top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ’’ - ኔትዎርክ



እንዴት ሰነበታችሁሳ? በዚህ ርዕስ መፃፍ ካቆምኩ ቆይቻለሁ። ስለዚህ ማለት ያለብኝ እንዴት ከረማችሁሳ? ነው ። ሰዎችዬ ከርሞ መገናኘት በዚህ ዘመን ብርቅ ነገር ሆኗል ። ለምን ብትሉ በደቂቃ ልዩነት የሆነ ቦታ ላይ የሆነ እሳት ተነስቶ መክረምና አለመክረም ፣ መሰንበትና አለመሰንበት አሻሚ ነገር ሆኗልና ። የታሪክ ሽሚያ አለ። የክልል ሽሚያ አለ ። የስልጣን ሽሚያ አለ። የዘረፋ ሽሚያ አለ። አጉል የሆነ የጀብደኝነት ሽሚያ አለ። የማፍረስ ሽሚያ አለ። የማፈናቀል ሽሚያ አለ ። መልሶ በማቋቋም ጊዜም ያልተፈናቀሉ ሰዎች ተፈናቃዮች መሐል ለመደመርና በኋላ ደግሞ የመቋቋሚያ ብር ተሻምቶ ለመውስድ ግፊያ መሻማትም አለ። ሽሚያ በሽሚያ።

ለነገሩ እኛ ባናውቅ እንጂ ችግሮች እየተፈጠሩ የሚያስቸግሩን ‘‘በኔትዎርክ’’ ፣ እየተሰመሩ ነው። ‘‘ በጌታ በየሱስ ክርስቶስ ስም ! ይሄ ኔትዎርክ የሚባለውን ክፉ መንፈስና አጉል መስመር ከሀገራችን ላይ ይንቀልልን!! ይመታ !! ይወጋ !!’’

ምክንያቱም ስራ ለመያዝ በኔትዎርክ፣ ለመነግድም በኔት ዎርክ ፣ ነቢይነትም በኔት ዎርክ፣ ስልክ ለመደወልም በኔትዎርክ፣ ቻት ለማድረግም በኔትዎርክ ፣ ስኳር አከፋፋይ ለመሆንም ኔት ዎርክ ፣ ሹመት ለማግኘትም በኔትዎርክ ፣ ለዘይት አከፋፋይነትም ኔትዎርክ ….ኔትዎርክ በኔትዎርክ!!

ሁሉም ነገራችን ያለኔትዎርክ አልሰራ፣ አልንቀሳቀስ ፣ ብሏል ። ‘‘ በጌታ በየሱስ ክርስቶስ ስም ! ይሄ ኔትዎርክ የሚባለውን ክፉ መንፈስ ከሀገራችን ላይ ይንቀልልን!!’’

የኔትዎርክ ነገር ሲነሳ ትዝ ያሉኝ ነገሮች አሉ ። መቼስ ካድሬዎች በሚሰበሰቡበት ስፍራ ብዙ ደሳስ የሚሉ ገፀ ባህሪዎቸ ትመለከታላችሁ። እንደኔ ያለው የመፃፍ ሱስ የተጠናወተው ሰው ደግሞ በእንዲህ ያሉ መድረኮች ላይ ሲገኝ የስብሰባውን አጀንዳ ይተውና የሰው ዓመል ይቃርማል።

አንድ ጊዜ ነው። የአንድ ዞን ካድሬዎች ተሰብስበዋል። የኔትዎርክ ንፋስ ፣ በኔትዎርክ አማካኝነት የሚሰራው ሻጥር፣ ከፖለቲካ አመራሩ ተነስቶ በተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት ጭምር በዓውሎ ንፋስ ጉልበት እየነጎደ ማህበራዊ ተቋሞቻችንን ጭምር እያፈረሰ የመሆኑ ነገር ተነሳ።

አንድ ሰው ፣ ‘‘ ይሄ ኔትዎርክ የሚባለው ነገር ቸርችም ውስጥ ግብቷል።…’’ ፣አሉና ጀመሩ ። ‘‘ነገሩ እነዲህ ነው ። አንድ ወጣት ፓስተር መድረክ ላይ ወጥቶ ስብከት ማሰማት ጀመረ። እንዲህ እያለ። ‘ እያንዳንድሽ አዚህ የተሰበሰብሽ መከራ መጥቶብሻል! በቤትሽ ውስጥ ሴጣን እየዘለለ ነው ። በረከት የለም ። መስማማት የለም ። ብርኩሰት ሸተሻል ። በቤትሽ ውስጥ ክፉ መንፈስ ተፈልፍሏል፡፡’….’’ ፓስተሩ ወጣት የሚናገረው በሙሉ ተስፋ የራቀው ነገር ነው ። ምንም የብርሀን ቃል የሌለው ።

‘‘በስብከቱ አዳራሽ ውስጥ የተገኙና ይህንኑ ሁኔታ የታዘቡ አዛውንት ተበሳጩ ። ስሜታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። በዚህ ምክንያት ፣ ‘ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሴጣን ከመድረክ አውርድ! የሰራዊት ጌታ ይህንን የሴጣን መልክተኛ ከዚህ መድረክ ላይ አንሳ!! … ’ ’ ፣ አሉ በታላቅ ድምፅ።

ድንገት ከኋላ ተነስቶ ‘‘ አንተ ምን አገባህ ይላል ጌታ እየሱስ ክርስቶስ !! ’’ በማለት ሽማግሌውን በጎረምሳ ድምፁ ያስደነበራቸው ወጣት፣ ለካ የሰባኪው ኔትዎርክ ኖሯል ፡፡ የገረመኝ ነገር ። ለካ ኔትዎርክ ለሰው ልጅ ክብር የለውም።አንቱ የሚባሉትን ሰው አንተ አላቸዋ!!

ሰሞኑን ደግሞ እንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ነገር አስገርሞኛል። አንድ ቤቱን መሸጥ የፈለገ ሰው ነው ። ቤቱን መሸጥ ወደፈለገው ወደዚህ ሰው ብዙ ገዢዎች መጥተዋልም ። ወደርሱ ከመጡት ገዢዎች መካከል ትልቁን ገንዘብ ለመክፈል የፈለገው ገዢ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ቆጥሮለታል ።

ይኸው ቤት ሻጭ ሰውዬ እሀድ እሁድ ቸርች ይሄዳል ። የቸርቹ ፓስተር ፣ ‘‘ ቤት ለመሸጥ ያሰብክ ወንድሜ እዚህ አለህ ። ስምህ ደረጀ ነው ። አሁን ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ቤቱን ለወንድም ዓለሙ በ8መቶ ሺ ብር እንድትሸጥለት የሚል መልዕክት ነግሮኛል ፡፡ ተባርከኻል ። ቤቱን ለተባለው ሰው ሽጥለት። ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ላንተ ከዚህ ሶስት እጥፍ ሚበልጥ በረከት አዘጋጅቶልሀል!....’’

አንደንድ ፓስተሮች ድለላም ይሰራሉ ላካ !! ይሄም እንግዲህ በኔትዎርክ ነው የሚሰራው ። እናንተዬ፣ ለኔ የሚታየኝ የቸርች ውስጥ ማጭበርብር አይታያችሁም? ይኸው ይህን ወግ እያወጋኋችሁ የቡሄ ጅራፍ እየጮኸ ነው ። ክርስስቶስ ዳግመኛ መጥቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተሰበሰቡትን ነጋዴዎች ምናለ በጅራፍ እየጠበጠበ ባሰወጣቸው !

አንድ ወዳጄ የነገረኝን እዚህ ጫወታ ላይ ቢደመር ። ዘመኑ የመደመርም አደል? ግን መደመር የሚጠናቀቀውና ሰላምም ተባዝቶ ተባዝቶ የሚትረፈረፍልንንና እፎይ ብለን ያለ አንዳች የስጋት ሀሳብ ወጥተን የምንገባው፣ ተኝተን የምንነሳው መቼ ነው ? ይሄ ቀን ናፈቀኝ !! ማርያምን!!

ወዳጄ ወደነገረኝ ጉዳይ፡-

ደቡብ ክልል ውስጥ ቡና ሲያሸትና ለሽያጭ መዋል ሲጀምር ብዙ የገጠር ቸርቾች ይዘጋሉ ። አንዳንድ አምላኪና ሰባኪ ውሎና አዳሩ ከተሞች ውሥጥ ይሆናል። ፊለፊቱ ኮካ ኮላ ያስቀምጥና ከኮካኮላው ጀርባ ቢራ አቁሞ ይጋሽራል። ቢራ በኮካ ፓንች እያረገ ሲጠጣ ይሰነብታል። ሴት እየገዛ ያድራል ። በቃ ፣ አስርቱ ትዕዛዛት ፣ ሰኪውሪቲስ ፣ድንገት ወደ ህሊናው ቢመጡ እንኳ ‘‘ ፓስ ፣ ፓስ ሲል ፣ ቅዱስ ቃላት አይምሮው ላይ ተፅፈው ቢያገኛቸው ተር፣ ተር። ተረር.. ተረር አርጎ ሲቀድ ፣ ‘‘ፓስ -ተር ፣ፓስ -ተ ተረር ’’ ፣እያደረገ ይሰነብታል ። ቢራና ኮካ መግዣው ሲሟጠጥ ፣ ሴት መሸመጫውም ሲጠናቀቅ ፣ ከተማውን ትቶ ወደ መንደሩ ይመለሳል።

የተዘጉት ቸርቾች እንደገና ይከፈታሉ ። የንሰሀ ስብከት ፣ የንሰሀ መዝሙር እንደገና ይጀመራል።

መዝሙሩ፡-

‘‘ ጌታ ሆይ …

ወራዳ ባሪያህ ነኝና፣

ማረኝ እንደገና ፡፡

አምላክ ሆይ….

