top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የመስቃን ቤተ ጉራጌ ታሪካዊ አመጣጥ



የመስቃን ቤተ ጉራጌ ታሪካዊ አመጣጥ

በመጀመሪያ ስለ መስቃን ህዘብ ታሪካዊ አመጣጥ ከመመልከታችን በፊት ስለ ህዝቡ አሰፋፈርና ስለ አካባቢው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ማወቅ አስፈላጊ ነው። የመስቃን ህዝብ በጉራጌ ዞን ከሚገኙ አስራ አንድ ወረዳዎች መካከል አንዱ በሆነው በመስቃን ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሚዋሰነውም በሰሜን ሶዶ በደቡብ ስልጤ በምእራብ ሰባት ቤት ጉራጌና በምስራቅ ከማረቆ ጋር ነው። የመስቃን ህዝብ ካለው የህዘብ ብዛትና ከሰፈረበት ይዞታ አኳያ የወረዳው መጠሪያ ስም ለመሆን የቻለ ሲሆን ህዝቡ ተራራማ ከሆነው የመስቃን ደጋና ወይና ደጋ ክፍል አንስቶ የወረዳው ርእሰ ከተማ የሆነችው ቡታጅራን ጨምሮ እስከ ቆላማው የወረዳው ድንበር ድረስ ሰፍሮ ይገኛል። በተጨማሪም የመስቃን ቤተ ጉራጌ አባላት በአጎራባች ወረዳዎችና በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በከንባታ አለባ ጠንባሮ በሲዳማና በጌዲኦ ዞኖች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በመቂ አከባቢና በሃገሪቷ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ውስት ተሰራጭተው ኑሮአቸውን መስርተው የገኛሉ።

የመስቃን ቤተ ጉራጌ አመጣጥ

የመስቃን ህዝብ ታሪካዊ አመጣጥን በተመለከተ እስከዛሬ ድረስ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሃገር የታሪክ ምሁራን በኩል የተካሄደ ጥናት ካለመኖሩ ባሻገር የጉራጌን ህዝብ ታሪክ ለመጻፍ የተነሱ የታሪክ ምሁራን ባሰባሰቧቸው የታሪክ መዘክሮች የጻፉት ነገር ቢኖር በጣም አናሳ በሆነ ሁኔታ የጉራጌ ብሄረሰብ አካል መሆኑንና የጉራጌ ብሄረሰብ የዘር ግንድ ከሆኑት ሰዎች ጋር ወደ ዛሬው የጉራጌ ምድር መምጣታቸውን የሚጠቁም መጠነኛ ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን።

በዚህ ምክንያት የህዘቡን ማንነት የሚገልጽ ጥናት ባለመካሄዱ በተጨማሪም ወደ ሰነድነት የተሸጋገረ የቆየ ታሪኩን የሚዘግብ ጽሁፍ ባለመኖሩ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ስለህዝቡ ታሪክ ባህልና ገድል በቂ ግንዛቤ ለመጨበጥ የተቸገረ መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ሆኖም ባንድ ታሪክ ወቅት የሚገኝ ህብረተሰብ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ይሁን እንጂ የትኛውም ህዝብ የራሱ የሆነ ታሪክ ባህልና ቋንቋ ያለው ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይሆንም ።

በመሆኑም ከዚህ መሰረታዊ ጉዳይ በመነሳት የመስቃን ህዝብ የማንነት መግለጫ የሆነው ታሪኩና ባህሉን ለማጥናት ከላይ በተገለጸው ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም ባሁኑ ጊዜ በህይወት ያሉ የማህበረሰቡ ተወላጆ የሆኑ አዛውንቶች ባፈ ታሪከ የሚናገሩትን መረጃ በማሰባሰብና አንዳንድ መጽሃፍቶች ስለ መስቃን ህዘብ ከሚሰጡት መጠነኛ ፍንጭ ጋር በተገናዘበ መልኩ የተሟላ ባይሆንም መጠነኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የመስቃን ህዝብ የረጅም ዘመን ታሪክን ከዚህ ቀጥሎ ለማየት እንሞክራለን። በመጀመሪያ ደረጃ የመስቃን ህዝብ መስቃን የሚለው መጠሪያ ስያሜ ያገኘው በመካከለኛው ዘመን መባቻ ላይ ቢዳራ በሚባለው ቀበሌ ተገንብቶ የነበረውና በሗላም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባህመድ ግራኝ የፈረሰው መስቀለ እየሱስ ከሚባለው ቤተክርስቲያን ስም የተወሰደ ለመሆኑ የመስክ ጉብኝት በተደረገበት ወቅት ለጥናቱ ተባባሪ የሆኑ አዛውንቶች ገልጸዋል። በተጨማሪም ስሙንት(ስምንት) ሰንጋ መስቃን በመባል የሚታወቁት አከባቢዎች ደግሞ የጠቀር፣ ሚካኢሎ፣ ውሪብ፣ አቦራት፣ እም (እናት) መስቃን ፣ እምቦር (ፈረዝአገኝ) ፣ የተቦን እና ጎይባን ናቸው። ወደ ተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ ስንመለስ የዛሬው የመስቃን ህዝብ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በስሩ 62 (ስልሳ ሁለት) ጎሳዎችን ያቀፈ ነው። የእነዚህ ጎሳዎች ታሪካዊ አመጣጥን ስንመለከት በተለያየ ወቅት ከተለያ አቅጣጫ በተለያ ምክንያት የመጡ ሲሆን ከነባርና ቀድመው ከመጡ ጎሳዎች ጋር በስምምነትና በግጭት እየተቀለቀሉ እየተዋሃዱ በረጅም ጊዜ የታሪክ ሂደት የዛሬውን የመስቃን ቤተ ጉራጌ በመባል የሚታወቀውን ህዝብ ለመመስረት ችሏል።

