top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ቀደምት ተመራማና ሳይንቲስት ጃቢር ኢብኑ ሀያንጃቢር ኢብኑ ሀያን የመካከለኛው ዘመን የኬሚስት ሊቁ ጀብር የሚባል ሲሆን “የኬሚስትሪ አባት” በመባል በስፋት ይታወቃል።

ሙሉ ስሙ አቡ ሙሣ ጃቢር ኢብኑ ሀያን የሆነው ጃቢር አልፎ አልፎ አል ሀራኒ እና አል ሱፊ በሚባሉ ስሞችም ይጠራል። ጃቢር አባቱ የመድሃኒት ቀማሚ (አጣር) ናቸው። ትክክለኛ የተወለደበትን ቀን ለማወቅ ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም እንደ አጠቃላይ ግን ጃቢር በ776 አካባቢ ኩፋ ውስጥ ህክምናን እና ኬሚስትሪን ያዘወትር እንደነበር በታሪክ አጥኚዎች መካከል ስምምነት አለ።

ጃቢር በኢማም ጃዕፈር አስ ሣዲቅ እና የኦማያድ ሠርወ መንግስት ልዑል በሆነው ኻሊድ ኢብኑ የዚድ ሥር ሆኖ ነው ትምህርቱን የተከታተለው። ህክምናን የተማረው ገና በልጅነቱ በባርማኪ ወዚር ቤት ሆኖ በአባሲድ አገዛዝ ኸሊፋ ሃሩን አር ረሺድ ዘመን ነበር። ለባርማኪስ መውደቅ የተወሰነ ሚና የነበረው ሲሆን በወቅቱም ምድር ቤት ውስጥ ታስሮ ነበር። ጃቢር የሞተው እ.ኤ.አ. በ803 ነው።

ማክስ ሜየርሃፍ (Max Mayerhaff) እንዳለውም በአውሮፓ የኬሚስትሪ እድገት በቀጥታ መመለሻው ጃቢር ኢብኑ ሀያን ነው ብሏል።

ጃቢር በኬሚስትሪ ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ወደ ዘመናዊው ኬሚስትሪ ለማደግ መሠረት የሆነውን ተግባር ተኮር (experimental investigation) የኬሚስትሪ ምርምርን ለዓለም ያሣወቀው እርሱ ነበር። እጅግ የታወቀው ላቦራቶሪው ፍርስራሹ ለዘመናት የቆየ ቢሆንም ነገር ግን ጃቢር እውቅናን የተጎናፀፈው በመቶ ትላልቅ ድርሰቶቹ ምክኒያት ነበር። ከነኚህም መካከል ሀያ ሁለቱ ከኬሚስትሪ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ለኬሚስትሪ መሠረት ከሆኑትና የሱ አስተዋፅኦ ከታከለባቸው ነገሮች መካከል የኬሚስትሪን ሣይንሣዊ ዘዴዎች በላቀ መልኩ ማሣደግ ሲሆን ማድረቅ (ክሪስታላይዜሽን)፣ ማጣራት (ዲስቲሌችን)፣ ማጠጠር (ካልሲኔሽን)፣ ማቅለጥ (ሰብሊሜሽን)፣ ማትነን (ኢቫፖሬሽን)፣ እና የተለያዩ ለዚሁ ምርምር የሚያግዙ ቁሣቁሦችን ያጠቃልላል። ያልጠሩ ሀሳቦች ተንሰራፍተው በሚገኙበት በዚያ ዘመን ኬሚስትሪ እንደ አንድ የሣይንስ ዘርፍ ሆኖ በዐረቦች ዘንድ በእጅጉ ተደራጅቶ ነበር። ኬሚስትሪ የሚለው ቃል የመጣውም “አል-ኪሚያ” ከሚለው የዐረብኛ ቃል ነው። ይህም በሙስሊም ተመራማሪዎች በሰፊው ጥናት ተደርጎበት ተሻሽሏል።

