top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ስትሮክ - Stroke



ስትሮክ (አስፈሪው ገዳይ በሽታ) ልጆች አባታቸውን እና እናታቸውን አጥተዋል። እናት ልጇን ቀብራለች። በሰርግ መሃል ድንገት ወድቀው ፓራላይዝድ የሆኑ አሉ። እየተዝናኑ ድንገት ወድቀው የሞቱ አሉ። ብዙዎች ድንገት ወድቀው በዛው ሞተዋል። ሌሎች ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ተዳርገዋል። እጅግ አሰሳቢ የሆነውን እና ብዙ ወዳጆችን እያሳጣን ያለውን "የስትሮክ በሽታ" ለግንዛቤ እናካፍላችሁ ...እባክዎ ለወዳጅዎም ሼር ያርጉና ይህን ገዳይ በሽታ ወዳጅዎ አውቆ እንደ እርሶ እንዲጠነቀቅ ያድርጉ !

ስለ ስትሮክ በሽታ አስከፊነት ለማወቅ መረጃዎችን ሳገላብጥ የመላኩ ብርሃኑ አሳዛኝ ፅሁፍን አገኘሁ ... እጅግ አዝኜ አነበብኩት ... እነሆ ለእናንተም ይጠቅማልና ላካፍላችሁ :- ስትሮክ የዕለት ከዕለት ችግራችን እየሆነና የሁላችንንም ጓዳ እያንኳኳ በመሆኑ መረጃው ይጠቅመናል ብዬ አስባለሁ ... ምናልባት በዚህ መረጃ የአንድ ሰው ህይወት ታተርፉ ይሆናል። እኔ በበኩሌ ከ8 አመት በፊት ይህ መረጃ ቢኖረኝ ኖሮ ምናልባት ወንድሜን ከሞት የማትረፍ እድል ይኖረኝ ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው ....እሁድ ቀን ጠዋት ነው ... ወደ ጓደኛዬ ኒካ ስነስርአት ለመሄድ ስነሳ ወንድሜ ቀድሞኝ ከቤት ወጥቶ ስለነበር ከቤታችን ደጃፍ የሚገኝ አስፋልት መንገድ ዳር ላይ ተቀምጦ አይቼው ነበር። ከአይኑ እስክጠፋ ቁጭ ባለበት ቦታ ሆኖ ያየኝ እንደነበር ያወቅኩት ርቄ ሄጄ ዘወር ስል ወደኔ አቅጣጫ ያይ እንደነበር በመታዘቤ ነው።

ከሁለት ሰአታት በኋላ ፑል በመጫወት ላይ እንዳለ ተዝለፍልፎ ወደቀ ተብሎ ተደወለልኝ። ስደርስ ቤተዛታ ሆስፒታል ገብቶ ስትሬቸር ላይ ተኝቶ አገኘሁት። ሃኪሞች ከሻይ እስኪመለሱ እርዳታ አላገኘም። ቀስ በቀስ ራሱን ሙሉ በሙሉ ሳተ። ችግሩ ምን እንደሆነ አላወቅንም የነገረንም ሃኪም የለም። በመጨረሻ ቤተዛታ ከአቅሜ በላይ ነው አልችልም አለ …ጥቁር አንበሳ በበኩሉ አልጋ የለኝም ሲል …እኛም ለጭንቅላት ምርመራ የታዘዘልንን IRI ፍለጋ ስንንከራተት ሰአቱ ገፋ። መጨረሻ ላይ ሀያት ሆስፒታል አልጋ ተገኝቶ የፅኑ ህሙማን ጥብቅ ክትትል ክፍል (ICU) ገባ። በዚያው ሁኔታ ሳለ በሶስተኛው ቀን ህይወቱ አለፈ ... ገና በ22 አመቱ ነበር። ለቤታችን ታላቅ ሃዘን ሆነ። ዛሬ ድረስ ሁኔታውን ሳስበው እንባዬን ማቆም አልችልም ... እጅግ የምወደውን ወንድሜን የነጠቀኝ ስትሮክ ነው። ከዚያ ጊዜ በኋላ የቅርብ ዘመዶቼን ጨምሮ የማውቃቸው ብዙ ሰዎች በስትሮክ ተጠቅተው አይቻለሁ። ብዙዎቹ ሞተዋል። ብዙዎቹ ፓራላይዝ ሆነዋል። በዚህ ሁለት ወር ብቻ የማውቃቸው ሶስት ሰዎች በስትሮክ ሞተዋል። ስትሮክ ወደአንጎል የሚሄደው ደም ስር በረጋ ደም በሚዘጋበት ጊዜ የደም ዝውውር ሲቋረጥ የሚከሰት የደም ወደ አንጎል መፍሰስ የሚያስከትለው ከባድ የጤና አደጋ ነው።

  • ከባድ የደም ግፊት

  • የልብ እና

  • ኩላሊት በሽታ

ለስትሮክ መከሰት ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ሃኪሞች ይናገራሉ። ብዙዎቻችንስለማናስተውለው እንጂ የምንሰማው የዘመድ ወዳጆቻችን ድንገተኛ ሞትና ራስ መሳት ከስትሮክ ጋር ቁርኝት አለው።ይህ አደጋ ድንገት ባልታሰበ ሰአት ይከሰታል።

  • ተኝተን

  • እየሰራን

  • እየበላን

  • እየተጫወትን

  • መንገድ ላይ ሆነን ሊከሰትብን ይችላል።

በስትሮክ የተመታ ሰው ለብዙ ጉዳቶች ሊዳረግ ይችላል ...ለምሳሌ :-

1. አንዳንዶችን በሙሉ ወይም በከፊል ፓራላይዝ ያደርጋል።

2. አንዳንዶቹን የአእምሮ ማስታወስ ችሎታቸውን በሙሉ ወይም በከፊል ይነጥቃቸውና ሚስትና ልጆቻቸውን ጭምር እንዲረሱ ያደርጋቸዋል።

3. የከፋ ጊዜ ልክ ኮምፒውተር ፎርማት እንደሚደረገው ሁሉ ስትሮክ ያጠቃቸውን ሰዎችም አዕምሯቸው ምንም ሳያስቀር ሙሉ በሙሉ የመርሳት ችግር ይጋርጥባቸዋል።

4. አንዳንዶቹ ላይ ደሞ ራስን ስቶ ሽንትና ሰገራ ለመቆጣጠር እስካለመቻል ምግብ እስካለመቀበልና በመጨረሻም እስከሞት ያደርሳቸዋል።

5. የስትሮክ የከፋው ጠባይ የያዘውን ሰው አንዳንዴ ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች አድርጎ ማስቀረቱ ነው።

6. እናት ለታመመ ልጇ ሞትን እስክትመኝ የታመመ ሰው በጠያቂ "አሁንስ በገላገለው " እስከሚባል ድረስ ተስፋ ያስቆርጣል።

7. የጭንቅላት ቀዶ ሃኪሞች አንዳንዴ ከተሳካላቸው በአንጎል ውስጥ የፈሰሰ ደምን በመጥረግ ህይወት ያተርፋሉ ወይም ጉዳት ይቀንሳሉ።

8. በኛ አገር ደረጃ በከባድ ስትሮክ ተመትቶ ሙሉ በሙሉ የመዳን ብቻ ሳይሆን ከሞት የመትረፍ እድል ራሱ አናሳ ነው። እግዚአብሄር ተጨማሪ የመኖር እድል የሰጠው ሰው ከሳምንታት ወይም ወራት ራስን መሳት በኋላ ሙሉ በሙሉ ተርፎ በተአምር ከሞት ወደህይወት ይመለሳል::

