top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ባለመጠበቅ እራስህን ጠብቅየሰው ልጅ ህይወት በየትኛውም ሁኔታ ላይ በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ ያለተስፋ የሚኖሩት ህይወት ካለመኖር አይተናነስም፡፡ ተስፋ ጥሩ ነው በተለይም ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ ያካተተና በስራ የታገዘ ሲሆን እውን የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

በዚህ በምንኖርበት ሳዑዲ አረቢያ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የቤተሰብ ክፍያ እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጎችን በሚያሰሩ ድርጅቶች ላይ የመኖሪያ ፈቃድ ዕድሳት ክፍያ ጭማሪን የያዘው አዋጅ ከወጣ አስር ወር ሊያደርግ ቀናት ብቻ ነው የቀሩት፡፡ ይህ አዋጅ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች አዋጁ ከመተግበሩ በፊት በግንዛቢያቸው ልክ የራሳቸውን ዝግጅት እያደረጉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የኤሌክትሪክና ውሀ ፍጆታ ክፍያዎች መጨመር ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንዲሁም ከጃንዋሪ/2018 ጀምሮ ተግባር ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው የቫት ክፍያ በቀጣይ ኑሮን ያከብዳሉ ተብለው ከሚታሰቡት አስቸጋሪ ክስተቶች ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሚከሰት የገበያ መቀዛቀዝ ድርጅቶችም መጪ ጊዚያቸው ምን ሊመስል እንደሚችል የራሳቸውን ትንበያ በማድረግ የመጪ ጊዜ እቅዳቸውን ይከሰትብናል ብለው ባሰቡት የገበያ መቀነስ ልክ አስተካክለዋል፡፡ ለብዙዎች የፍጆታ ዕቃ አምራች ድርጅቶች ሸማቹ አዋጁ ከመተግበሩ በፊት ባሳየው ምላሽ ሽያጫቸው በመውረዱ አዋጁ ሲተገበር ሊኖር የሚችለውን ጫና መተንበይ ብዙም አልከበዳቸውም፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ከአዋጁ መተግበር በፊት የነበራቸው ግንዛቤ የተለያየ እንደነበር በየአካባቢው በአዋጁ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች አመላካች ነበሩ፡፡ በአብዛኛው ሀገሪቱ ከምትመራበት የሸሪዓ ህግ እና ጉዳዩ ከእስልምና አስተምሮት ጋር ያለውን ግንኙነት በማዛመድ አዋጁን ንጉሱ አዎንታዊ ምላሽ እንደማይሰጡትና እንደማይተገበር ገምተው ነበር፡፡ በጣም ጥቂት ባይባሉም አዋጁ የወጣበትን ምክንያት እንዲሁም የሳዑዲ አረቢያ መንግስት አሁን እየተከተለ ካለው የኢኮኖሚ ለውጥ ጋር በማገናዘብ የአዋጁን አይቀሬነት እርግጠኛ ሆነው ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ከትግበራው በፊትም አዋጁ ከሚፈጥርባቸው የክፍያ ጫና ለማምለጥ ቤተሰባቸውን የላኩም ነበሩ፡፡

