top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የደም አይነቶች



አራቱ የደም አይነቶች “ኤ”፣ “ቢ”፣ “ኤቢ” እና “ኦ” በተለይም ስለ ጤንነታችን በርካታ ጉዳዮችን እንደሚናገሩ ነው ባለሙያዎች የሚገልፁት። ለአብነትም የደም አይነታቸው “ኤቢ” የሆኑ ሰዎች አርቀው የሚመለከቱ እና በነገሮች ላይ ተስፋ የሚጥሉ እና ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። “ኦ” የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ደግሞ ለጭንቀት ቦታ የሌላቸው እንደሆኑ የሚነገር ሲሆን፥ በሆድ ህመም የመጠቃት እድላቸው ደግሞ የሰፋ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በርካታ ጥናቶች እያንዳንዱ የደም አይነት የራሱ በጎ እና መጥፎ ጎኖች እንዳሉት አመላክተዋል። በመሆኑም የደም አይነታችን ማወቅ ጤናችንን የበለጠ ለመጠበቅ እንደሚረዳ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

እርግጥ ነው እድሜ፣ ጾታ፣ በራሂዎች (ጂኖች) እና ሌሎችም ምክንያቶች በተለያዩ ህመሞች የመጋለጥ እድላችን የማስፋት ወይም የማጥበብ አቅም ይኖራቸዋል። ጤናማ አመጋገብና የኑሮ ዘይቤ ከተለያዩ እክሎች በፍጥነት ለመውጣት እንደሚያግዙም ሊዘነጋ አይገባውም። ከዚህ በታችም የደም አይነታችን ከጤንነት ሁኔታችን ጋር እንዴት ይያያዛል? የሚለውን እንመለከታለን። “ኤ” የደም አይነት ባለሙያዎች እንደሚሉት “ኤ” የደም አይነት ያላቸው ሴቶች ለበርካታ አመታት ልጆችን መውለድ ይችላሉ። ይህ አይነት የደም አይነት ያላቸው እንስቶች ለረጅም አመታት የዘር እንቁላሎችን የማፍራት አቅም አላቸው ተብሏል። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች “እድሜዬ ሳይገፋ በፍጥነት መውለድ አለብኝ” በሚል ሊጨነቁ አይገባም ነው የሚሉት ተመራማሪዎች። “ኤ” የደም አይነት ያላቸው ሰዎች አልኮል የተለያዩ የህመም ስሜቶችን በቀላሉ ያባብስባቸዋል።

ለሆድ ካንሰር የመጋለጥ እድላቸውም ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። “ቢ” የደም አይነት ስፖርትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምታዘወትሩ እና የምታፈቅሩ “ቢ” የደም አይነት ያላችሁ ሰዎች በጣም እድለኞች ናችሁ ተብላችኋል። ይህ የደም አይነት ሰውነታችን በተለይም ጡንቻዎቻችን ለአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋል። የምግብ መፈጨት ሂደት እንዲቀላጠፍም ያግዛል። ይሁን እንጂ የደም አይነታቸው “ቢ” የሆኑ ሰዎች ለጣፊያ ካንሰርና ለሆድ ህመም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል። ለከፍተኛ የመርሳት በሽታ (አልዛይመር) እና ከፍ ሲልም ለአዕምሮ መሳት ሊዳርግ እንደሚችል ነው የሚነገረው። “ኤቢ” የደም አይነት ይህ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ ኮርቲሶል የተሰኘ ሆርሞን ለረጅም ጊዜያት በተመሳሳይ ሁኔታ መገኘት ከጭንቀት ነፃ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ለበርካታ ስዓታት ያለ ድካም የመስራት ብቃት የማላበስ ባህሪ እንዳለውም ይነገራል።

የደም አይነታቸው “ኤቢ” የሆኑ ሰዎች የማስታወስ ችግር ይሰተዋልባቸዋል ይላል በጆርናል ኒዮሮሎጂ ላይ የወጣ ጥናት። በተለይም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። ኤቢ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ደም የመርጋት ችግር ያጋጥማቸዋል፣ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠንም በደማቸው ውስጥ ይኖራል ነው የሚሉት፥ በአሜሪካ ቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ የህክምና መምህር የሆኑትና ጥናቱን ካደረጉት ተመራማሪዎች አንዷ ሜሪ ኩሽማን። ይህም እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የማሰብ እና የማስታወስ ችግር እንደሚያስከትልባቸው ኩሽማን ገልጸዋል። “ኦ” የደም አይነት ተመራማሪዎች እንደሚሉት “ኦ” የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ጭንቀትን በሚጨምሩ ሁኔታዎች እንኳን ሰውነታቸው የደስታና ሀዘን ስሜትን የሚቆጣጠረው ኮርቲሶል ሆርሞን መጠን የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል። በዚህም ምክንያት በራስ ምታትና እንቅልፍ እጦት የመሰቃየት እድላቸው ዝቅተኛ ነው። ይህ የደም አይነት የራሱ መጥፎ ጎኖችም አሉት፤ በተለይም ወንዶች በከፍተኛ ደረጃ ክብደት እንዲጨምሩ የማድረግ እድል አለው።

ሴቶችም የሚያመርቷቸው አነስተኛ እና ጥራታቸው ዝቅተኛ የሆኑ የዘር እንቁላሎች የማርገዝ እድላቸው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል። ይህ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች በሆድ ህመም የመጠቃት እድል አላቸው። የደም አይነታቸው “ኤቢ” የሆኑ ሰዎች “ቢ” እና “ኦ” የደም አይነት ካላቸው ሰዎች ለሆድ ካንሰር ተጋላጭነታቸው በ26 በመቶ ይጨምራል። የአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ኢፒደሚዮሎጂ ጥናት እንደሚያሳየው “ኤ” የደም አይነት ያላቸው ሰዎችም ከ“ቢ” እና “ኦ” ጋር ሲነፃፀር ለሆድ ካንሰር የመጋለጥ እድላቸው በ20 በመቶ ከፍ ያለ ነው። በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው የደም አይነቶች እንዲሁም መልካም እና መጥፎ ገፅታዎቻቸውን መቀየር የሚቻል ባይመስልም፥ የኑሮ ዘይቤን ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጭንቀት አለማብዛት እና በየጊዜው የጤና ምርመራ ማድረግ ጤናችን ለመጠበቅ ይረዳሉ።

ምንጭ፦FBC

#የደምአይነቶች

753 views0 comments
bottom of page