top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ምንሽን



የሰው አገር ሙጥኝ ብየ-በወጣሁበት እንዳልቀር ሀገሬ ፍቅርሽ ሳበኝ -ግና ምንድር ነው ማፍቀር? እንዳስመሳይ አዝማሪ -ካልሸነገልኩሽ በቀር ከተወለድሁ እስተዛሬ ከጣትሽ መች ጎርሼ ወተትሽን መች ቀምሼ ወለላሽን መች ልሼ ሲርበኝ ጠኔ በቀኝ በግራ እንደ ጭፍራ ሲከበኝ የት ነበር የንጀራሽ ሌማት ሾላ ስለቅም ተሻምቼ ከሽመላ ከማማት ኑሮየ ሁዳዴ ጦም ! ፋሲካ አልባ ህማማት እና ከድሎት አገር የሲሳይ ዶፍ ከሚያወርደው ምን ገፍቶኝ ነው በሞቴ ? ወዳንቺ ምሰደደው ምን ነክቶኝ ነው? ምንሽን ነው የምወደው

እኔና ብጤዎቼ- እኛ ቅብዝብዝ ልጆችሽ መስኮት በሩ ተዘግቶብን- ተበትነን በደጆችሽ ይሄው ሶስት ሺ ዘበን- ወደ ሰማይ አንጋጠን በንዝርት እግር ተንበርክከን -በቀይ እንባ ስንማጠን የእለት እንጀራችንን ነፍጎ- የለት ገጀራችንን ሰጠን::

አሁንማ ለመከራሽ ማን አለና የሚገደው እሪታሽን እንደዘፈን ያለም ጆሮ ለመደው እና ምንሽ ነው ሚስበኝ ? ምንሽን ነው የምወደው?

ዛሬም ሆነ ያለፈው በላባ ብእርም ይሁን- በኪቦርድሽ የተፃፈው ታሪክሽን ሳነበው -ደምና አመድ ነው የሞላው መች ተነቅሎ ከወለልሽ -የሾህ ጉንጉን አሜኬላው መች ተጥሶ ያውቃልና -የጭቆናሽ ዘመን ኬላው ስልጣን ፈልሶ ቢሸጋገገር ካንዱ ጭራቅ ወደ ሌላው::

እናም እንሆ! ያለፈውን ዘመን ትቼ የቀረኝን እያሰላሁ የብርሃን ቅሪት ባጣ አምፖሌን በተስፋ ሞላሁ እንጀራየን እንደ ሀሰን* በዳበሳ እየበላሁ::

ከዚህ ሁዋላ አልልሽም ወዴት አለ ያንቺ አለኝታ? ምንሽ ነው ግን የሚስበኝ ልማድ ይሆን ወይ ይሉኝታ እግሬን ከምድርሽ ጋራ ምንድነው ያስተሳሰረው ያገር ፍቅር አለኝ ብልስ-ምንሽን ነው የማፈቅረው?

(ተፃፈ በመስከረም 9/ አዲሳባ ጉርድ ሾላ)

*ሀሰን ተብሎ የተጠቀሰው ሀሰን አማኑ የተባለው ዝነኛው አይነስውር የወሎ አዝማሪ ነው::

10 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page