የጃቢር ተግባር ተኮር ምርምር ከፍተኛ ስኬት የነበሩት የተለያዩ ማዕድናትን እና ሌሎችን አሲዶችን ማግኘቱ ላይ ነበር። እነኚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በርሱ አለምቢክ (አለንቢቅ/alembic) የማጣሪያ መሣሪያ ውስጥ የተዘጋጁ ነበሩ። ለኬሚስትሪ መሠረታዊ ባህሪ በርካታ አስተዋፅኦዎችን ከማድረጉም በላይ አዳዲስ ውህዶችን (compounds) እና የኬሚካል አሠራር ዘዴዎችን እንዲሁም በርካታ ተግባር ተኮር የሆኑ ኬሚካላዊ ሂደቶችን (applied chemical processes) አጎልብቷል። በዚህም ሰፊ ሥራው የተነሣ በተግባር ተኮር ሣይንስ ዘረፍ መሪና ሞዴል ተጠቃሽ ለመሆን ችሏል። በዚሁ ዘርፍ ካስመዘገባቸው ስኬቶች መካከል የተለያዩ ብረታ ብረቶች ስለሚዘጋጁበት ሁኔታ፣ የሽቦ (steel) አሠራር፣ የልብስ አነካከር፣ የቆዳ አዘገጃጀት፣ ውሃ የማያስገቡ ልብሦችን ስለ መቀባት፣ በመስታወት ሥራ ማንጋኒዝ ዳይ ኦክሣይድን መጠቀም፣ ዝገትን መከላከል፣ በወርቅ መሙላት፣ ቀለማትን መለየት፣ ቅባቶች እና የመሣሰሉት ይጠቀሳሉ። በዚህ ረጅምና እልህ አስጨራሽ የተግባር ምርምር ወቅት ወርቅን ለማሟሟት የሚያስችል አኳራጂያ ማግኘት ችሏል። አለምቢክ የሱ ትልቅ ፈጠራ ሲሆን ይህም የማጣራትን ሥራ ቀላልና ስልታዊ በሆነ መልኩ እንዲሆን አድርጎታል። ጃቢር ከዚህም በላይ በተግባር ምርምሮችና በትክክለኛነታቸው (experimentation and accuracy) ላይ ትልቅ ትኩረት የመስጠትን መሠረት ጥሏል።

ጃቢር ከባህሪያቸው በመነሣት ንጥረ ነገሮችን (substances) በሦስት የተለያዩ አይነቶች ይከፍላቸዋል። የመጀመሪያው ሰፒሪት/መንፈስ ማለትም በሚሞቁበት ጊዜ የሚተኑት ሲሆኑ እነኚህም ካምፎር፣ አርሰኒክና አሞኒየም ክሎራይድን የመሣሰሉትን ይይዛል። ሁለተኛው ብረት ነኬ ሲሆን ይህም ወርቅን፣ ብርን፣ መዳብን፣ ሊድ እና ብረትን ያጠቃልላል። በሦስተኛው ምድብ ውስጥ ደግሞ ወደ ዱቄትነት/ብናኝነት የሚለወጡ ነገሮችን አስቀምጧል። ይህም ክፍፍል ኋላ ላይ ነገሮችን ብረት ነኬ (metals)፣ ብረት ነኬ ያልሆኑ (non-metals) እና በቀላሉ የሚተኑ (volatile) ተብለው ለተከፈሉበት ሁኔታ መሠረትን ጥሏል።

ጃቢር ምንም እንኳ በኬሚስትነቱ ቢታወቅም እንደ አልኬሚያ ባለሙያ ግን ምናባዊ የተከበሩ ማእድናት አዘጋጃጀት ለይ ትኩረት አድርጎ የተንቀሣቀሠ አይመስልም። ባይሆን ትልቁን ጉልበቱንና ጊዜውን የጨረሠው መሠረታዊ የሆኑ ኬሚካለዊ አሠራሮች አንዴት እንደሚያድጉና በኬሚካል ፅግበራ (chemical reactions) ዙሪያ ነበር። በዚህም የኬሚስትሪ ሣይንስ ከአልኬሚ ምናባዊ እንቆቅልሽ ጎልብቶ ይወጣ ዘንድ ረድቷል። በኬሚካላዊ ፅግበራ በርካታ የተለያዩ ውጤቶች ሊገኙ እንደሚችሉ አፅንኦት ሠጥቷል። በዚህም የተነሣ የኮንስታንት ፕሮፖርሽን ህግ (the law of constant proportions) የማግኘቱ መንገድ ቀላል ሊሆን ችሏል።

