top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ኢብኑ ነፊስ (1213-1288 እ.ኤ.አ)ዐላእ አድ-ዲን አቡ አል ሀሠን ዓሊ ኢብኑ አቢ አል ሀዝም አል ቀርሺ አል ደመሽቂ አልሚስሪ ይባላል፡፡ የተወለደው እ.ኤ.አ በ607 በደማስቆ ከተማ ነው፡፡ ትምህርቱንም የተማረው በኑረዲን አዝ-ዘንኪ በተመሠረተው የህክምና ኮሌጅ ሆስፒታል ነው፡፡ በህክምናው ትምህርት ዙሪያ መምህሩ የነበረው ሙሀዘብ አድ ዲን አብዱል ረሂም ሲሆን ከህክምናው ትምህርት ሌላ ኢብኑ ነፊስ የህግ ትምህርትን፣ የሥነ-ፅሁፍንና ሥነ-መለኮትን ትምህርት ተከታትሏል፡፡

በፊቅሂ እውቀትም በሻፊዒይ መዝሀብ እውቀቱ የበቃ (ኤክስፐርት) ሲሆን የታወቀ ሃኪምም ነበር፡፡

በህክምናና በህግ እውቀት ከፍተኛ ትምህርት ካገኘ በኋላ ወደ ካይሮ በመጓዝ በታዋቂው ናስሪ ሆስፒታል በዋና ሥራ አስኪያጅነት የተሾመ ሲሆን እዚያም ሣለ ለታዋቂው የቀዶ ጥገና ባለሙያ ኢብኑ አል ቁፍ አል መሲሂን ጨምሮ ለበርካታ የህክምና ጠበብቶች ሥልጠና ሠጥቷል። ከዚህም ሌላ በካይሮ በሚገኘው መንሱሪያ ትምህርት ቤት ግልጋሎት ሠጥቷል፡፡ የሞተውም እ.ኤ.አ በ678 ሲሆን የግል ቤቱን፣ ቤተ-መፅሃፍቱንና ክሊኒኩን ለመንሱሪያ ሆስፒታል በስጦታነት አበርክቷል፡፡

የኢብኑ አን-ነፊስ ዋነኛ አስተዋፅኦዎቹ በህክምና ዙሪያ ያተኮሩ ናቸው፡፡ አቀራረቦቹም በቀደሙት ሥራዎች ላይ ዝርዝር አስተያየቶች መፃፍን፣ እነሱን በጥልቀት መመርመርንና የራሱን ወጥ የሆኑ አስተዋፅኦዎች መጨመርን ያካትታሉ፡፡ ጉልህ ተፅእኖ ከነበራቸው ትላልቅ ወጥ ሥራዎቹ መካከል ከሦስት ምእተ አመታት በኋላ በዘመናዊው ሣይንስ እንደገና የተደረሠበት የደም ዝውውርን ማግኘቱ ይጠቀሳል፡፡ ሣንባ ውስጥ የሚገኙትን ነገሮች በትክክል ለመግለፅ የመጀመሪያው ሰው ሲሆን ስለ ብሮንካይ ምንነት፣ በሰው ልጅ የደም ቱቦዎችና በአየርና በደም መካከል ስለሚከሠተው አጠቃላይ ሁኔታ በዝርዝር አስፍሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልብ ላይ የሚገኘውን የኮሮናሪ አርተሪን (ልብ ላይ የሚገኝ የደም ሥር) ጥቅም በመግለፅ የልብ ጡንቻዎችን የሚመግብበትን ሁኔታ ተንትኗል፡፡

አሽ-ሻሚላ ፊ አጥ-ጢብ የሚባለው ባለ ብዙ ጥራዝ መፅሃፉ ሦስት መቶ ክፍሎችን ሊይዝ የሚችል እንሣክሎፒዲያ ተደርጎ የተቀረፀ ሲሆን በመሞቱ ምክኒያት ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡ የእጅ ፅሁፎቹ ግን ዛሬም ድረስ በደማስቆ ይገኛሉ፡፡ በአይን ህክምና ዙሪያ የተፃፈው መፅሃፉ ወጥ የሆነ የራሱ አስተዋፅኦው ሲሆን ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ነገር ግን እጅግ ሊታወቅ የቻለው መፅሃፉ ሙጃዝ አልቃኑን የሚባለው ሲሆን በሱ ዙሪያ በርካታ ማብራሪዎችም ተፅፈዋል፡፡ ከሱ ማብራሪያዎች መካከል አንዱ በሂፖክራተስ መፅሃፍ ላይ የጻፈው ነው፡፡ የኢብኑ ሲናን ቃኑን አስመልክቶ ዛሬም ድረስ ያሉ በርካታ ጥራዞችን ፅፏል፡፡ እንደዚሁም በሁነይን ኢብኑ ኢስሃቅ መፅሃፍ ላይም ማብራሪያ ፅፏል፡፡ ሌላው ታዋቂውና የሱ ወጥ ጥንቅር አስተዋፅኦ የሆነው መፅሃፍ ምግብ በጤና ላይ ስለሚያሣድረው ተፅእኖ የሚዳስሰው ኪታብ አልሙኽታር ፊ አል አግዚያ የሚባለው ነው፡፡

የኢብኑ አን-ነፊስ ሥራዎች በያኔውን ዘመን የነበረውን እውቀት በእጅጉ ከመዋሃዳቸውም በላይ አበልፅገውታልም፡፡ ከዚህም ባለፈ መልኩ በምሥራቁም ሆነ በምእራቡ ዓለም በነበረው በያኔው የህክምና ሣይንስ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም ከመፅሃፎቹ መካከል አንደኛው ብቻ ነው ወደ ላቲን የተተረጎመው፡፡ በመሆኑም ከፊል ሥራዎቹ ለአውሮፓ ሣይታወቁ ለረጅም ዘመናት ኖረዋል፡፡

ምንጭ EM ድረ ገጽ


12 views0 comments
bottom of page