• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጸንተህ ለመቆም ከፍርሃትህ የሚበልጥ ነገር ፈልግ!


ጸንተህ ለመቆም ከፍርሃትህ የሚበልጥ ነገር ፈልግ!

ፍርሃት በሁለት መንገድ የሚከፈል ይመስለኛል። አንደኛ እራሳችን የምንፈጥረው ፍርሃት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሌሎች በውስጣችን የሚጭሩት ፍርሃት ነው። ሁለቱም ሀይለኛ ስሜቶች ናቸው። ሁለቱም ጉልበትን የማሸብረክ፤ ውሳኔን የማስቀየር፤ አላማን የማሳት፤ አሸማቆ ወደ ብቸኝነት ጉድጓድ የማስገባት ጉልበት አላቸው። እራሳችን በራሳችን የምንፈጥረውና ሌሎች በኛ ሊጭሩት የሚሞክሩት ፍርሃት የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። እንደሚከተለው እንመልከታቸው

እራሳችን በራሳችን የምንፈጥረው ፍርሃት- ይህ በእራስ ካለመተማመን የሚመነጭ ስሜት ነው። በራስ መተማመን ትርጉሙ ጥልቅ ቢሆንም እራስን መቀበል፤ አቅም እና ችሎታዎችችን ማወቅ፤ በሌሎች ሰዎች አስተያየት ሳይሆን በራስ ፍላጎት መመራት ጥቂቶቹ መመዘኛዎች ናቸው። እንግዲህ እኒህን ነገሮች ማሟላት ሲያቅተን ፍርሃት በውስጣችን ይሰርጻል። ምን አይነት ፍርሃት? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ግላዊ ነው።

ሌሎች በእኛ ላይ የሚፈጥሩት ፍርሃት- ይህ ደግሞ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በእኛ ላይ እምነት ሲያጡ የሚፈጠር ፍርሃት ነው። የመጀመሪያውን ፍርሃት ካሸነፍን ይህ አይነቱ ፍርሃት እኛን ለማስቆም አቅም አይኖረውም። ምክንያቱም እኛን እንደገዛ እራሳችን ሊያስደነብረን የሚችል ማንም ሰው ባለመኖሩ ነው። “ሰው ከራሱ የበለጠ ጠላት የለውም” የሚለው የአፍሪካውያን አባባል፤ ያለምክንያት የተተረተ አይደለም።

እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ እውነት ቢኖር፤ ሁሉም በእኛ ላይ እምነታቸውን ቢያሳድሩ እና እኛ በራሳችን ማመን ቢያቅተን ምንም ነገር ብንሞክር የመሳካት እድሉ በጣም ጠባብ ነው። በአንጻሩ እኛ በራሳችን እምነት ኖሮን ሌሎች ግን በእኛ እምነት ቢያጡ አላማችን የማይሳካበት ምንም መንገድ የለም። ከላይ እንዳሰፈርኩት ከገዛ እራሳችን በበለጠ እኛን ለማስቆም የሚቻለው ማንም ሰው ባለመኖሩ ነው።

እንግዲህ ሳይንሳዊ የሆነውን የፍርሃት ትንተና ትተን በተለያየ ደረጃ የሚገጥመንን ፍርሃት እንድንጋፈጥ የሚረዳን አንድ መፍትሄ አለ። ይህም ከፍርሀታችን የበለጠ ነገር መፈለግ! አላማችን ከፍርሃታችን ከበለጠ፤ ህልማችን ከፍርሃታችን ጥላ ከገዘፈ፤ እራሳችንም ሆነ ሌሎች የሚጭሩት ፍርሃት ከጉዟዋችን አይገቱንም። ስለዚህ ድንገት አዲስ ነገር ለመጀመር አስበን ፍርሃት ከተሰማን ይህንን ጥያቄ እራሳችንን እንጠይቅ፤ ከፍላጎታችን እና ከፍርሃታችን የቱ ይበልጣል?

ሁሌም ከፍርሃትህ የገዘፈ ህልም ይኑርህ!!!

(በሚስጥረ አደራው)

37 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean