top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

‘‘ የሰው ዓመል ዘጠኝ’’ ‘‘ይዛብራል’’ ፣ ቀዥበርባራው  ወንዝ



እንዴት ናችሁሳ?

ዛሬ የመረረ እና ያመረረ ጫወታ አለኝ ፡፡

በቅድሚያ የደኢህዴን ሊቀ መንበር ስለሆኑት ክብርት ፣ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል- የማውቀውን አንድ ነገር ፡፡

ደኢህዴን በመደበኛ ጉባኤው አሰፈፃሚውንና ማዕከላዊ ኮሚቴውን በመረጠበት ያለፈ ወቅት ነው ፡፡ ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካለል የጉባኤው ተሳታፊዎችን ህጋዊነት አስመልክቶ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡

ጭቅጭቁ ከሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ከመጡት ተወካይ ተሳታፊዎች መካከል ፣ ህጋዊ የሚያደርገውን የተሳትፎ መንገድ ባልተከተለ መንገድ አንድ ሰው ጉባዔውን ተቀላቅሏል የሚል መነሻ ነበረው ፡፡ ይኸውም በጉባዔው ላይ እዲሳተፍ የተመረጠው ሰው ቀርቶ በምትኩ ሌላ ሰው ገብቷል ተባለ፡፡

የተመረጠው ሰው ቀርቶ በምትኩ ጉባዔው ላይ እንዴት ሊገኝ ቻለ? ጥያቄ ተነሳ ፡፡

በህጋዊ መንገድ ፣ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ በተከተለ መንገድ በጉባኤው ላይ እንዲሳተፍ የተመረጠው ሰው በሰጠው ውክልና ምክንያት ነው ፣ የዞኑ ድርጅት ፅ/ቤት ሀላፊ ፣ የማይመለከተው ሰው ጉባኤው ላይ የተገኘው ፡፡ የጥያቄው ምላሽ ሆነ ፡፡ ይሄ የፅ/ቤት ሀላፊ ተብዬው፣ ሰውየውን በሾኬ ብሎ አስቀርቶት ቢሆንስ? ስልጣን ለህዝብ ብልፅግና ጥቅም ላይ የሚውል መሳሪያነቱን እየሳቱ የሾኬ እግር የሚያደርጉት አሉ፡፡ ጉድኮ ነው፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ ’’ ፣ ይላል- ጭንቄሶ፡፡

ጉድኮ ነው! በወቅቱ አንዳንዶቹ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ፣ መድረኩን ጭምር የያዙት ፣ የሰውየው መገኘት ችግር የለውም አሉ፡፡

‘‘ አኣይ እንዲህማ አይሆንም! ’’ ፣ የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ድምፁ የክብርት ሙፈሪያት ካሚል ነው ፡፡ ክብርቷ፣ ‘‘የድርጅቱ ህግና ደንብ አይፈቅድም ! ስለዚህ ግለሰቡ የጉባዔው አባል መሆን አይችሉም! ’’ ፣ሲሉ ውዝግቡን አቀዘቀዙት፡፡

ከኖርማል ከፍ ያለው የጉባዔው ‘‘ ቴምሬቸር’’ ፣ ወደነበረበት ተመለሰ፡፡ ኣኻ እሳቸው ባይገላግሉንኮ የኢዲሞክራሲያዊነት ግለት ፈጅቶን ነበር፡፡

ትልቅ ሰው -ክብርቷ፡፡ የህግ የበላይነት ይጠበቅ ያሉ ፣ ደጋግመው ይንገሱ!!

ስለ ድርጅቱ ምክትል ሊቀ- መንበርም - ስለ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፡፡ ክቡሩ ጋር በስራ ጉዳይ ተመላልሻለሁ፡፡ እነሆ ስለርሳቸው ከሶስት ዓመት በፊት ባሰተምኩት አንድ መፅሐፍ ምስጋና ገፄ ላይ የሰፈረው፡-

‘‘ ሁሌም ለስራ ጉዳይ ወደ ቢሮህ ጎራ ባልን ቁጥር ታናሽ ንሆን ከታላቅነት ወንበርህ ተነስተህ በፈገግታ የምትቀበለን አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ …. ’’ እያለ ይቀጥላል፡፡

ያኔ የፃፍኩት አውነት ነው - ማሪያምን ! ካላመናችሁ መፅሐፉን ፈልጉና ገዝታችሁ አንብቡ!

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ በስልክ ያጫወተኝ ነገር አለ፡፡ አንድ ወንዝ አለ- ጎጃምንና ጎንደርን የሚለይ ፡፡ የጎጃምና የጎንደር አርሷደሮች፤ ወንዙ ወደ ጎጃም አቅጣጫ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ጎንደር አቅጣጫ ወሰኑን እየሰበረ ይፈሳል፡፡ ይሄኔ አርሷደሮቹ ወንዙን፣ ‘‘ ይሄ ወንዝ ምን ይዛብራል? ! ’’ ፣ያቀዣብራል ፣ አሉት አለኝ፣ ወዳጄ፡፡

ደኢህዴን ውስጥ እንደጉጃሙና ጎንደር ወሰን መለያው ወንዝ ፣ ‘‘ የሚዛብር ካድሬና አመራር ’’ ፣ ለውጡን ማቀላጠፍ ፈተና የሚሆንባቸው ይመስለኛል ፡፡ ‘‘ አንተ የሴጣን ወፍጮ ’’ ፣ ሆነናል ያልከው ሰውዬ አባባልህ እንዴት ይመቻልሳ!

አሁንስ እንዴት ነው? ወፍጮው እንደቀድሞው ጥሬ ጎርሶ ዱቄት የማይተፋ እንደሆነ ፣ በሴጣን ወፍጮነቱ ቀጥሏል ወይስ?...

አሁን እንቁጣጣሽ እየመጣ ነው ፡፡ እንዴት ነው በዚህ ዓመት- ባልም ወደ አንዳንድ የክልሉ ባለስልጣናት ቤት በነፍስ ወከፍ የሚገባው ያመትባል ግማሽ የበሬ ስጋ ይኖራል እንዴ? ይሄ ነገር ካለ ፣ ከግማሽ ጎኑ ለኔም የበዓል መዋያ ሁለት ሙዳ ስጋ፡፡ በማርያም !!

የበሬ ጎን ስጋ!!? መቼም በልተን እንጨርሰዋለን ካላችሁ ሆዳችሁ ውስጥ ምን ቢኖር ነው ? ገምቶ ከሚወረወር ግን ሁለት ሙዳ ስጋ -ለኔ ብትጡልልኝ ብዬ ነው ፡፡

ኧረ! አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ወዳጆቼ የነገሩኝም ሌላ ገራሚ ነገር አለ፡፡ ለማንም እንዳትናገሩ!!! ታስበሉኛላችሁ!!

አንዳንድ ትላልቅ ሆቴሎች ወደ ባለስልጣናት ቤት ብፌ ለዓመት በዓል ደግሰው ይወስዳሉ አሉ፡፡ አጋፋሪነት ዘምኗልሳ!! ኧረ በማርያም ለኔም በንቁጣጣሽ!! ብፌው ቀርቶ አንድ ሳህን እንጀራ በቀይ ወጥ ንፋስ እየመታው ይዛችሁልኝ ኑ፡፡ በማርያም!!

የደኢህዴን ጉባዔ እየቀረበ ነው ፡፡ ክበርት ፣ እርሶም ክቡር ፣ እነዚህ በየጉባዔው የሚታዩት አንዳንድ አጓጉል ልማዶች ይቀጥላሉ ፣ ወይስ ይቃጠላሉ?

አንድ ሚስጠር አዋቂ ወዳጄ እንደነገረኝ ፡፡ ተሳታፊዎቹ ከሚያነሷቸው የአጉል ልማድ ጥያቄዎች መካከል፡-

1. ለምንድነው ለነገሌ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ማረፊያ ሰዘጋጅ ፣ ለኔ በለ 3 ?

2. ለኔ የተዘጋጀው የባህል ኮት ደረጃው ያነሰ ነው ፡፡ በምን አንሼ ነው?....ልኬ አይደለም በልኬ ይሰፋልኝ የሚሉም አሉ ተብያለሁ፡፡

እንዴት ነው ነገሩ? ቁምጣ ከሚለብስ አርሷደር በተዋጣ ገንዘብ ኮት ማማረጥ፡፡ መብላትና ማደር ፈተና ከሆነበት ሲቪል ሰርቫንት በተዋጣ ገንዘብ ኮት በፕሮቫ ካልሆነ ማለት፡፡ አሁን በቅርቡ በሚካሄደው ጉባኤ ላይስ ውድ ውድ ኮት ይኖራል እንዴ?

ለነገሩ ይቺ ምን አላት ?ያሰገረመኝ ሌላ አለ፡፡

‘‘ ሩም ሰርቪስ ’’

ባለ ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ እረፍት አርጉ ለተባሉት ሰዎች ቁርስ፣ ምሳና እራት ፣ እንዲሁም የማወራረጃ ፈሳሽ ይዘጋጃል፡፡ እነርሱ ግን ሩም ሰርቪስ ይጠይቃሉ፡፡ ማለት ከተፈቀደው ውጪ ወደ ክፍላቸው ሌላ ዕራት ፣ ሌላ መጠጥ (ውድ ውድ የሆኑ ውስኪዎችን ይጨምራል) ያዛሉ ፣ አለኝ ፡፡ ኧረ አልተፈቀደም ቢሏቸውም እንኳ መስሚያ የላቸውም፡፡ ጆሮ የሌለው ጉባዔተኛ ምን ያደርጋል? ትርፍ የለውም ፡፡ የስኮትላንድ ውስኪዎችን እያማረጠ አምጡልኝ የሚል ከሆነ ወጪ እንጂ ምን ትርፍ አለው ? ሩም ሰርቪስ ይቀጥላል ወይስ ስልጣኑን ይለቃል?

ከርሷደር የተሰበሰበ መዋጮን ምነው እንደጠላት ገንዘብ ፣ ብትን ብትን ፡፡ ምነው እንደዚህ ብትንትንትን?

አሁን በዚህኛው ጉባዔም ለቲሸርት፣ ለኮፍያ፣ ለውድ ኮት … ብትን ፣ በትን አለ እንዴ?

እኔ 'ምለው ፣ ክብርትና ክቡር ያ ልማድ አሁንም ይቀጥላል እንዴ? ሳስበው በናንተ ዘመን ይሄ የሚፈቀድ አይመስለኝም፡፡ ክቡራን ፤ የዓመትባል፣ የሩም ሰርቪስ ፣ የቲሸርት ፣ የኮፍያ፣ የኮት ፣ የምናምን ፣ የምናምን ‘‘ ቴምፕሬቸር’’ በጣም ከፍ ብሎ ‘‘ ፋታል’’ ሀኗል፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ ! ’’ ፣ ይላል - ጭንቄሶ፡፡

ይህን አልክ ብላችሁ አንዳንዶች ፣ ‘‘ ከቀጭን እንጀራዬ ’’ ፣ ሂድ! እንዳትሉኝ፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ!! ’’´፣ ይላል - ጭንቄሶ፡፡

‘‘የሰው አመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ ! ’’


36 views0 comments
bottom of page