• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’‘‘ብርዝ አፍላቂው ነቢይ¡¡’’ (በደራሲና ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ)

Updated: Jun 9, 2019‘‘ታዲያሳ !’’ ፣ይባል ነበር-በድሮ ሰላምታ፡፡

ቆየት ባለ ጊዜ አንድ አያቴ ቤት ይኖሩ የነበሩ አሮጊት ታዲያሳ! ሲባል መልስ ነበራቸው ፡-

‘‘ ይታሰር በጓሳ! ’’ ፣ ይላሉ፡፡

እናንተዬ ጓሳ ምንድነው ? የምታውቁ ላላወቅኩት አሳውቁኝ ፡፡

ለማንኛውም ታዲያሳ ! ብያችኋለሁ፡፡

መቼስ እዚች አገር ላይ ነቢይ በዝቷል፡፡ ትንቢት ተናጋሪ እንደ አሸን ፈልቷል፡፡ የላይኛው ወርዶ ካላቀዘቀዘው በስተቀር ነቢይነት መንተክተኩን የሚያቆም አይመስለኝም፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ!’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ፡፡

በሰሞኑ አንድ ወዳጄ የሆነ ነገር አጫወተኝ፡-

‘‘ምን ትመስላለች መሰለህ ልጅቱ … ’’ ፣ ብሎ ጀመረልኝ፡፡ ‘‘ ምንትመስላለች መሰለህ ልጅቱ፡፡ ከንፈሮቿ ፣ አፍ ያስከፍታሉ- ኣ! ጉንጮቿ ስርጉድ ከመሆናቸው ባሻገር ስትስቅ ልብ ታቀልጣለች፡፡ ሽንጧ ወደ አከርካሪዋ ተለጥፎ ፣ ዳሌዋ ግን ወደ ደጅ ወጥቷል፡፡ ችቦ አትሞላም አይነት ናት-ጄሪ…….’’

‘‘ሂድ እንግዲህ !! ’’ - ይላል ጭንቄሶ፡፡

አንድ ነቢይ ነኝ ያለ ሰው ፣ ወደ ጄሪ መጣና ፣ ‘‘ ጌታ ወዳንቺ ልኮኛል ’’ ፣ አላት ፡፡

ምን ብላ ብትመልስለት ጥሩ ነው ? ‘‘ አላገኘኋትም በለው!’’

ትልቅ ሰው -ጄሪ፡፡ መኪናው ሳይገለበጥብሽ ‘‘ባርፋ ’’ ወረድሽ! የመኪናው ፍጥነት ግን እንዴት ከባድ ነበር መሰለሽ! ትልቅ ሰው!-ጄሪ

እግረ መንገዴን አንድ ያሳቀኝን ጥያቄና መልስ ባጫውታችሁስ?

ነዳይ የሆነ ሰው ነው ፡፡ አንድ መኖሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ቆሞ ፣ ‘‘ ስለግዚያብሀር ! የግዜያብሄር ወዳጆች …. ’’ ፣ እያለ ምፅዋት ይጠይቃል፡፡

የቤቱ እመቤት ድምፁን ሰምታ መጣች፡፡ ‘‘ እግዜያብሀር ይስጥህ!’’ ፣ አለቸው፡፡

አርሱ መልሶ ምን አላት መሰላችሁ? ‘‘ እግዜያብሄር ሲሰጠኝ ምን ይዤልሽ ልምጣ ?’’

ኻ!ኻ!ኻ!ኻ!ኻ!ኻ!ኻ!ኻ… ጉድኮ ነው!!

አንድ ሌላ ወዳጄ ደግሞ ብርዝ ከመሬት ስለሚያፈልቀው ነቢይ የነገረኝ እነኋችሁ፡-

ነቢዩ ሉሻሸቤ መሬትን በያዘው ጦር ሲወጋት ማር ታፈልቅለታለች፡፡ ከዚያ በኋላ ሉሻሼ ወደርሱ የመጡትን ምእመናን ብርዝ ያጠጣቸዋል፡፡ ብርዙም ቸርቹ በራፍ ላይ ይሸጣል-ታሽጎ ፣ታሽጎ፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ ! ’’ - አለ ጭንቄሶ፡፡

ያው ወትሮም እንደሚያደርገው መሬትን በጦር ወጋት -ነቢይ ሉሼ ፡፡ ብርዝ ሊያፈልቅ ፡፡ ደጋግሞ ቢወጋትም መሬት ወገመች ፡፡ ብርዝ አላፈልቅም አለች፡፡ በዚህ ቢወጋት ፣ በዚያ ዞሮ ቢወጋት ፡፡ ብርዝ የለም አለች ፡፡ ብርዙን ጠጣችው እንዴ ለራሷ!?

‘‘ሂድ እንግዲህ! ’’ ይላል- ጭንቄሶ፡፡

ለካ እርሱ ፣ ነቢይ ሉሻሸቤ መጀመሪያ ሰው ሳያይ ስልቻ ሙሉ ብርዝ መሬት ውስጥ ይቀብራል፡፡ ከዚያም ስልቻው እንዳይታይ አፈር ነስነስ ይደረግበታል፡፡ ምዕመናኑ ተሰብስበው ሳለ ነቢይ ሉሼ መሬትን በጦር ሲወጋት ብርዝ ፍልቅ ከመሬትĺĺ ብርዝ ፣በብርዝ ነበር፡፡

የዛን ዕለት ግን መሬት ወገመች!!

መሬት የወገመችው ፣ ብርዝ አላፈልቅም ያለችው፣ ግብረ ጉዳን የተቀበረው ብርዝ ሽታ ጠርቷቸውና ከየአገራቸው ተሰብስበው የብርዙን ስልቻ ወንፊት አርገውት ነው ፡፡ ወንፊት አርገውት ብርዙ ፈሶ ለራሳቸውም ጠግበው ለመሬትም ተርፈዋል!! ምድረ ቀጫጫ ጉዳን ብርዝ ጠግቦ ጠግቦ ፣ ቦርጭ አውጥቶ እርስ በርስ እየተገፋፋ፣ ምናለ ዞር ብትልልኝ ! እያለ ሰነበተ፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ !’’ ፣ ይላል ጭንቄሶ፡፡

ሰዎችዬ አይናችን ሊጠፋኮ ነው- በየፈርጁ አጭበርባሪያችን በዝቶ፡፡

‘‘ የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’

#ብርዝአፍላቂውነቢይ

(በደራሲና ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ)

25 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean