የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ’’ - ውጡና ወጪ በዛ

እንዴት አረፈደችሁ-ዛሬም?
በአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሂንዱስታንን የሚያስተዳድራት ብልህ ንጉስ ነበር ፡፡ ንጉስ አክባር ነው - መጠሪያ ስሙ ፡፡ ንጉስ አክባርን የሚያማክር ሰው እንዲሁ ነበር፡፡ ራጃ ብርባል ሜናሽ ነው-መጠሪያ ስሙ፡፡ ብርባል ብልህ ብቻ ሳይሆን ፣ ፍርድ አዋቂም ነበር ፡፡
አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፡-
ሁለት የተካካዱ ሰዎች ሰዎች ወደ አክበር ቤተ መንግስት እየተነታረኩና እየተጯጯሁ መጡ፡፡ አንደኛው ለሁለተኛው የውሀ ጉድጓድ ሸጦለታል፡፡ ከሸጠለት በኋላ ሻጩ ፣ ‘‘ እኔ የሸጥኩልህ ጉድጓዱን እንጂ ውሃውን አይደለም ’’ ፣ አለው ፡፡ ‘‘ ሂድ እንግዲህ !’’ ይላል- ጭንቄሶ፡፡
ንጉስ አክባር ብርባል ሜናሽን የተካካዱትን ሰዎች እንዲዳኛቸው ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ብርባል ፣ ‘‘ ጉድጓዱን መሸጥህን ትክዳለህ ?’’ ሲል ጠየቀው - ጉድጓዱን እንጂ ውሀውን
አልሸጥኩም ያለውን ሰው ፡፡ አለመካዱን ነገረው ፡፡
‘‘ በጣም ጥሩ!! ያልሸጥከው ውሀውን ነው ፡፡ ነገር ግን ውሀህን ሰው ጉድጓድ ውስጥ
ማስቀመጥ ትችላለህ? ስለዚህ ሰው ጉድጓድ ውስጥ ላስቀመጥከው ውሀህ በየእለቱ ለዚህ
ሰውዬ ኪራይ ክፈል ፡፡ ያለበለዚያ ግን ውሀህን በአንድ ቀን ውስጥ ከሰው ጉድጓድ ጠርገህ
አውጣ!’’ ፣ አለው ፡፡
‘‘ ሂድ እንግዲህ !! ’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ ።
ይህንን የፍርድ ውሳኔ በሰማ ጆሯችሁ እኛ አገር አንዳንዱ የፍትህ ነገር የሞላ ወንዝ የወሰደው አይመስላችሁም?
ከዓመት በፊት አንድ ፍርድ ቤት የሚያመላልሰኝ ጉዳይ ነበረኝ ፡፡ ክርክሩን ትቼ ለክርክሩ የተሰየመውን ዳኛ ነበር የምመለከተው ፡፡ በአንድ እጁ የበሰለ ሎሚ እያሸና እየመጠጠን ነው ዳኝነቱን የሚያከናውነው ፡፡ አንድ ጆሮው ላይ የጤናዳም ቅጠል ሰክቷል፡፡ በዚህ ላይ አፍንጫው ውስጥ የተላጠ ነጭ ሽንኩርት ቢወትፍ እንዴት ያምር ነበር እያልኩኝ እላለሁ በውስጤ ፡፡ ፍርድ ቤት ሳይሆን የአበሻ መዳኒት አዋቂ ቤት የመጣሁ እየመሰለኝ ፡፡
ለሚውን እያሸና እየመጠጠ ነው የፍርድ ሀተታውን 38 ገፅ ያነበበው ፡፡ ሁኔታው እያስገረመኝ መቆሜን ረሳሁት እንጂ ያን ያህል ገፅ ሀተታ ሲነበብ ቆሞ የማዳመጥ እቅም አልነበረኝም ፡፡ እንደፈረደብኝ ያወቅኩት ፍርድ ቤቱን ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ ነው ፡፡ የርሱን ሎሚ መጠጣና ጆሮው ላይ የሰካውን ጤናዳም እያየሁ -ጉዳዬን ሳላይ፡፡የእኔስ ግዴለም፡፡ ያልተማረ አርሷደር በበዛባት ሀገር 38 ገፅ ፍርድ ቤት ሀተታ እንዴት ይሆናል?
በነገራችን ላይ ፍትህ ብቻ ሳይሆን የዳኝነት ስነ-ስርዓትም አንዲህ ባለው ዳኛ በኩል ሲታይ ፡፡ እሱንም የሞላ ውሃ ወስዶታል፡፡
አንዳንድ ሞራል የጎደላቸው ህግ አስከባሪ ፖሊሶች የሚሰሯቸው ፌኮች ደግሞያስገርሙኛል ፡፡ አንድ የስራ ባልደረባዬ የሆነ ሰው አምሽቶ ሲገባ ማጅራት መቺዎች ጠብቀው ጥቃት ፈፀሙበት ፡፡ ኮኬውን ይዘው,፣ እግሮቹን መሬት አስለቅቀው፣ እንደተሰጣ ልብስ ያንጠለጠሉት ፡፡ አንጠልጥለው መረመሩት ፡፡ ወሰዱ -ደሞዙን ፡፡
በማግስቱ አቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ሄደ፡፡ ሪፖርት ለማድረግ ፡፡ የዕለቱ መርማሪ ፖሊስ ‘‘ ወንጀሉን የፈፀሙትን ሰዎች ብታያቸው ታውቃቸዋለህ ’’ ፣ ጠየቀው ፡፡ ‘‘ አዎን ፡፡ አይጠፉኝም ’’ ፣መለሰ፡፡
ያገር ፎቶ ግራፍ የተደረደረበትና ግርግዳ ላይ የተለጠፈ ሰሌዳ ወዳለበት ወሰደው ፡፡ ወንጀለኞቹን ከፎቶ ግራፍ ዝርዝሩ ውስጥ ፈልጎ እንዲያመለክተው አዘዘው፡፡
ፈልጎ አገኛቸው ፤ ‘‘ ይኸው አንደኛው ፡፡ ይኸው ሁለተኛው ፡፡ ሶስተኛውም….’’ ፣ አሳየው ፡፡ ‘‘ በል ነገ ተመለስ ’’ ፣ ብሎ ቀጠሮ ሰጠው ፡፡ ነገ ሲሄድ ተነገወዲያ ተመለስ ፡፡ ነገ ተመለስ ፡፡ ተነገዎዲያ ብቅ በል ፡፡ ሲመላለስ ሲመላለስ፡፡ መመላለስ እንጂ መልስ የለም፡፡ ሰልችቶት ጉዳዩን እርግፍ አርጎ ተወው ፡፡
ይህንኑ ጓደኛዬን ፣ ‘‘ ታዲያ ለምንድነው ወንጀለኞቹን ከፎቶ አርካዬቫቸው ለይ ያሉህ? ’’ ፣ ጠየቅኩት ፡፡
‘‘ ለስራ ነዋ! ከተዘረፍኩት ገንዘብ ላይ ለመካፈል ’’ ፣ ብሎ መለሰልኝ ፡፡
እንዲህ ለካ ነገሩ ፡፡ ‘‘ ሂድ እንግዲህ! ’’ ፣ ይላል - ጭንቄሶ ፡፡
አንድ ወዳጄ የነገረኝን ልጨምርላችሁ ፡-
ደራፍት ቀጂ የሆነ ሰው ነው ፡፡ ሁለት ቀን ድራፍት የተሸጠበትን ሂሳብ መኝታ ክፍሉ ፍራሽ ስር ያስቀምጣል ፡፡ መደበቁ ነው ፡፡ እዚያው ቤት ውስጥ አሳ የሚበልት ወጣት አለ፡፡
እግር ጥሎት ድራፍት ቀጂው መኝታ ክፍል ገብቶ ፍራሹን ገለጥ ሲያረግ ይገርማል - ሁለት የታሰሩ አስር አስር ሺ ብሮች ፡፡ አሳ በላቹ ብሮቹ አማለሉት ፡፡ ግን መስረቅ ፈርቶ ትቷቸው ወጣ ፡፡ እንደገና ተመለሰ፡፡ የመስረቅ ድፍረት አሰባስቦ፡፡
ብሮቹን ሰረቀ፡፡ ከሆነ አይቀር ብሎ አንድ ስልክም አከለበት ፡፡ ሶስት የተለያዩ ሱሪዎችን ደራርቦ ከለበሰ በኋላ ፣ አሳ መበለቻ ቢላውን ይዞ ከአካባቢው ተሰወረ ፡፡ ተሳፍሮ ወደሌላ አካባቢ እየተጓዘ ፍተሻ የሚደግበት ጣቢያ ላይ ደረሰ፡፡ጊዜው የፍተሻም አይደለል?
