top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የዲስክ መንሸራተት“የዲስክ መንሸራተት ሁሉ ችግር አይደለም” – ዶ/ር ኃይሉ ሰይፉ – የፊዚዮቴራፒ ሐኪም

በተለምዶ የዲስክ መንሸራተት ተብሎ የሚጠራው የአጥንት ህመም ብዙም ትኩረት ካልተሰጣቸው የአጥንት ህመሞች መካከል አንዱ ነው። ይህን ችግር በተመለከተ ባለሞያ አነጋግረናል። ባለሞያው ዶክተር ኃይሉ ሰይፉ ይባላሉ።

ዶክተር ኃይሉ በሞያቸው የፊዚዮቴራፒ ሀኪም ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅትም በቅዱስ ጳውሎስ ህክምና ኮሌጅ ሌክቸረር ናቸው። በተጨማሪም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ድሮጋ ፊዚዮቴራፒ ክሊኒክ በፊዚዮቴራፒ ሀኪምነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሞያ ላለፉት 11 ዓመታት ያገለገሉት ዶ/ር ኃይሉ፤ በሀገራችን ከሚገኙ ጥቂት የፊዚዮቴራፒ ሀኪሞች መካከል አንዱ ናቸው።

ጥያቄ፡- ዲስክ ምንድነው? ከሚባለው ብንጀምር ጥሩ ነው። በሰውነት ውስጥ የሚገኘው ዲስክ ምንድን ነው? ጠቀሜታውስ? ዶ/ር ኃይሉ፡- ዲስክ ማለት ጠፍጣፋ ነገር ማለት ነው። በሰውነት ውስጥ ያለው ዲስክ በእያንዳንዱ የጀርባ ወይም የአከርካሪ አጥንት መካከል የሚገኝ ክፍል ነው። ዲስክ በተፈጥሮው ከውጭ በኩል ሽፋን ያለው ሲሆን፤ በሽፋኑ ውስጥ ደግሞ ሁለት አይነት ፈሳሾች አሉ። አንደኛው ፈሳሽ ላላ ያለ እና እንደ ጄል ያለ (ዝልግልግ) ፈሳሽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ እንቁላል አስኳል ጠንከር ያለ ፈሳሽ ነው። ጥንካሬው ከአስኳል ጋር የሚነፃፀር ሳይሆን አቀማመጡ እንደዚያ ስለሆነ ነው። ይሄ ጠንከር ያለው ፈሳሽ ወደ ውስጥ (መካከል) ላይ የሚገኝ ነው። ይሄ ዲስክ የተሰራበት አላማም የአከርካሪ አጥንቶች እርስ በርሳቸው እንዳይገናኙ ለማድረግ ነው። በዚህም አጥንቶቹ እንዳይጋጩ የማድረግ እንዲሁም መሬት ስንረግጥ የመሬቱ ግፊት ወደ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ቀንሶ የማሳለፍ ጠቀሜታ አለው።

አንድ ሰው ስንት ዲስኮች አሉት የሚለውን ስንመለከት የሰው ልጅ ሰባት የአንገት አጥንቶች አሉት። በእነዚህ አጥንቶች መካከል ከሁለተኛው አጥንት ጀምሮ ዲስክ ይገኛል። በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የአንገት አጥንት መካከል ዲስክ የለም። ከዚያ በታች ባሉት መካከል ግን አለ። ደረት ላይ ደግሞ 12 አጥንቶች አሉን። በእነዚህ ሁሉም አጥንቶች መካከልም ዲስኮች አሉ። በታችኛው ወገብ ክፍልም አምስት የጀርባ አጥንቶች ያሉ ሲሆን፤ በእያንዳንዳቸው መካከል ዲስክ አለ። እነዚህ ዲስኮች ከላይ ወደ ታች እየወረዱ ሲሄዱ መጠናቸው እየጨመረ ነው የሚሄደው።

የሚሸከመው ነገር እየጨመረ ሲሄድ መጠኑም ይጨምራል። በሁለተኛው እና በሶስተኛው የአንገት አጥንት መካከል ያለው ዲስክ የሚሸከመው ጭንቅላትን ብቻ ስለሆነ መጠኑ አነስተኛ ነው። ወደ ደረት ስንመጣ ደግሞ ሸክሙም ብዙ ስለሆነ መጠኑ ይጨምራል። በታችኛው የወገብ ክፍል ያለው ዲስክ ደግሞ ከዚህ በመጠኑ ከፍ ይላል። ስለዚህ ስለ ዲስክ ሲነሳ ስለ አንድ ክፍል ሳይሆን ስለሁሉም ዲስኮች ነው የሚነሳው።

ጥያቄ፡- ዲስክ ይሄ ከሆነ የዲስክ መንሸራተት የሚባለው ምንድን ነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- በህክምናው ዲስክ ተንሸራተተ የሚለው ብዙም ጥቅም ላይ አይውልም። ይልቁንም ዲስኩ አበጠ ወይም ፈነዳ ነው የሚባለው። ችግሩ የዲስክ ማበጥ፣ መፈንዳት ወይም መድረቅ ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው ችግር መካከል ላይ ያለው እና ጠንካራው የዲስክ አካል ወደሆነ አቅጣጫ ማበጥ ነው። ይህ ፈሳሽ ወደ አንድ ወገን ወጥቶ ወደቦታው መመለስ ሲያቅተውና አብጦ ሲቀር ዲስኩ አበጠ ወይም ተወጠረ ይባላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሁለቱን ፈሳሾች የያዘው ሽፋን ሙሉ ለሙሉ ተበጥሶ ደረቁ ፈሳሽ ወደ ውጭ ሲፈስ ዲስኩ ፈሰሰ ወይም ፈረጠ ይባላል። መንሸራተት የሚለው ቃል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ነው የሚመስለው። ነገር ግን ዲስክ ከቦታው ወደ ሌላ ቦታ ሸርተት የሚል ሳይሆን ያቺ የተሸፈነችው ነገር በጭነት ምክንያት ፈንድታ ወይም አብጣ ቀርታ ሌላ ነገር ላይ ጉዳት ስታደርስ የሚፈጠር ችግር ነው።

ጥያቄ፡- ይህን የዲስክ ማበጥ ወይም መፍረጥ የሚያስከትሉት ምክንያቶችስ ምንድናቸው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ዲስክ ድርቅ ያለ ሳይሆን እርስ በርሳቸው ከተያያዙ ፈሳሾች የተሰራ ነው። ስንተኛ ይህ ዲስክ ጫና ስለማይኖርበት ፈሳሹ የመጨመር ባህሪይ አለው። ቀን ላይ ግን ጫናው ስለሚኖርበት በተወሰነ ደረጃ ጠጣሩ የመብዛት አዝማሚያ አለው። ስለዚህ ፈሳሹ በሚበዛበት ወቅት የሚደረጉ ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች ለችግሩ አጋላጭ ናቸው።

ሁለተኛው ደግሞ የሰውነታችን እንቅስቃሴ ባህሪይ ነው። ማጎንበስ ዲስክ ወደ ኋላ እንዲያብጥ የሚያደርገው አንዱ ነገር ነው። በተለይ የምንጎነበሰው ክብደት ይዘን ከሆነ የበለጠ ተጋላጭ ነን። በዚህ ላይ ደግሞ አጎንብሶ መማዘዝ ካለበት ያንን ያበጠ ነገር ጨምቀን ወደ አንድ ቦታ ስለምንወስደው የበለጠ ተጋላጭ ነን። ዋናው መንስኤ ክብደት ይዞ ወይም ሳይዙ አጎንብሶ መጠማዘዝ ነው። ይሄ የሚደረገው ጠዋት ላይ ከሆነ ደግሞ ጉዳቱ ይብሳል። ሌላው ደግሞ የእድሜ መግፋት ነው። ችግሩ የሚከሰተው እድገት በጨረሰ ሰው ላይ ሲሆን፣ እድሜያቸው ከሰላሳዎቹ እስከ ሃምሳዎቹ ያሉ ሰዎች በብዛት ይጠቃሉ። ነገር ግን በአደጋ ምክንያት ከሆነ በየትኛውም እድሜ ላይ ሊከሰት ይችላል። አንድ ሰው ከእንቅልፉ ተነስቶ ቀና ከማለቱ ግማሽ ሰዓት በፊት ማንኛውንም መጎንበስ እና መጠማዘዝ ያለበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ለችግሩ መንስኤ ነው።