በአብዛኛው የኛ ማለትም ኢትዮጵያዊው ህብረተሰብ ከትግበራው በፊት አዋጁ ይፈፀማል የሚል እምነት አልነበረውም፡፡ የአዋጁ ትግበራ የዛሬ ሶስት ወር ከአስራ አምስት ቀን አካባቢ ሲጀመር ነበር ባለው ቤተሰብ ልክ ለክፍያ መዳረጉን የተረዳው፡፡ በተለይም አዋጁ መተግበር በጀመረበት አንድና ሁለት ሳምንት ውስጥ ከመኖሪ ፈቃድ እድሳት ጋር ተያይዞ አተገባበሩ ምን እንደሚመስል በተረዳ ጊዜ ጫናው የከፋ መሆኑን የተገነዘበው፡፡ በነዚህ ጊዚያት ውስጥ ቤተሰቡን ወደ ሀገር አስጠቅልሎ የላከው እና በሀገር ላይ የትምህርት ቤት ምዝገባ ሳያመልጠው ለመላክ የሚጣደፈው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በአብዛኛው በደህናው ጊዜ በሀገር ላይ ለመኖር ቅድመ ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ አለያም ያጋመሱ ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ አዲሱ አዋጅ የሚያመጣባቸው ወጪና ከቤተሰብ ጋር እዚህ ለመኖር የሚያወጡት ወጪ ሲደማመር ቤተሰብን ሀገር ልኮ ለትንሽ ጊዜ እዚህ መስራት ያዋጣል በሚል ድምዳሜ ቤተሰባቸውን ያሰናበቱ ናቸው፡፡ ሌሎች ግን ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ቢያንስ ይህንን አመት ክፍያውን ከፍለው ከቤተሰብ ጋር ለመኖር ወስነው አብረው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ አይነት ውሳኔ እዚህ የቀረው የህብረተሰብ ክፍል 95% ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

የዚህ ፅሁፍ የትኩረት አቅጣጫ የራሱን ውሳኔ ወስኖ ሀገር የገባው የህብረተሰባችን ክፍል ሳይሆን ይህንን አመት ትንፋሽ ላግኝበት ብሎ እዚህ የቀረው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ብዙም ሙያዊ (Professional) ባልሆነ የስራ መስክ (የጉልበት ስራ) ላይ የተሰማራ ሲሆን ገቢውም አነስተኛ ነው፡፡ ቀሪው ደግሞ በራሱ የንግድና የትራንስፖርት ስራ ላይ ተሰማርቶ ያለና ስራውን ሰርቶ ለመኖር የሚያስችሉትን መደበኛ የመኖርያ ፈቃድ ዕድሳት ፣ የንግድ ፈቃድና ከንግድ ፈቃድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ክፍያዎች እንዲሁም የንግድ ቤቱን ወይም የትራንስፖርት መኪናውን በስሙ ለገዛው አሰሪ ወይም ድርጅት የሚከፍላቸውን ክፍያዎች ያካትታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደማንኛውም የውጭ ዜጋ ከላይ የጠቀስነው የቤተሰብ ክፍያንም የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ቪዥን 2030 የሚል ራዕይ በመያዝ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን አቅዶ ለመተግበር በከፍተኛ እንቀስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በሀገሪቱ ላይ እያደገ ያለውን የዜጎችን ስራ አጥነት በዕጅጉ መቀነስ ሌላው እቅድ አውጥቶ እየሰራበት ያለ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለዜጋው ይሆናሉ ተብለው ከታሰቡት መስኮች አንዱ በብዛት በውጭ ዜጎች ተይዞ የሚገኘው የችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ነው፡፡ በቅርቡ በእያንዳንዱ የችርቻሮ ሱቅ ውስጥ የሳዑዲ ዜጋ ብቻ ተቀጥሮ እንዲሰራ የሚያዝ ህግ ተግባራዊ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ይህ ሲተገበር ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በንግድ ዘርፍ ተሰማርቶ ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስራ አጥ ከመሆኑም በላይ ደክሞ ያሳደገውን ንግድ ቤት ያለምንም ጥቅም አለያም በወረደ ዋጋ ትቶት እንዲወጣ ይገደዳል፡፡

በትራንሰፖርት ዘርፍ ላይም ተሰማርቶ ያለው የውጪ ዜጋ ዕጣ ፈንታ ብዙም አስደሳች አይደለም፡፡ የሀገሪቱ መንግስት ለዜጎቹ የትንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖችን በብድር በማቅረብ ስራውን እንዲቆጣጠሩት ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ የፀደቀውና በቀጣይ ጁን/2018 ይተገበራል ተብሎ የሚታሰበው የሴቶች መኪና መንዳት ፈቃድም በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ የውጪ ዜጎች ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን ይገመታል፡፡