አመንዚራ ባሪያህ ነኝና፣

ማረኝ እንደገና …..’’

ፈጣሪን እንዲህ ያለ የምህረት ጥያቄ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ነው ለካ የኛን ጥያቄዎች እንዳይመልስ ቢዚ ያረጉብን። ይኸው በዚህ ምክንያት ኑሮ መሮብን እኛም ተማረናል።

ለነገሩ ዕውነተኛ አምላኪ እየሳሳ ሄዷል። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ የሰው ህይወት የሚቀጥፉ ክፉ መንፈሶች ባልተባዙ። ይህንን የዕውነተኛ አምላኪ መሳሳት ሳነሳ ትዝ አለኝ አንድ

ነገር ፡-

አንድ ጊዜ የደቡብ ክልል ኮር አመራሮች፣ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሙያተኞችን አስከትለው በክልሉ ውሥጥ ወደ ሚገኙ ያርሷደር መንደሮች አቀኑ። አብዛኛው የክልሉ አመራር አማኝ ‘‘ ነበር’’ ።

የጉዞው ፕሮግራም በቅድሚያ ያርሷደሩን ማሳ ካርሷደሩ ጋር ማበጀት ። ከርሷደሩ ጋር ማረም። ከርሷደሩ ጋር ማረሰ። መኮትኮት …

ሁለተኛው ፕሮግራም ካረማ ፣ካረሳና ኩትኳቶ….በኋላ ካርሷደሩ ጋር አርሷደሩ በገጠሙት ችግሮች ዙሪያ ውይይት ማድረግ ነበር። እንዳጋጣሚ ሆኖ ለነዚህ ተግባሮች ከወጡት ኮር አመራሮች መካከል አንደኛው ኮር አመራር የትውልድ መንደር መገኘት ! ሰውየው አማኝም ይመስሉኛል።

እዚህ መንደር ውስጥ ደግሞ አጋጣሚው ወደ ትውልድ መንደሩ ባመጣው ኮር አመራር ላይ በጅጉ የተማረሩ አርሷደር አሉ። ኮር አመራሩ ግን ቁና ቁና እየተነፈሰ ፣ ላቡ እየተንዠቀዠቀ ሲያርምና ሲኮኩት ብታዩት !! - ያውም የተማረሩበትን አርሷደር ማሳ ። በቃ እርሱ ሆነ - አንደኛ ያርሷደሩ ትከሻ !!

አርሷደሩን ያማረራቸው ጉዳይ ፣ የዚህ ኮር አመራር ወንድም የሆነ ሰው የዕርሻ መሬታቸውን ወሰን እየገፋ ዝም መባሉ ነው። አቤት ቢሉም ሰሚ አላገኙም። ወረዳ አመራሩም የኮር አመራሩ ኔትዎርክ ስለሆነ ፣ የቀበሌ አመራሩም የኮር አመራሩ እና የወረዳ አመራሩ ኔትዎርክ ስለሆነ ለጩኸታቸው መፍትሄ አጥተዋል። በነገራችን ላይ የቴሌ ኔትዎርክ እየቀነሰ ፣ የሙሰኝነት ኔትዎርክ ከፍ ያለ እድገት እያሣየ መምጣቱ !

አረምና ኩትኳቶው ተጠናቆ ውይይቱ ሲጀመር ምሬት ያንገሸገሻቸው እኚህ አርሷደር ሀሳባቸውን የመግለፅ እድል አገኙ።

እንዲህ አሉ፡-

‘‘ እኛ ሀገር እባብ አለ። እኛ ሀገር ያለው ዕባብ እንቁላል ይወጣል። እንቁላል ከዋጠ በኋላ ዛፍ ላይ ይወጣል። ዛፍ ላይ ከፍ ብሎ ከወጣ በኋላ ወደ መሬት ዱብ ብሎ ይወድቃል ። እንደገና ይወጣል። ወደ መሬት ይፈጠፈጣል። ይህንኑ ድርጊት መላልሶ ደጋግማል…’’ ፣ ካሉ በኋላ የበደል ጩኸታቸውን ‘‘በኔት ዎርክ ’’ ፣ እያፈነ ወዳማረራቸው ኮር አመራር አተኩረው ተመለከቱ። በእልኸኛ ዐይኖቻቸው ወግተው ፣ አመልካች ጣታቸውን ጭኖቹን ተንተርሶ ዘፍ ያለ ቦርጩ ላይ ቀስረው ፣ ‘‘ አንተ የመጣኸው ….. አንተ የመጣኸው የዋጥከውን እንቁላል ለመስበር ነው!!!…. አይደለም ? ’’፣ አሉት ።

‘‘ ሂድ እንግዲህ !! ’’ ፣ ይላል-ጭንቄሶ ።

በነገራችን ላይ ቴሌ ከነዚህ ሰዎች ይህንን ‘‘ኔትዎርክ’’ ነጥቆ የኛን የስልክ ኔት ዎርክ ችግር ለምን አይፈተታልንም?

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’


39 views0 comments
bottom of page