ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ብሔራዊ ትያትር ስገባም ሆነ፣ ጥላሁን ገሰሰን ሲዘፍን በአካል ሳየው የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ እያንዳንዷን የእለቱን ክንውል በቅደም ተከተል ቀርጬ ይዤዋለሁ፡፡ ጥላሁን ገሰሰ ሊዘፍን ሲመጣ ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ ጭብጨባና ፉጨቱን አቀለጠው፡፡ እሱ ‹‹የትዝታዬ እናት›› የሚለውን ዘፈን ሲጀምር ነው ሰው ጭብጨባና ፉጨቱን አቁሞ የተቀመጠው፡፡ ዘፍኖ ሲጨርስም ሰዉ ጭብጨባውን አላቆም ስላለ እዚያው እቆመበት ዘፈኑን ደግሞ ዘፈነ፡፡ እንግዲህ ይህ ነው ተፈጥሮአዊው ጭብጨባ! ዛሬ ጭብጨባን በተፈጥሯዊ መልኩ ለማግኘት የነጥላሁንን ክሊፕ መቆፈር ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

ባለፈው ወር ከተመረቁ ፊልሞች መካከል በሁለቱ ምርቃት ላይ በዚሁ በብሔራዊ ትያትር የመታደም እድል ይሁን እርግማን አላውቅም ገጥሞኝ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ምርቃ ላይ የመድረክ አጋፋሪው በስንት ጥበቃ፣ የታዳሚን አንጀት አቃጥሎ ወደ መድረኩ ጫፍ መጣና እንደማጐንበዝ ቃጥቶ ሰላምታ ሰጠ፡፡ እኛ ስለተቀመጥን አላጐነበስንም፡፡ ቀጠለና ‹‹ምነው፣ የለም እንዴ?›› ጭብጨባ ጠየቀ፡፡ ሳይጀምረው የተሰላቸው ታዳሚ አጨበጨበ፡፡ ጆሮውን በእጁ ደግፎ ‹‹አልተሰማኝም›› የሚል ምልክት አሳየ፡፡ እጥፍ ጭብጨባ፡፡ አሁን እስቲ ጐበዝ! ማይክ የጨበጠ የመድረክ አጋፋሪ ወደ መድረክ መምጣት ምን ያስጨበጭባል? የአጋፋሪውምን መልክ እንኳ ያን ያህል የሚያስደስት አይደለም፤ እንደማንኛውም መደዴ የአዘቦት መልክ ነው ያለው፤ አለባበሱም እንዲሁ፡፡ ቀጠለና በፊልሙ ላይ የተሳተፉትን ዘረዘረ፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ስም ሲጠራ ማጨብጨብ ነበረብን፡፡ ካላጨበጨብን ይደግመዋል፤ እስከምናጨበጭብ፡፡ ታዳሚውም ሞቅ አድርጐ ያጨበጭባል፡፡ አይተን አይደለም ስሙን ሰምተን ለማናውቀው ሁሉ ካጨበጨብን በኋላ ፊልሙ ተጀመረ፡፡ ፊልሙ አልቆ መብራት እንደበራ ያ አስጨብጫቢ መጣና ‹‹ታዲያስ! በፊልሙ የተሰማችሁ እርካታ የት አለ?›› በፊልሙ ባረረ አንጀታችን ላይ እጃችንንም በጭብጨባ አሳርረን ወጣን፡፡

ዛሬ ዛሬ በየአጋጣሚው የምናያቸው የመድረክ አጋፋሪዎች ዋናው ስራ ማስጨብጨብ ነው፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ኮሜድያንም ሳያስቁን አጨብጭበንላቸው ከመድረክ ይወርዳሉ፡፡ ነብሱን ይማረውና ተስፋዬ ካሳ በሳቅ ፍርስ አድርጐ ያስጨበጭበን ነበር፡፡