ፍተሻ ሲጀመር ቫይብሬት አደረገ ፡፡ ምን ይዋጠው! የጣቢያው ፖሊሶች ሲፈትሹት የደበቀው 20 ሺብር ፣ ቢላዋ ፣ በዚያ ላይ ሶስት ሱሪ ላይ በላይ ደራርቦ -በዚህ ወቅት ፡፡
‘‘ አደገኛ ወንጀለኛ ያዝን!!’’ ፣ አሉ -ፖሊሶቹ ፡፡ የሰረቀውን የተዘጋ ስልክ እንደከፈቱ ፣ ‘‘ ጭርጭርር …’’ ፣ ማለት የጥሪ ድምፅ፡፡ ደዋዩ ‘‘ አንተ ሌባ ብሬን ይዘህ ጠፋሕ? ’’ ፣ አለ፡፡
‘‘ ሌባው ተይዟል ፡፡ ….’’ ፣ ስልኩን ያነሳው ፖሊስ፡፡
ብሩ የተሰረቀበት ድራፍት ከማሽን አንዠቅዣቂ ስሙ ወደ ተጠቀሰው የፍተሻ ጣቢያ ፡፡ በ700 ብር መኪና ተኮናትሮ ፡፡ ደረሰ፡፡
ብሬን ስጡኝ ሲል ለበላይ አካል ተላልፏል አሉት ፡፡ አስከተሉና እነርሱም ሌባውን በመያዝ ላከናወኑት ተግባር ከተያዘው ብር ላይ ቃል ይገባልን ሲሉ ጠየቁ ፡፡ ብሩ እግዚቢት ሆኖ ተቀምጧል ወደ ተባለበት አካል እስኪደርሰስ በየፌርማታው የሚጠየቀው የውለታ ክፍያ ፣ የምርመራ መዝገብ ለማዘጋጀት እጅ መንሻ ፣ ....... የቀረበለት ጥያቄ 22 ሺ ብር ደፈነ ፡፡
እንዴት ነው ነገሩ? ከተሰረቀ ሰው የሰረቀ ተሻለኮ፡፡ ምን ወጪ አለበት? ክስ ከተመሰረተ በኋላ ወደ ዳኛ ሲኬድ ውሳኔ ለማሰጠት ወጪ፡፡ ከውሳኔው በኋላም ገንዘቡ ይሰጠኝ ለማለት ለፍታብሄር ጉዳይ ማስፈፀሚያ ወጪ ፡፡ ወጪ በወጪ…
ዘንድሮ ውጣና ወጪ በዝቶብናል!!!
‘‘ ሂድ እንግዲህ ! ’’ ይላል- ጭንቄሶ፡፡
‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’
ከወደዱት ሼር ያርጉ