​​​​​​1. እናት መስቃን

  • ቦንጂ

  • አልወድሽ

  • ማሬኖ

  • ወሬቦ

  • ድላባ

  • ሊላቶ

  • ሰጦ

  • ፋጌ

  • ተራሞ

  • በጋሞ

  • ሰቡቴ

  • አውራሪ

  • ጅገና​​​

​2. እምቦር

  • ​​ስናኖ

  • ​ኦዳ

  • ​ኢንዴ

  • ቃሶ

  • ኤሉ

​3. ዲራማ

  • ​ሞንኢሎ

​​4. ፈረዝአገኝ

  • ሱሚየ

  • ንቡወ

  • ጋሎ

​5. ግዴይ

  • ዋተራ

  • ገሬኖ

  • ጃርሶ

6. ውሪብ

  • ቸሮ

  • ሱነከሌ

  • ቦሰኖ

  • ጎዳና

  • ገሬኖ

  • ጃርሶ

7. ሚካኢሎ

  • ሚካኢሎ

8. የጠቀር

  • አረቢዳስ

  • ጃተኒ

  • ቅምቦት

  • ወጎ

  • ከሳዬ

9. የተቦን

  • ዳረጎት

  • አስፎ

  • ገድፍ

  • አማኖ

  • ወሶ

  • ግድርወ

  • ራያ

  • ዋቆ

  • ኤቤኝ

  • መንደል

  • ጅርመከር

10. ጐይባን

  • ሸዋ

  • ጨዋ

  • አትርዱ

  • ወይንጉስ

  • ወልዶ

  • ሁልየ

  • አርቦ

  • ደዋዲን

  • ዳሞ

  • ሼህ መረዲን(ማሬኖ)

  • ባሮ

  • ጉምባር

ከዚህ አኳያ የዛሬው የመስቃን ህዝብ ታሪካዊ አመጣጥን ለማወቅ በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶችና ጊዜያቶች ከፍለን መመልከት የበለጠ ግንዘቤን ስለሚያስጨብጥ ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር ለመመልከት እንሞከራለን። ሀ) በሰሜኑ ማእከላዊ መንግስት የግዛት መስፋፋት ፖሊሲ ምክንያት በአጼ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት (1314 –1344) በመጀመሪያ ደረጃ በዛሬው መስቃን ምድር ላይ የሚታዩ ትክል ድንጋዮች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህም የትክል ድንጋዮች መጀመሪአ ባካባቢው ሰው ኖር እንደነበር የሚጠቁም የታሪከ አሻራ ነው። ከዚህ አኳያ "ኢትዮጵያ ህዝብ ረጅም የህዝብና የመንግስት ታሪክ" በሚለው መጽሃፍ ስለ ደቡብ ነባር ህዝቦች ሲጽፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ያሉ የዋሻ ድንጋይ ላይ ስዕሎች የቀረጹ የትክል ድንጋዮች የሰሩና የተከሉ ፣ የመቃብር ላይ ሃውልቶች ያነፁ የጥንታዊ ህዝቦች መንነትና ታሪካዊ አመጣጥ በሚመለከት በዘመነ ክርስትና ከስምንተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቀይ ባህር ከዳህለክ ደሴትና ከጠረፍ ወደቦች ጀበርቲ በመባል የሚታወቁ የአረብ ነጋዴዎችና የሃይማኖት ሰባኪዎች በምስራቅ አፍሪካ እስኪገኙ ድረስ ከትሮሎጅሎድ ከበርበራና ከአዛኒያ የጠረፍ አገሮች እና ሀዝቦች ውጪ ጥንተዊ የግሪክ የሮማውያንና የአረብ የታሪክ ፀሃፊዎች ስለ ምስራቅ ደቡብና መሃል ኢትዮጵያ ነባር ሃገሮችና ህዝቦች የፃፉት ነገር እስከ ዛሬ አለመገኘቱን አስምሮበታል።

