top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ኦሜጋ – 3››: የስኳር እና የልብ በሽታዎችን ጨምሮ ለ7 የተለያዩ በሽታዎች ተፈጥሯዊ መፍትሄኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ (Omega-3 fatty acid) ከቅባት ዝርያዎች አንዱ ሲሆን በጣም አስፈላጊ ከሆኑት የቅባት ዘሮችም እንደ አንዱ ይቆጠራል፡፡ ኦሜጋ-3 ለሰዎች ጤንነት እጅግ አስፈላጊ ጠቃሚ የመሆናቸው ያህል በሰውነታችን ውስጥ ግን መመረት አይችሉም፡፡ ስለሆነም እኒህን የቅባት ዘሮች ማግኘት የምንችለው ከምግብ ብቻ ነው፡፡ የዚህን አይነት ቅባት (ኦሜጋ-3) በአሳ ዘይት፣ በአሳ፣ በቱና እና በሌሎችም የባህር ምግቦች ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ኦሜጋ-3 የተባለ የቅባት ዘር ለሰውነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም የአዕምሮን አሰራር እጅግ ከማጎልበቱም በላይ ለህፃናት አካላዊ ዕድገትም ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ የአሜሪካ የልብ ማህበር (American heart association) ቢያንስ በሳምንት ከሁለት ጊዜ ላላነሰ የአሳ ምግቦችን በመመገብ ሊከሰት ከሚችል የልብ በሽታ ራስን መከላከል እንደሚቻል አበክረው ይገልጻሉ፡፡ ኦሜጋ-3ን በመመገብ የተለያዩ እንደ ልብ በሽታ፣ ካንሰር እና የመገጣጠሚያ ህመሞች ያሉ ስር ሰደድ በሽታዎች ሊያመጡ የሚችሉ አጋጣሚዎችን መከላከል ይቻላል፡፡

ከሰውነታችን ክፍሎች ኦሜጋ-3ን በአብዛኛው የሚጠቀሙት የነርቭ ሴሎች ናቸው፡፡ የአዕምሮአችን ይህም በአዕምሮአችን አሰራርና በባህሪያችን ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚያመጣ እሙን ነው፡፡ ገና የሚወለዱ ህፃናትም ይህን ኦሜጋ-3 የተባለ ቅባት ወይ በፅናታቸው ማህፀን ውስጥ አሊያም ከተወለዱ በኋላ ደግሞ በአሳ ዘይት መልክ ተዘጋጅቶ የሚሸጠውን ፈሳሽ ቅባት ካላገኙ የእይታ ወይም የነርቭ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የኦሜጋ-3 እጥረት በተለይም በድካም፣ አነስተኛ የማስታወስ ችሎታ፣ የቆዳ መድረቅ፣ ከልብ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች፣ የአዕምሮ አስተሳሰብ መዋዠቅን (Mood swing)፣ የድብርትንና ደካማ የሆነ የደም ዝውውርን በማምጣት ይታወቃሉ፡፡

በመቀጠል የኦሜጋ-3 ቅባት ለሰውነታችን የሚያበረክታቸውን በርካታ ጥቅሞች አንድ በአንድ እናያለን፡፡ ምንም እንኳን ኦሜጋ-3 ቅባቶች በተለየ ሁኔታ የልብ በሽታን እንደሚከላከሉ ቢታወቅም ከዚያም አልፎ ተርፎ ግን ለተለያዩ ሌሎችም በሽታዎች እንደሚጠቅሙ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የኮሌስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር

በአብዛኛው የባህር ምግብ የሚመገቡ ግለሰቦች የደማቸው የኮሌስትሮል መጠን እጅግ ጤነኛ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥም በሜዲትራኒያን አካባቢና በአንታርክቲክ የሚኖሩ ግለሰቦች ላይ የደማቸው የኮሌስትሮል መጠንን የሚመለከት ምርመራ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በውጤቱም በሁለቱም አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች እጅግ ጤነኛ የሚባል የኮሌስትሮል መጠን በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል፡፡ ይህን ኦሜጋ-3 የተባለ ቅባት በምግብነት በመጠቀም የኮሌስትሮል መቸመርን መከላከል ብቻ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ መቀነስም ይቻላል፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት

ከፍተኛ የደም ግፊት ባለባቸው ግለሰቦች ላይ በተደረገ ተከታታይ ጥናት በኦሜጋ-3 ቅባት የተቀመመ ምግብን አዘውትረው የሚመገቡ ግለሰቦች ላይ የደም ግፊታቸው የቀነሰ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት ያባቸው ሰዎች ላይ በየቀኑ ከ3 ግራም በላይ ኦሜጋ-3 ቅባትን በመውሰዳቸው ብቻ የደም ግፊት መጠናቸው በእጅጉ ሊቀንስ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ የልብ በሽታዎች