በምድር ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው እንዲህ አይነት አደጋዎች እንደሆነ እየተረዳን በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ግን አሁንም በተለያዩ ተስፋዎች በመሸበብ ወደፊት ከአሁን የተሻለ እንደሚሆን ይገምታል፡፡ የዚህ ግምት መነሻ ሀሳብ ደግሞ የሳዑዲ መንግስት አሁን እየተገበረ ያለውን የቤተሰብ ክፍያ ህግ በተለያዩ ጫናዎች ያስቀረዋል አለያም በቤተሰብ አባል የሚከፈለውን ክፍያ በወር በነፍስ ወከፍ 100.00 ሳ.ሪ ሆኖ እንዲቀር ያደርጋል የሚሉ አሉባልታዎች ናቸው፡፡ ወደፈት ጥሩ እንደማይሆን የተረዳውም የህብረተሰባችን ክፍልም ቢሆን መጪውን ጨለማ ፈርቶ በራስ ተነቃንቆና በአቅሙ ልክ አቅዶ ከጨለማው ከማምለጥ ይልቅ በሰው ሀገር ያፈራወን ሀብትና ንብረት ወደ ሀገር ይዞ የሚገባበት የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚነት ወይም በረዥም ጊዜ ክፍያ በሚጠናቀቅ የክፍያ ስርዓት ቀረጡን የሚከፍልበትን ሁኔታ ከመንግስት በኩል እንዲመቻችለት ይጠብቃል፡፡

ጎበዝ የናንተን አላውቅም እኔ ግን መጪው ጨለማ ካሁኑ የከፋ እንደሚሆን ይታየኛል፡፡ አሁን እንደበፊቱ ባይሆንም ህዝባችን በተጨማሪ ሰዓት ወይም በዋናው የጨዋታ ወቅት ባክኖ ለማካካሻ የተሰጠ የማሰቢያ ጊዜ አለው፡፡ ይህን ጊዜ ከማንም ምንም ሳንጠብቅ የራሳችንን አቅም ብንችል ለብቻችን አለያም የየግል አቅማችንን አስተባብረን ከመጪው የከፋ ጭለማ ቀድመን ብናመልጥ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ በአዋጁ ዙሪያ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በጎ ለውጥ ያመጣል ብሎ ተስፋ ባለማድረግ ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ከሳዑዲ ለሚፈናቀሉ ዜጎቹ ብቻ የተለየ ህግ አውጥቶ ይደግፈናል ብሎ ተስፋ ባለማድረግ ከወዲሁ መጪው ጭለማ ሳይመጣ የማንንም ዕገዛ ሳንጠብቅ የራሳችንን ውሳኔ ብንወስን ከሚመጣው ጭንቀት እፎይ እንላለን፡፡ እንደመጠበቅ አክስቶና ተስፋ አስቆርጦ ገዳይ የለም፡፡ አለበለዚያ ግን የስራ አለመኖር ፣ የመኖሪያ ፈቃድ እድሳትና ተያያዥነት ያላቸው ወጪዎች ቤተሰብን ማስተዳደር ፣ የልጆች ት/ቤት እንዲሁም ሌሎች ያልጠቀስኳቸው ሀሳቦች ሲደራረቡ ጤናን የሚፈታተን ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ ስለሆነም ዛሬ አለን የምንለውን ንብረት ላይ ለመወሰን የሌላን እገዛ ስንጠብቅ እሱኑ ተነጥቀን ወይም ሸጠን በልተን ባዶ እጃችንን እንዳናጨበጭብ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ አካላት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ኤምባሲ ፣ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ት/ቤት ምሁራን የሚሆነውንና የማይሆነውን በማመላከት የዜግነት ግዴታችንን ከመወጣት ባሻገር ወገናችንን ከማይመስል ተስፋ እናላቀው፡፡

ሰውየው ኑሮ እንዴት ነው ቢሉት ከወደፊቱ ይሻላል አለ አሉ፡፡ የወደፊቱ ችግር ካሁኑ የፀና እንደሚሆን እንገምት፡፡

ከማንም ምንም ባለመጠበቅ ከወዲሁ እራሳችንን እንጠብቅ!

ከአያልቅበት ኃይለማርያም


12 views0 comments
bottom of page