በየቀበሌውና በየወረዳው ስኳርና ዘይት አቅርቦት ላይ ሊወያይ የተሰበሰበ ነዋሪ፣ የሚመለከተውን አካል የስኳርና የዘይት አቅርቦት እክል የዳሰሳ ገለፃ ካደመጠ በኋላ በጭብጨባ ክንዱን አላሽቆ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተቀር አርቲስቶችን ሰብስበው አወያይተው ነበር፡፡ ታዲያ አርቲስቶቹ ለአንዳንድ ስራ ባንክ ብድር እንደማይሰጣቸው አማረው በመንግስት በኩል ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀው ነበር አሉ (አንድ ጓደኛዬ ነው የነገረኝ)፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የባንክ አሰራር እንደሆነና፣ ባንክ የራሱ አሰራር እንዳለው ሲመልሱ፣ አርቲስቱ ሁሉ አዳራሹን በጭብጨባ አቀለጠው አሉ፡፡ ጭብጨባ የደስታ ስሜት መግለጫ ነው ይሏችኋል ይቺ ናት!

ታዲያ ይህ ከቁብ የሚገባ ተግባር ሳያከናውኑ ማስጨብጨብና አንጀት እያረረ ማጨብጨብ ከየት የመጣ ነው? የዚህ የግብር ይውጣ ጭብጨባ ምንጭ መቼም በየመድረኩ የሚዘጋጀው ኪነ ጥበብና በየቲቪው የሚታየው ‹‹የሾው›› ዝግጅት አይደለም፡፡ እነዚህ ዝግጅቶች የግብር ይውጣ ጭብጨባ ምን ያህል ትውልዱን እንደቃኘው ማሳያ ናቸው፡፡ አንድ የመድረክ አጋፋሪ ‹‹አጨብጭቡ›› ሲል፣ ታዳሚው ‹‹አናጨበጭብም›› ቢለው ዝግጅቱን ከማቅረብ በስተቀር ምንም አያመጣም፡፡ ‹‹አጨብጭብ›› ሲል፣ ‹‹አላጨበጭብም›› ቢባል የሚቆጣው ፖለቲካዊ አስተዳደሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መሰረቱን በስፋት የጣለው ዘመነ ደርግ ይመስለኛል፡፡ በዘመነ ደርግ ህዝብ ንብረቱ ሲወረስ፣ ልጆቹ ሲታሰሩና ሲገደሉ… ወዘተ ግራ ክንዱን እየወነጨፈና እያጨበጨበ ‹ድርጊቱን› ሲደግፍ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ግራን አለማንሳት/ አለማጨብጨብ በቀኝ ያውላል፡፡ በቀኝ መዋል ደግሞ እስርና ሞት አለበት፡፡ እናስ! እናማ ህዝቡ ደርግን በለጠው፡፡ ቀድሞ ክንድን ማወናጨፍ፣ ቀድሞ ማጨብጨብ ጀመረ፤ የልቡን በልቡ ይዞ፡፡ ባያሳስር፣ ባያስገድል እንኳን ያላጨበጨቡለት ባለስልጣን ቂም ይይዛል፡፡ በመንግስት እርከን ላይ በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት ከህዝብ ፍላጐት የሚፃረር ፖሊሲያቸውንና አምባገነን የአስተዳደር ፈሊጣቸውን ጥሩነትና ታላቅነት ጠመንጃ ተደግፈው በሚያስተዳድሩት ህዝብ ጭብጨባ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡

ደርግን ተከትሎ ኢህአዴግ መንግስት ሲሆን፣ የጠበቀው ህዝብ (እድሜ ለደርግ) የመንግስትን ሞራ አንብቦ የሚያጨበጭብ ነበርና የቤት ስራው ቀሎለት ነበር፡፡ ኢህአዴግን የጠበቀው ህዝብ ተደስቶ ሳይሆን፣ ለማስደሰት የሚያጨበጭብ ነበር፡፡ ለልጆቹ ሞት ተምሳሌት ተደርጐ፣ በጠርሙስ የተሞላ ደም አደባባይ ሲታጠብበት ያጨበጨበ ህዝብ፣ አንቀጽ 39 ማጨብጨብ እንደምን ይገደዋል!? እናም እያንገሸገሸው ለአንቀጽ 39 አጨበጨበ፡፡ ይህ ህዝብ ተቃዋሚን መርጦ ለኢህአዴግ አሸናፊነት አጨብጭቧል፡፡ በስፖርት መድረክ ማለትም አትሌቶቻችን ሜዳሊያ ሲያጠልቁ፣ የእግር ኳስ ቡድናችን እያሰለሰለም ቢሆን ሲያሸንፍ ካልሆነ በስተቀር፣ በእኔ እድሜ ህዝብ ተደስቶ ሲያጨበጭብ ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ገዢዎቹን ለማስደሰት ሲያጨበጭብ ግን እስኪሰለቸኝ ተመልክቻለሁ፡፡

