top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ’’ - ሚጥሚጣ የማያስለቅሳቸው  ዓይኖችhttps://www.meskanmedia.com/single-post/2018/08/29/yesew-amel-zetegn-mitmita-yemiyaslekishachew

እንደምን ናችሁ ? እንደምንስ አደራችሁ? አሁን አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ ነው። በጥሞና አዳምጡ። ጥሞና የብልህነትና የዕውቀት መግቢያ በር ነው።

አንድ አዛውንት ነበር።

አዛውንቱ ከብቶች ወደማደሪያቸው ከገቡ በኋላ፣ጀንበርም ወደማረፊያዋ ከወረደች በኋላ፣ ያካባቢውን ወጣት ወጣት ልጆች እግሩ ሰው አስቀምጦ ያስተምራቸዋል። መልካም ሰው የሚያደርጋቸውን ትምህርት ነው የሚያስተምራቸው።

በነገራችን ላይ ዛሬ ላይ ብልህነትን የሚያስተምር አዛውንት አለ? ሽበትና ጋቢ ሁሉ ፖለቲከኛ ሆኖ እየቀረኮ ነው። አንዳንዱ ሰው ሽምግልናው፣ ጋቢው ትዝ የሚለው ሽበቱን ማበጠር የሚያስታውሰው መች መሰላችሁ? ስብሰባ ሲኖርና የፖለቲካ ሰዎች አጀንዳ ቀርፀው ለጥያቄ ሲያሰልፉት ።

ያልተዘራ አይታጨድም ። ፖለቲከኛውም ሳይቀር ሽምግልናን መጠየፍ ፋሸን አረገውኮ። ሽበት ዓረም እየመሰለው ‘‘ አረም ማጥፊያ’’፣ መጠቀም ይጀምራል- የጣሪያ እድሳት። ገና የራስ ቅሉ ላይ ሽበት ማቆጥቆጥ ሲጀምር አናቱን በማጥቆሪያ ቀለም ይዘፈዝፋል ። ፂሙን መድምዶ ፊቱን በግሬደር አሳምሮ የተጋጠ ሜዳ አስመስሎ ይወጣል። ወጣትና ልጅ ሆኖ ለመታየት ፣ ሽበቱንም ለመካድ ትግል ውስጥ ይገባል። በዚች ደሀ ሀገር ላይ ስንት ትግል የሚያስፈልገው ነገር እያለ የፀጉር ማጥቆሪያ ቀለም ኢምፖርት እንዲደረግ ሞቲቭ ይጨምራል። የዕድሜ በረከትን ላለመቀበል ይለፋል። እንኔን የሚገርመኝ ነገር አንዳንዱ፣ ኢምፖርት ተቀብቶ ኤክስፖርትን ማበረታታት አለብን የሚል ዲስኩር በቴሌቭዥን መስኮት ሲያሰማ መታየቱ። ያልተዘራ አይታጨድም። ለነገሩ ዕድሜን በሚቀሽብ ህብረተሰብ መሀል ካደገ ዜጋ ምን ይጠበቃል።

ጊዜው ክረምትም አይደል ። ጣራ አዳሾችን ፣ ፀጉራቸውን በቀለም የዘፈዘፉትን፣ ዝናብ አናታቸውን አበስብሶ ፣ ከበሰበሰ አናታቸው ላይ የሚንቆረቆረውን አካባቢ በካይ የጠለሸ ጎርፍ ተመልክተን በአካባቢ ብክልት የሚጠየቁበትን ማስረጃ እናገኝ ዘንድ ሾፌሮቻቸው ከተባበሩኝ አንድ ዕቅድ አለኝ። ዋርካ የሚያክል ዣንጥላ ይዘው አለቆቻቸውን ከመኪና ሲወርዱና መኪና ላይ ሲገቡ ኢምፖርት የፀጉር ቀለሞች ታጥበው እንዳይጋለጡ የማገልገል ስራን ሾፌሮቻቸው ካቆሙልኝ ማለቴ ነው።

በመግቢያዬ ላይ ወዳነሳሁት ፣ ብልህነትን ባካባቢው ያሉትን ወጣቶች የሞራል ስንቅ ወደሚያስታጥቃቸው አዛውንት ሰው ልመልሳችሁ።

አዛውንቱ በየዕለቱ ወጣቶቹን እያስተማሯቸው ሳለ አንድ ቀን፣ በመካከላቸው ሌባ የሆነ ወጣት መኖሩን ነገሩት፡፡ ሰምቶ እንዳልሰማ ሰው አለፏቸው።

በሁለተኛው ቀንም ለትምህርት መጥተው፣ በመካከላችን ሌባ የሆነ ወጣት አለ። አሁንም ከኪሳችን ገንዘብ ሲሰርቀን ያዝነው አሉት፡፡ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም አላቸው። የዚህን ዕለትም ለነርሱ መልካም ሰው መሆን ይጠቅማል ብሎ ያሰበውን ነገር አስተምሯቸው ተለያዩ።

በሶስተኛውም ቀን ሌባ አለ ብለው ተናገሩ። አስከትለውም ይሄ ሌባ ወጣት ከትምህርት ቤቱ ይባረር ። ወይም እኛ እንባረር ብለው አዛውንት አስተማሪያቸውን ጠየቁት ።

ይህን ጥያቄ ያነሱትን ተማሪዎቸሁን አተኩሮ ተመለከታችው። ሌባ የተባለውንም ወጣት አተኩሮ አየው። አተኩሮ ሲያያው ደነገጠ። ከድንጋጤው ብዛት ሽንቱ በልብሱ ላይ ሄደ። ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ።

ከዚህ በኋላ ይህንን ተናገረ፡- “እናንተ…”አላቸው ሰርቋል ያሉትን። ‘‘…እናንተ በጎ የሆነውና በጎ ያልሆነውን ነገር ለይታችሁ አውቃችኋል። እርሱ ግን እናንተ ያወቃችሁትን ያህል አላቀወም። ይባረር ትላላችሁ እንጂም የተማራችሁትን አላስተማራችሁትም። አሁን ታዲያ እኔ ካላስተማርኩት ማን ያስተመምረዋል። ስለዚህ እሱ ከኔ ጋር ሲቆይ ሌሎቻችሁ፣ ሁላችሁም ለትሄዱ ትችላላችሀ”፣ አላቸው።

ሌባው ልጅ አለቀሰ። ዕንባው ፎለለለለል-ጉንጮቹ ላይ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ግን አልሰረቀም።

አንድ የሰረቀን ሰው ብታገኙ የምታስተምሩት በምን መንገድ ነው? እርግጠኛ ነኝ አብዛኞቻችሁ የሰረቀው ህፃን ከሆነ ትቆነጥጡታላችሁ። አዋቂም ከሆነ በእጅና በግራችሁ ትነርቱታላችሁ። እኔ በስርቆት ምክንያት ልጇን በጋለ ቢላዋ የጠበሰች ዕናት አውቃለሁ። የሰረቀው ሰው ግን እንዲህ ያለ ቅጣት ሲፈፀምበት ቂምን እንጂ ፍቅር አይወርሰም። ይቅርታ ግን ፍቅርን ያፈሳል። የድሮውን አይነት ሳይሆን አዲስና ጨዋ ሰው ይፈጥራል።

እናንተ ግን ፣ ‘‘ ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም ’’ ፣ እያላችሁ ትተርቱስ የለም?

ሌባ ነው ተብሎ በጓደኞቹ መባረር የተወሰነበት የአዛውንቱ ተማሪ ይቅርታ ሲሰጠው የዘራውን ዕንባና ከዚያም በኋላ ከስርቆት መራቁን ልብ ብላችኋል?

እኛ ሀገር ያሉ ሌቦች ፣ ሀገር ዘርፈው ፣ ይቅርታ እነኋቸሁ ሲባሉ እንኳን ማልቀስ ፣ እንኳን መፀፀት ቀርቶ ዞረው አስፈራሪዎች ይሆናሉ። ጉድ ነው!! የፀፀት እንባ እንዲወርዳቸው ማገዝ ፈልጋችሁ ፣ ሚጥሚጣ ዐይናቸው ላይ ብትነሰንሱ እንኳ ከንቱ ድካም ነው። እንዲህ ሲሆን ግን ፣‘‘ ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም !!!’’ የህግ ዱላ ያስፈልጋል። በህግ አምላክ!! ብያለሁ።

‘‘ ሂድ እንግዲህ !! ’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ ።

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’


19 views0 comments
bottom of page