የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የጥርስ መሰረታዊ እንክብካቤ እና ምክሮች

ፈገግታዎ የሚወሰነዉ ለጥርስዎ በሚያደርጉት የመቦረሽና ቆሻሻዉን የማዉጣት እንክብካቤ ልምድ ነዉ፡፡ ነገር ግን ይህን ለማድረግ እየተከተሉት ያለዉ ዘዴ ትክክል ነዉ ወይ ብለዉ መጠየቅ ያስፈልጋል?
ጥርስዎን መቦረሽ የአፍዎን ዉስጥ ጤንነት መጠበቅ የሚጀመረዉ ጥርስዎን በማፅዳት ነዉ፡፡ የጥርስዎን ንፅህና መጠበቅ የጥርስ መቦርቦርን የሚከላከል ሲሆን የጥርስዎና የድድዎ መገናኛን በደንብ ማፅዳት ደግሞ የድድ በሽታን/ ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር ይከላከላል፡፡ ጥርስዎን በሚፍቁበት/በሚያፀዱበ ወቅት የሚከተሉትን መሰረታዊ ነገሮች ማወቅ/መተግበር ያስፈልጋል፡፡ • ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ጥርስዎን መፋቅ/መቦረሽ፡- ጥርስዎን በሚቦርሹበት ወቅት በችኮላ ሳይሆን በእርጋታ ጊዜ ወስዶ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ • ትክክለኛ የሆነ የጥርስ መቦረሻ እቃዎች መጠቀም፡- የጥርስ ሳሙናዉ ፍሎራይድ ያለዉ መሆን አለበት፤ የጥርስ ቡርሹ ደግሞ ለስለስ ያለ ሆኖ ከአፍዎ ጋር የተመጣጠነና ምቾት ያለዉ መሆን አለበት፡፡ ከተቻለ በባትሪ ወይም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የጥርስ ቡርሽ ቢሆን ይመረጣል (በተለይ የእጅ ጣቶች የመገጣጠሚያ ችግርና ሌሎች በእጅ የመቦረሽ ችግር ላለባቸዉ ሰዎች)፡፡ • ትክክለኛዉን ዘዴ /ቴክኒክ መከተል፡- የጥርስዎን መቦረሻ በተወሰነ አንግል መያዝ በተለይ ጥርስዎና ድድዎ በሚገናኝበት ቦታ በቀስታ መቦረሽ፡፡ ሲቦርሹ የጥርስዎን የዉጪኛዉን፣ የዉስጠኛዉን፣ የማኘኪያዉን ቦታ/ chewing surfaces እና ምላስዎን ማጠቃለል ያስፈልጋል፡፡ • የሚፍቁበትን መሳርያዎች በንፅህና መጠበቅ፡- ጥርስዎን ከቦረሹ በኃላ መቦረሻዉን በዉሃ በደንብ ማጠብ ያስፈልጋል፡፡ ከተቻለ መቦረሻዉን ሲያስቀምጡ ቀና አድርገሁ ማስቀመጥ፤ በአየር እንዲደርቅ ማድረግ፤ ባክቴሪያ/ተዋሲያን እንዳያድጉበት ወይም እንዳይራቡበት በተዘጋ/አየር በደንብ በማይዘዋወርበት እቃ ዉስጥ ከድኖ ያለማስቀመጥ • የጥርስዎን መቦረሻ መቼ መቀየር እንዳለብዎ ማወቅ፡- የጥርስዎን መቦረሻ በተቻለ መጠን በየ 3 ወይም 4 ወራት መቀያየር፡፡ የጥርስ መቦረሻዉ ካረጀ/ከተበላሸ (የመፋቂያዉ ቦታ) ቀደም ብለዉም መቀየር ይችላሉ፡፡
በጥርስዎ መካከል ያለዉን ቆሻሻ ማዉጣት/ ፍሎሲንግ በጥርስዎና በጥርስዎ መካከል ያለዉን ቦታ በጥርስ መቦረሻ መድረስ/መፋቅ አይችሉም፡፡ ስለሆነም በጥርስዎ መካከል የሚቀረዉን ቆሻሻ በጥርስ መጎርጎሪያ በየቀኑ ማዉጣት ለአፍዎ ጤንነት ስለሚረዳ በሚገባ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡
ምንጭ - ማህደረ ጤና ደረ ገፅ