ይህ ህዝባዊ አጨብጫቢነት መሰረቱ የየዘመኑ ነገስታት ጭካኔ ነው፡፡ የአለምን ነገስታት ታሪክ ስናጠና አንባገነኖች ለፍርድ ቀርበው ስለፈፀሙት ግፍና መከራ ተቀጥተዋል፡፡ የተወሰኑት በፍትህ አደባባይ ላለመቅረብ ድንበር ተሻግረው፣ ራሳቸውን ቀይረው፣ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ ተደብቀው ኖረዋል፡፡ ከዚህ የከፉት ነገስታት ደግሞ ለፈፀሙት ግፍና በደል ህዝብን እያስጨበጨቡ የፈፀሙትን ጭካኔ ገድል አድርገው፣ ድርሳን እያፃፉና ሀውልት እያስቀረጹ ኖረዋል፡፡ እነዚህ መሪዎች ስለገደሉት፣ ስላሰሩት፣ ስላሰደዱት ዜጋ ህዝብን እያስጨበጨቡ፣ ህዝቡን የግፋቸው ተካፋይ ያደርጉታል፡፡ የመሪዎቹን ጭካኔ ወሰን የለሽነት ከራሳቸው በላይ ያውቀዋልና ህዝቡ ያጨበጭባል፡፡

ህዝባዊ አጨብጫቢነት ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ትርፍ የለውም፤ ለመሪዎችም ሆነ ለህዝብ፡፡ ለመሪዎች እንዲህ አይነቱ ጭብጨባ የለሊት እንቅልፍ እንጂ የዘላለም እድሜ አያጐናጽፋቸውም፡፡ የአስተዳደራቸውን ህጸጽ ሸፍኖ እፎይታ ይሰጣቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚመሩት ህዝብ የእጁን ጭብጨባ እንጂ የልቡን መሻት አልተረዱምና ስህተታቸውን እያረሙ ለዘላቂ ይሁንታ አይበቁም፡፡ በሌላ በኩል ህዝቡም ቢሆን ለጊዜው ከመሪዎች ዱላ በማጨብጨቡ ያለመጣል እንጂ ዘላቂ ፍትሃዊ አስተዳደር አያገኝም፤ ዱላው ይከብድበታል እንጂ አይቀልለትም፡፡ ችግሮቹ ይደራረባሉ እንጂ ለመፍትሄ አይበቁም፡፡ በአንባገነንነታቸው የተነሳ ከህዝቡ ገንቢ ግብአት የተነፈጋቸው መንግስታት ወደመቃብራቸው የሚወርዱት በጭብጨባ እንደታጀቡ ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት ህዝባዊ አጨብጫቢነት ጦሱ ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም፡፡ መሪዎችን በመፍራት የተጀመረ ጭብጨባ እንደማይከፈልበት ድርጐ ተቆጥሮ ሲዘወትር፣ የአኗኗራችን አካል ባህላችን ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አስፈላጊ በሆነበት ሁሉ እንጠቀምበታለን፡፡ በእኛ ሀገር አሁን እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል አንድ አመት ተኩል ያህል ረዝሞብን በመከራ ለጨረስነው ‹‹ሲኒማ›› እናጨበጭባለን፡፡ የድፍረቱን ልጓም ጐትቶ ስሜቱን ለመግታት ላቃተው ‹ገጣሚ› ልጓም ከመሆን ይልቅ እጃችን እስኪቃጠል እናጨበጭባለን፡፡ ዛሬ በየሲኒማ ቤቱ የሚታዩት አብዛኞቹ እንቶፈንቶዎችና ግጥም ተብለው በየመጽሐፉ የሚታተሙት ቅርሻቶች የዚህ ህዝባዊ አጨብጫቢነት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ህዝባዊ አጨብጫቢነት ድንቁርና በእውቀት ላይ ይሰለጥናል::


ከበድሉ ዋቅጂራ (ዶ/ር) (ፋክት መጽሄት)

59 views0 comments

Σχόλια


bottom of page