በጃቢር የፅሁፍ ክምችት ውስጥ በርካታ የመፅሃፍ ቅጂዎች ተካተዋል። ከኬሚስትሪ በተጨማሪ ለህክምና እና ለሥነ ከዋክብት ጥናትም የጃቢር አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በኬሚስትሪ ዙሪያ ከሚጠቀሱ መፅሃፎች መካከል “ኪታብ አል-ኪሚያ” እና “ኪታብ አስ-ሰቢኢን” ይጠቀሳሉ። መፅሃፎቹም ወደ ላቲን እና በርካታ የአውሮፓ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። እነኚህም ትርጉሞች በአውሮፓ ውስጥ ለክፍለ ዘመናት ገነው የቆዩ ሲሆን ዘመናዊዉ ኬሚስትሪ መከሠትም አቢይ ምክኒያት ነበሩ። ጃቢር ይጠቀምባቸው የነበሩና የዛሬው የአውሮፓውያኑ ቋንቋዎች የሚጠቀሙባቸው አልካሊ (alkali) እና የመሣሠሉት በርካታ ከምርምሩ ጋር የተያያዙ ቃላት የሳይንስ መዝገበ ቃላት ክፍል ሊሆኑ ችለዋል። ከመፅሃፎቹ ታርመው ለህትመት የበቁት የተወሰኑት ብቻ ሲሆኑ በርከት ያሉትና በዐረቢኛ ቋንቋ የተፃፉት ግን ዛሬም ድረስ ትኩረት ተነፍጎአቸው ሣይታተሙ ተቀምጠዋል።

በሱ የፅሁፍ ክምችት ውስጥ ሁሉም የሱ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ስለመካተታቸው ጥያቄ ያለ ሲሆን ክምችቶቹም የሱ ስብስቦች ብቻ ናቸው ወይንስ ኋላ ላይ የመጡ ተከታዮቹ ትንታኔ ተካቶባቸዋል የሚል ጥያቄም አለ። እንደ ሣርቶን (Sarton) አባባል ከሆነ የሱ ሥራዎች ስለመሆናቸው ልናረጋግጥ የምንችለው ሁሉም መፅሃፎቹ የታረሙና የታተሙ እንደሆነ ብቻ ነው። በፅሁፉ ውስጥ የተካተተው ሃይማኖታዊ አመለካከቱና የፍልስፍና ጭብጡ ምንም እንኳ ትችት የገጠመው ቢሆንም ስለ ትክክለኛታቸው የሚነሣው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ሊካድ የማይችል ሀቅ ቢኖር ጃቢር በዋናነት ለሃይማኖቱ ሳይሆን ለኬሚስትሪ ሣይንስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ መሆኑን ነው።

በርካታ ግኝቶቹ ለምሣሌ አሲድ ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘቱ በተለይ ናይትሪክ፣ ሃይድሮ ክሎሪክ፣ ሲትሪክ፣ እና ታርታሪክ አሲድ እና ስልታዊ ሙከራዎቹ እጅግ የተዋጣላቸው ነበሩ። ይህም በመሆኑ ነው ይህ ሰው የዘመናዊው ኬሚስትሪ አባት (father of modern chemistry) ተብሎ ሊታይ የቻለው። ማክስ ሜየርሃፍ (Max Mayerhaff) እንዳለውም በአውሮፓ የኬሚስትሪ እድገት በቀጥታ መመለሻው ጃቢር ኢብኑ ሀያን ነው ብሏል።

ምንጭ - ኢትዮ ሙሰስሊም ድረ ገጽ

48 views0 comments
bottom of page