9. የአንዳንዱን ህይወት ደግሞ እስከእድሜ መጨረሻው ድረስ አበላሽቶ ያስቀረዋል።

በአጠቃላይ ስትሮክ መቼና እንዴት እንደሚከሰት ስለማይታወቅ ሰይጣን በሽታ በሉት። ሹክክ ብሎ መጥቶ ውድ ህይወታችንን ይነጥቀናል ...ወይም ከነበርንበት ሙሉነት ወደከባድ ጎዶሎነት ይቀይረናል።

ስትሮክን በተመለከተ ያለው መልካም ዜና አንድ ብቻ ነው። ምልክቱን አውቀን ከቀደምነው የሞት በትሩን የማስጣል እድል አለን ። በጣም ቀላል በሆኑ ዘዴዎች አንድ ሰው በስትሮክ ስለመመታቱ ማረጋገጥና በፍጥነት ወደሀኪም ወስደን ህይወቱን ማትረፍ እንችላለን። በርግጥ እግዜአብሔር ይጠብቅ ነው እንጂ በኛ ሃገር ሃኪሞችና ሆስፒታል ሁኔታ ብዙ ተስፋ ማድረግ አይቻል ይሆናል። በወንድሜ ሞት ያረጋገጥኩት ይህንኑ ነው ... ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚያረጋግጡት የስትሮክ ምልክት የታየበት ሰው በ3ሰአታት ጊዜ ውስጥ ሃኪም ጋር ከደረሰ ሙሉ በሙሉ ለመዳን እድል አለው።

ዋናው ጥያቄ አንድ ሰው በስትሮክ ሲመታ የሚያሳያቸው ምልክቶች ምንድናቸው ? .... እንዴትስ ማወቅ ይቻላል? የሚለው ነው። አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹን ለመለየት ከባድ ቢሆንም STROKE አንድን ሰው እንዳጠቃው ለማወቅ የምንረዳባቸውን ቀላል ዘዴዎች አሉ። ቀዳሚው ዘዴ የስትሮክን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ፊደላት በቃል ይዞ በአዕምሮ መመዝገብ ነው።" STR " ፊደሎቹ ናቸው ::

1. S = smile ... በስትሮክ የተመታ ሰው ፈገግ ማለት ያዳግተዋል ... ፊቱ ስሜት አልባ ይሆናል ... አንድ ጊዜ ፈገግ እንዲል መጠየቅና ውጤቱን ማየት።

2. T =talk ስትሮክ አንደበት ስለሚይዝ የሚወጡ ቃላት እንዲንተባተቡና ትርጉመ ቢስ እንዲሆኑ ያደርጋል። ቀላል አረፍተነገርን ሳያቆራርጥ እንዲናገር መጠየቅ (ምሳሌ:- ቴሌቪዥኑን ስንት ትሸጠዋለህ? እንዲል ) ውጤቱንም ማጤን

3. R=raise hands ስትሮክ እጅና እግር እንዳይታዘዝ ያደርጋል። ሁለት እጆቹን ወደላይ እንዲያነሳ መጠየቅና ውጤቱን ማየት ከነዚህ አንዱን በትክክል መወጣት ከተሳነው የስትሮክ ምልክት ነውና ሃኪም ጋር በፍጥነት መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል።

4. በተጨማሪም ምላሱን ቀጥ አድርጎ እንዲያወጣ መጠየቅ ማውጣት ከተሳነው ወይም አጥፎና አጣሞ ካወጣው በስትሮክ የመመታት ምልክት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል ። (ከመላኩ ብርሃኑ ፅሁፍ የተገኘ)

