top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ’’ - ሙገሳን ሳይሆን ስድብን ያሳደገ ቋንቋ



እንዴት ይዟችኋል-ክረምቱ? እኛም አለን! እንዳለን አለን!

ዛሬ በኢትየጵያ ስነ-ፅሑፍ ታሪክ ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳውን ፣ ትልቅ ሰው፣ እቀሰቅሳለሁ፡፡ ሰውየው ደበበ ሰይፉነው ፡፡ የዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጥናጥና ምርምር ኢንሰቲቲዩት መስራች፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ቲያትር ዲፓርትመንት ተጠሪ፣ ምምህር ፣ ተመራማሪ፣ አዳዲስ የአማርኛ ቃላቶች ፈልሳሚ፡፡

ደበበ ሰይፉ የቲያትር ዲፓርትመንት ተጠሪ ሆኖ ባገለገለበት ዘመን ነው ፡፡ በዲፓርትመንቱ ተማሪዎች መካከል ጭቅጭቅ ተነሳ ፡፡ ጭቅጭቁ ነደደ ፡፡ ለጭቅጭቁ መለኮስ ምክንያት የሆነችው በዲፓርትመንቱ ውስጥ መመምህርት የነበረቸው ሴት ፣ ጂና ፣ ነች፡፡ መምህርቷ ሩሲያዊት ነች፡፡

ንትርክ ያለምክንያት ፣ ተቃውሞ ያለሰበብ አይቀሰቀስም፡፡ በርግጥ እኛ ሀገር የችግሮች ምክንያት ግምት ውስጥ አይገባም፡፡ ለውጤቱ እንጂ ለምክንያቱ ቦታ አንሰጥም ፡፡ ግንኮ ውጤቶች የሚቀየሩት ምክንያቶቹ ሲቀየሩ ነው፡፡

በወቅቱ የቲያተር ዲፓርትመንቱ ተማሪ የነበረች አንዲት ቆንጆ ነበረች፡፡ ይህችን ተማሪ አበውረዋት ይማሩ የነበሩ ጓደኞቿ አይዘነጓትም፡፡ ጂና ዘጠኝ ኮርሶች አካባቢ ሰጥታ ዘጠኙንም ‘‘ ኤ’’ ብላታለች፡፡

ተቃውሞውንም የቀሰቀሰው ይኸው ጉዳይ ነው ፡፡ ተማሪዋ ዘጠኙንም ኮርሶች ያገኘቸው በችሎታዋ ሳይሆን ሩስኪኛ ስለምትናገርና በዚሁ ምክንያት ከጂና ጋር ባላት ተግባቦትና ያልተገባ ግንኙነት ነው አሉ፡፡

ሄዱ ወደ ዲፓርትመንቱ ተጠሪ- ደበበ ሰይፉ ጋ፡፡ ክሱን በጥሞና ሰማ- ደቤ፡፡ከዚያም ተማሪዎቹን በሙሉ አስከትሎ ወደ መማሪያ ክፍላቸው ተመለሰ፡፡

ክፍል ከገቡ በኋላ በሉ ቁጭ በሉ አላቸው- ተማሪዎቹን፡፡ አስከተለና ከተማሪዎቹ መካከል ውበትና ቁንጅና የደፋባትን ተማሪ ‘‘ እስኪ ነይ ወዲህ ? ’’ ፣አላት፡፡

ተማሪዋ ወጣችና ጓደኞቿ ፊት ቆመች፡፡

አሁንም አንዱን ወንድ ተማሪውን ፣ ‘‘አንተም ና ወዲህ! ’’´፣ አለው ፡፡

ወጥቶ ገኗ ቆመ፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ !’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ፡፡

ወንዱን ተማሪ በል የዚችን ቆንጆ ውበት እፈስ አለው ፡፡ ማለቴ አድንቃት ሲል አዘዘው ፡፡

ተማሪው እንዲህ ያለ ይመስለኛል፡-

‘‘ አንቺ የውበት ጉልላቱ፣ የቁንጅና ጥጉ፣ የኣኖችህ ብርሀን ከዋክብትን ያስናቁ፣ጉንጮችሽ የትኩስ ደም ጋኖቹ፣ መዓዛሽም አልባቡ፣ እርምጃሽ ምጥኑ….’’

ነገር ግን እያሞገሳት ቡዙ አልዘለቀም፡፡ የቃላት ድርቅ እየመታው ፣ ሄደ ሄደና በስተመጨረሻ ልክ ነዳጅ እንደጨረሰ ሞተር ተንተፋተፈና አንደበቱ ፀጥ አለ፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ !’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ፡፡

ደበበ ሰይፉ ትልቅ ሰው!!! የዘመን ዕሳት አቃጥሎት ፣ ተናዶ እየነደደ የጠፋ ጧፍ!!!

ደበበ ሰይፉ እንደገና ወጣቱን ፡፡ በል እንዳሞገስካት ሁሉ አንኳሳት ሲል አዘዘው!