የልብ በሽን መከሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቅባት መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ምግቦችን መመገብ ይመከራል፡፡ እኛ የምንመክረው ደግሞ የቅባቱን አይነት በመቀየር እንደ ኦሜጋ-3 ያሉ ብዙም ጉዳት የሌላቸውን ቅባቶች በመጠቀም የቅባት ክምችትን ማስቀረት ይቻላል እንላለን፡፡ በአሳ ዘይት ውስጥ የሚገኙት የቅባት አይነቶችም ለልብ በሽታ አጋላጭ የሚሆኑትን እንደ ኮሌስትሮልና ከፍተኛ የደም ግፊት በሽታን መከሰት በማስቀረት ግለሰቡ የልቡን ጤና እንደተጠበቀ እንዲቆይ ይረዳሉ፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ቅባቶች የደም ስር መጥበብንና የደም መርጋትን ስለሚከላከሉ በተዘዋዋሪ የልብን ጤንነት ይጠብቃሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በየቀኑ የአሳ ዘይት የሚመገቡ ግለሰቦች የልብ በሽታ ቢኖርባቸውም እንኳን በተደጋጋሚ የመታመም እድላቸው እጅግ አናሳ ሲሆን የአሳ ዘይት ከማይመገቡት ይልቅ የመሞት ዕድላቸውም የዚያኑ ያህል አናሳ ነው፡፡ የአሳ ዘይት ከዚህም በተጨማሪ በደም መርጋትና ወደ አዕምሮ ደም የሚያደርሱት የደም ስሮች በቅባት በመደፈን የሚመጣውን የስትሮክ በሽታ መከሰትን ይቀንሳል፡፡ ከላይ እንደጠቀሱትም በሳምንት ቢያንስ ከ2 ጊዜ ያላነሰ የአሳ ምግብ የምንመገብ ከሆነ የስትሮክን መከሰት እስከ 50% በሚደርስ ልንቀንሰው እንችላለን፡፡

ለስኳር በሽታ

በስኳር በሽታ የተጠቁ ግለሰቦች ከፍተኛ የሆነ የትራይ ግላይሴራይድ እና በጣም ዝቅተኛ የሆነ የሃይዴንሲቲ ሊፒድ መጠን በደማቸው ውስጥ አለ፡፡ ከአሳ ዘይት የምናገኘው ኦሜጋ-3 ቅባትም በደማችን ውስጥ ያለውን የትራይግላይ ሴራይድ መጠን የሚቀንሰው ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ የሀይዴንሲቲ ሊፒድ መጠንን ይጨምረዋል፡፡ ስለሆነም የስኳር በሽታ ታማሚዎች የኦሜጋ-3 ቅባትን በመመገብ የስኳር መጠናቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡

የመገጣጠሚያ ህመሞች

በዛ ያሉ ጥናቶች የሚያሳዩት የኦሜጋ-3 ቅባት እንደ ምግብነት ስንጠቀምባቸው በመገጣጠሚያችን ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ህመሞች በተለይም የሪህን በሽታን የህመም ስሜት ለመከላከል ይረዳል፡፡ በዚሁ ዙሪያ የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም የኦሜጋ-3 ቅባቶች የመገጣጠሚያ መላቀቅን፣ የጠዋት ጠዋት ህመሞችን በማስታገስና ለሪህ በሽተኞች ደግሞ የሚወስዱትን የመድሃኒት መጠን እንዲቀንሱ በማድረግ ከማስታገሻነት ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም ይህ የቅባት አይነት ከተለዱት የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ጋር በመቀናጀት በሪህ አማካኝነት ለሚመጡ የመገጣጠሚያ ህመሞችና ለሆድ ህመም በመድሃኒትነት ያገለግላል፡፡

ለአጥንት መሳሳት

በተለያዩ ታማሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት የኦሜጋ-3 ቅባቶች በሰውነታችን ውስ ያለ የካልሲየምን መጠን በመጨመር የአጥንታችን ጥንካሬ እንደተጠበቀ እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡ የዚህን ኦሜጋ-3 የተባለ የቅባት ወይም የሌላ እጥረት ያለባቸው ሰዎች በአጥንት መሳሳት በሽታ የመጠቃት እድላቸው የቅባት መጠናቸው ልከኛ (Normal) ከሆኑት ይልቅ ሰፊ ነው፡፡ የአጥንት ጥንካሬ በመጨመሩ ረገድ የኦሜጋ-3 ጥቅም የሚጎላው ዕድሜአቸው በገፉት ሰዎች ላይ ነው፡፡

ለድብርት በሽታ

ሰዎች በምግባቸው ውስጥ የኦሜጋ-3 ቅባት በቂ ካልሆነ በድብርት የመጠቃት ዕድላቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የኦሜጋ-3 የቅባት የነርቭ ሴል ሜምብሬንን ከሰሩት ወሳኝ ንጥረ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ይህም ነርቭ ሴሎች እርስ በርሳቸው በብቃት መልዕክት እንዲለዋወጡ ትልቅ እርዳታ ያደርጋል፡፡ ይህም አእምሮአዊ ጤንነት እንደተጠበቀ እንዲቆይ ስለሚያደርግ የእነሱ ማነስ በግለሰቡ የስነ ልቦና ሁኔታ ላይ ታላቅ ተፅዕኖን ያሳርፍበታል፡፡ በድብርት ተጠቅተው ሆስፒታል ከገቡ ግለሰቦች አብዛኞቹ የሰውነታቸው የኦሜጋ-3 የቅባት መጠን እጅግ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በድብርት ለተጠቁ ሰዎች በሳምንት ከ2-5 ጊዜ የሚደርስ የአሳ ምግብ ለ5 ዓመት እንዲመገቡ ከተደረገ በኋላ የድብርትም ሆነ የጥላቻ ስሜታቸው ፍፁም እንደጠፋ ይጠቀሳል፡፡

ኦሜጋ-3 ከምን አይነት ምግቦች ውስጥ ይገኛል?

ኦሜጋ-3 ቅባትን ከአሳ፣ ከአትክልትና ከለውዝ በዋናነት ማግኘት ይቻላል፡፡ በዝርዝር ለመጥቀስም ሰርዲን፣ ቱና እና ፍሬሽ የአሳ ውጤቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን ከተክሎች ደግሞ በሶያ ፍሬ፣ በሶያ ዘይት ከዱባ ፍሬ ውስጥ በዱባ ፍሬ ዘይት በለውዝና የለውዝ ቅቤ ውስጥ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የአሳ ዘይት ‹‹Code-liver oil›› በፋብሪካ ተመርቶ በገበያ ላይ ይሻጣል፡፡

Source- http://www.zehabesha.com

64 views0 comments
bottom of page