ከዚህ አኳያ በዚህ ስፈራ ነበሩ ህዝቦች የኢነርያንና የሲዳማ ህዝቦች እንደሆኑና የጉራግ ህዝብ ከምስራቅ አቅጣጫ መጥቶ ከእነዚህ ነባር ህዝቦች ጋር እንደተዋሃደ በርካታ የታሪክ ምሁራኖች የሚስማሙበት ቢሆንም የጉራጌን ህዝብ ታሪክ በጥልቀት ስንመረምረው ደግሞ እውነታው ከዚህ ሌት እንደሚል በመጀመሪያው ምእራፍ ላይ ለማየት ተሞክሯል ። በመሆኑም በመስቃን ምድር ከጥንት ጀምሮ ነባር የሆኑ ህዝቦች እንዳሉ ግልፅ ቢሆንም እስከ አስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት ታሪካዊ ማንነት በተመለከተ ካለው የመረጃ እጥረት አኳያ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም የዚህ ህዝብ ታሪክ በግልፅ ከሚታወቅበት ዘመን ጀምሮ ያለውን ለመመልከት እንሞክራለን ።

ከዚህ መሰረተ ሃሳብ በመነሳት "ባጼ አምደ ፂዮን ዘመነ መንግስት ባዝማች የሚመራ የኢትዮጵያ ሰራዊት ቡድን ባካለ ጉዛይ አውራጃ ትግረ ውስጥ ጉርአ ከሚባል ስፍራ ተነስቶ በዛሬው ሰሜን ጉራጌ አይመለል በሚባለው ቦታ ላይ ሰፈረ" በማለት ዊሊያም ሻክ።

ከዚህ በሗላ ያዝማች ሰብሃት ሰራዊት ከአይመለል ተነስቶ ወደ ጨቦ ፣ አመቦ፣ ጭላሎና ኦሞ ወንዝ ድረስ በቡድን በቡድን ተከፋፍሎ በመያዝ የራሳቸው ግዛት አደረጉ ። ከዚህ አኳያ በጉራጌ አካባቢ አንድ ቡድን መስቃን፣ አንድ ቡድን ሰባት ቤት ጉራጌ እና ሶዶ ምድር ገብተው እንደተቀመጡ ይነገራል። በመስቃን ህብረተሰብ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ጎሳዎች መካከል የመስቃን የዘር ግንድ ከሚታወቀው አንዱ ሻዶ ሲሆን የአያቱ ስም በዚያ ዘመን ከታግራይ መጥቶ እናት መስቃን በሚባል ስፍራ ተቀምጦ የሻዶን አባት ቤህሩንን መውለዱና ሻዶ ደግሞ ቦንጂ ፣ አልወድሽ እና ገራድባለከሽ የተባሉ ሶስት ልጆችን ወልደዋል ። ቦንጂና አልወድሽ ራሳቸውን የቻሉ የዘር ግንድ ለመሆን የበቁ ሲሆን ገራድ ባለከሽ ደግሞ ማሬኖ ፣ ወሬቦ ፣ ድላባ ፣ሲላቶ ፣ሰጦ እና በርኮ የተባሉ ስድስት ልጆችን በመውለድ ለዛሬዎቹ የተለያዩ የመስቃን ጎሳዎች መጠሪያ ስም ለመሆን በቅተዋል ።

በተጨማሪም በዚያ ዘመን አዝማች ስብሃትን ተከትለው ወደዚህ ስፍራ የመጡ ጎሳዎች ተራም፣በጋምና ፋጌ የመሳሰሉ ጎሳዎች ይገኙበታል። እነዚህ አዝማች ስብሃትን ተከትለው የመጡ ሰዎች አቦራት ፣በሚካኤሎ ፣በጎይባን አካባቢዎች ዝርየዎቻቸው ተሰራጭተው ይገኛሉ ።ሌላው ጐይባን አካባቢ ሸዋ የሚባል ጎሳ ከትግረ አገር ተነስቶ ሸዋ አካባቢ ከኖረ በሗላ ዘግየት ብሎ ወደ ዛሬው ጎይባን እንደመጣ ይነገራል ። የህም ጎየባን ውስጥ ሸበሬር የሚባል አካባቢ ሸዋ የሚባል ሰው ድላሞ፣ ኡራጎ፣ ዝወ፣ ማንዳኝ፣ ጦኔና አርጥቦ በመባል የሚታወቁ ስድስት ልጆችን የወለደ ሲሆን የመጨረሻዎች ሁለቱ ጦኔና አርጥቦ በአሁኑ ወቅት ዶቢ ቀበሌ አርጉሜ ስፍራ የሚገኙ ናቸው።

ሚካኤሎ ቀበሌ የሚገኝ ሚካኤሎ በመባል የሚታወቀው ጎሳ በዚያ ዘመን ከአዝማች ስብሃት ጋር አብሮ የመጣ ሲሆን ከእዣ (ቆንጫጫ) ጋር ወንድማማቾች እንደሆኑ ይነገራል።

​በተጨማሪም በዚህ ዘመን ከመጡት ውስጥ በኣቦራት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሱምየ፣ ንቡወና ጋሎ በመባል የሚታወቁ ጎሳዎች ናቸው። ንቡወ የዘር ግንዱ እዣ ውስጥ የሚገኝ ቆንጫጫ ጎሳ ጋር የዘር ትስስር እንዳለው ይነገራል።

ይቀጥላል ​...


210 views0 comments
bottom of page