ወጣቱ፡-

‘‘ አንቺ ዘልዛላ! ውዳቂ- የውድቀት አዘቅት ! ልበ ድፍን ፤ ፍቅር የማይገባሽ! ከማሰቢያሽ ይልቅ ሆድሽን ያሰፋሽ፡፡ አመለጭላጭ ሳሙና! ድብዳብ የአህያ ቆዳ! የጫማ ስር ጭቃ-እርጋጭ ፣ ተራጋጭ !!.... ’’ ፣ አዘነበው የስድብ ዶፉን፡፡

‘‘ሂድ እንግዲህ!’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ፡፡

ከሙገሳው ይልቅ ለስድቡ ልጁ ጉልበቱ ሲበረታና ፣ ማቆሚያ ጠፍቶት ተረረረር ሲል፣ ደቤ ፣‘‘በቃህ ፣ በቃህ፣ በቃህ፣ይበቃኛል !’’ ፣አለው፡፡ አስገድዶ አስቆመው ፡፡

ከዚህ በኋላ ይንን ተናገረ፡-

​‘‘ ጂና ስህተት ሰርታ ሊሆን ይችላል! ከዛ ባሻገር እኛም ጋ ችግር አለ፡፡ አያችሁ አደል ! ቋንቋችን ከሙገሳ ይልቅ ለሰድብና ለኩሳሴ እጅግ ቢዙ ቃላት አሉት ፡፡ ’’

ደበበ ሰይፉ ትልቅ ሰው !! እጅግ ትልቅ ሰው!!!!

ይህ ልሂቅ ፣ እጅግ ትልቅ ሰው ፤ አህአዴግ ፣ደርግ ራሱን ጥሎ ሲገባ የኢሠፓ አባል ነህ ተብሎ ከሌሎች 39 የዩንቨርሲቲው መምህራን ጋር ከስራ ተባረረ፡፡

የኢሠፓ አባል ነህ ስለተባለበት ጉዳይ ፡፡ ሰወየው የኢሠፓ አባል የነበረው ግን በዕምነት ሳይሆን በፍርሀት ስለመሆኑ ከመባረሩ በፊት ለተማሪዎቹ ነግሯቸው ነበር፡፡ እንደዚህ ነው፡-

አንድ ዕለት ለተማሪዎቹ የዕለቱን ትምህርት ካስተማራቸው በኋላ ፣ ‘‘ ነገ ከሰዓት በኋላ ሜካፕ ክላስ አለ ፡፡ እንድትመጡ !’’ ፣ አላቸው፡፡

ተማሪዎቹ ሳቁ!! በሳቀቸው ጩኸት ክፍሏን አንቀጠቀጧት!! ተንቀጥቅጣ አለመፍረሷ አትሉም!

ደገመና ፣‘‘ልጆች እመኑኝ ! እንደሌላ ጊዜ ቀጥሬያችሁ አልቀርም! እመጣለሁ ’’ አላቸው፡፡

እነሱም ደገሙት - ያን ሳቃቸውን፡፡

ይሄኔ ደበበ ሰይፉ ፣ ‘‘ካልመጣሁም እንኳንም አልመጣሁ!! ከናንተ በላይ እነሱን እፈራቸዋለሁ ’’ ፣ ሲል ተናገራቸው፡፡

‘‘ ሂድ እንግዲህ ! ’’ ፣ ይላል -ጭንቄሶ፡፡

‘‘ እነሱ ’’ ፣ እነማናቸው? ጉድ እኮ ነው! እነሱ ናቸዋ! ፀረ -ተራማጅ ፣ ፀረ- አብዮተኛ ፣ ፀረ- ሠርቷደር ፣ፀረ- ሶሻሊስት ፣ ፀረ- ኮሚኒስት ፣ አብየት ቀልባሽ፣ ወላዋና አታላይ ….ምናምን እያሉ እስር ቤት የሚዶሎቱ ፡፡ አዎ እነሱን ነው ሳያምን እያሰደገደጉ ከሠዓት በኋላ ወደቢሯቸው የመጠሩን እፈራቸዋለሁ ያለው ፡፡

ምንዋጋለው ! ያኛው አስፈራርቶ ገዢ ፣ ይሄኛውም ፈርጆ አባራሪ ሆኑበት ፡፡ ምስኪን ሰው ፡፡ ሰውየው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረረበት ከ1985 ህይወቱ እስካለፈበት አስከ 1992 ዓ.ም በራሱ ላይ በር ዘግቶ ፣ ከሰው ጋር መገኛኘትን ተጠይፎ ፣ በራሱም ነዲድ ጭመር ነዶና ተናዶ አለፈ፡፡ ምስኪን ሰው፡፡

ልጅነቱን በማር ጣፋጭነት ያሳለፈባት ይርጋለም ከተማ አፅሙን በሆዷ ተሸክማ እነሆ ትኖራለች፡፡ ከአፅሙ በላይ በቆመ ሀውልቱ ላይ ተከታዩ ግጥም ተፅፎ ይነበባል፡-

ለምን ሞተ ቢሉ

ብላችሁ ንገሩ

ሳትደብቁ ከቶ

ከዘመን ተኳርፎ

ከዘመን ተጣልቶ፡፡

(ከመፅሐፉ ተወስዶ ሀውልቱ ላይ የሰፈረ ግጥሙ)

ትልቅ ሰው ደበበ!! ህመሙን ፣ የዓመታት ብስችቱን የሰደረባቸው ውስጥ ስድብ የለም እኮ፡፡

እጅግ ትልቅ ሰው፣ ያስተማረውን የኖረ፡፡ ኖሮ ያለፈ ተወርዋሪ ኮከብ፡፡

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’


39 views0 comments
bottom of page