ከላይ ያለውን አሳዛኝ ታሪክ እንደ መረጃ አይቼ ሳበቃ ይበልጥ ለፍም ሃሳብ Tube ተከታታዮች ተጨማሪ መረጃ ይሆናል ብዬ ሌላ መረጃ ሳፈላልግ ይህን ጠቃሚ ፅሁፍ አገኘሁ ... እስኪ የወዳጆቻችንን እና የራሳችንን ህይወት ለመታደግ ይረዳን ዘንድ ይህን መረጃልጨምርላችሁ ...መረጃውን ከሚኪያስ ተፈራ ፅሁፍ እንዳለ ወስጄዋለሁ። እንዲህ ይላል ፅሁፉ ... አብዛኛውን የ”ስትሮክ” በሽታ መንስዔ መከላከል ይቻላል። በካናዳ ማክማስተር ዩኒቪርስቲ የስነ-ህዝብና ጤና ተቋም ከሰሞኑ በመካከላኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ከፍተኛውን የሞትና የአካል ጉድለት በሚዳርገው “ስቶሮክ” በሽታ ላይ ያደረገው የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡ በአለማችን ከፍተኛ ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው 26 ሺህ ሰዎች ላይ የተካሄደው ጥናት 90 በመቶ የሚሆነውን የ”ስትሮክ” በሽታ መከላከል እንደሚቻል ያመለክታል፡፡ በአመዛኙ በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚታየው “ስትሮክ” በድንገተኛ የአዕምሮ ደም ዝውውር መቋረጥ የሚከሰት ሲሆን በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡

1. የ”ስትሮክ” በሽታ በሁለት ክፍሎች ይከፈላል ... የመጀመሪያው “ischaemic stroke” እስካሚክ “ስትሮክ” በመባል የሚታወቀው ሲሆን 85 በመቶ የስትሮክ በሽታ ድርሻን ይዛል፡፡ እስከሚክ ስትሮክ በደም መርጋት የሚከሰት የ”ስትሮክ” በሽታ አይነት ነው፡፡

2. ሁለተኛው የ”ስትሮክ” አይነት “haemorrhagic stroke” ሄሞራጂክ ስትሮክ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቀሪውን 15 በመቶ የ”ስትሮክ” በሽታ ድርሻን ይዛል፡፡

ሄረሞራጂክ ስትሮክ በአዕምሮ ደም መፍሰስ የሚከሰት የ”ስትሮክ” በሽታ አይነት መሆኑን የሳይንስ ዴይሊ ዘገባ ያስረዳል፡፡ በጥናቱ መሰረት ከታች የተጠቀሱ 10 የ”ስትሮክ” በሽታ መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ከ10 በ”ስትሮክ” በሽታ ከሚሞቱ ሰዎች የ9ኙን ህይወት ማትረፍ ይቻላል፡፡

1. የደም ግፊት በሽታን በመከላከል 48 %

2. የአካል ብቃት አንቅስቃሴን አዘውትሮ በመስራት 36 %

3. አመጋገብን በማስተካከል 19 %

4. ሲጋራን በማቆም 12 %

5. የልብ በሽታን በመከላከል 9 %

6. የስኳር በሽታን በመከላከል 4 %

7. የአልኮል መጠጥን በማቆም 6 %

8. አለአስፈላጊ ጭንቀትን በማስወገድ 6 %

9. ኮልስተሮል ያለባቸውን ምግቦች በማቆም 27 %

10. ከላይ የተጠቀሱ የ”ስትሮክ” በሽታ መከላከያ መንገዶች በጥቅሉ 91 በመቶ የስትሮክ በሽታን መከላከል ይቻላል፡፡ (ከሚኪያስ ተፈራ ፅሁፍ የተወሰደ)

ሲጠቃለል ...ብዙዎችን ድንገት እየቀጠፈ ... ልጅን ያለ እናት እና አባት እያስቀረ ፣ ልጆቻችንን ድንገት በሞት እየነጠቀ እና ወዳጆቻችንን እየገደለብን ያለውን ስትሮክ በሽታ በመጠኑ አስቃኘናችሁ ... እባክዎ አንብበው ለወዳጆ ያካፍሉ ... መረጃ ምንግዜም ቢንያስ የአንድ ሰው ህይወት ያድናልና !

© ናቲ ቪሎፒያ (ጋዜፀሃዲዛ)


97 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page