ጥያቄ፡- ከአብዛኞቹ የአጥንት ህመሞች ለመለየት የሚያግዙት የዲስክ ማበጥ ወይም መፍረጥ ችግር ዋና ዋና ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም የዲስክ መንሸራተት ችግር አይደለም። ሁሉም ደግሞ ያማሉ ማለት አይደለም። የዲስኩ ማበጥ ወይም መፍረጥ ሳይሆን ችግሩ፣ ሲፈርጥ የፈሰሰው ወደ የት ነው? ምን ላይ ነው የተጫነው የሚለው ነው ወሳኙ። ዲስክ የሚያብጠው ወይም የሚፈርጠው ስናጎብስ ብቻ ሳይሆን ቀና ስንልም ወደ ፊት ሊያብጥ ወይም ሊፈርጥ ይችላል። ነገር ግን ወደፊት ከሆነ አያምም። ወደጎንም ከሆነ ችግሩ የተፈጠረው የሚፈሰው በጣም አንገብጋቢ የሰውነት ክፍል ላይ ስላልሆነ ችግር የለውም። ነገር ግን ወደጎንና ወደ ኋላ ከሆነ እያንዳንዱ የጀርባ አጥንት የሚወጣባቸውን የነርቭ ስሮች ሊጨፈልቅ ይችላል።

በዚህ ጊዜ ነርቮቹ ሕመም ያመጣሉ። ሁለተኛው ደግሞ መሀል ለመሀል ወደ ኋላ ከሄደ እስፓይናልኮርድ አለ። ስፓይናልኮርድ ማለት የአንጎላችን ተከታይ የሆነ በህብለሰረሰራችን መሀል ወደ ታች የሚወርድ ነጭ ነገር ነው። ስፓይናልኮርድ ብዙ ነርቮች ተሰባስበው መሀል ለመሀል የሚወርዱበትን የማእከላዊ ነርቭ ሥርዓት አካል ነው። ስለዚህ ወደኋላ ሄዶ ያንን ማእከላዊ የነርቭ ስርዓታችንን ቢጫነው ያን ጊዜ ችግር ይኖራል። ይህ ማእከላዊ የነርቭ ስርዓት ስሜታችንን፣ እንቅስቃሴያችንን፣ የማላብ እና የሽንት መቆጣጠራችንን የሚቆጣጠር ስለሆነ ጫና ሲፈጠርበት ችግር ይሆናል።

ከዚህ ውጭ ዲስኩ ስላበጠ ሊያም ይችላል። ነገር ግን ህመሙ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ የሚለቅ ነው። የዲስክ ችግር ህመም የሚሆነው አንገብጋቢ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሲጫን ነው እንጂ መኖሩ ብቻ ችግር አያደርገውም። እድሜው ከአርባ እስከ ሃምሳ አመት ያለ እና የጀርባ ህመም አሞት የማያውቅ ሰው እንኳን ኤም አር ወይም ሲቲ ስካን ቢነሳ በአብዛኛው የዲስክ ችግር አለበት። በእኛ ሀገር ጥናት ባይደረግም በሌሎች ሀገራት በተደረገ ጥናት ግን ግማሽ ያህሉ የዲስክ ችግር አለባቸው።

ወደ ምልክቶቹ ስንመጣ ከሌሎች የጀርባ ህመም ምልክቶች ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን ለየት የሚያደርገው ነርቭን መጫን አለመጫኑ ነው። የመጀመሪያው በምንጎነበስበት ወቅት ህመም መኖር ነው። በሌላ ምክንያት የመጣ ህመምም ቢሆን መጎንበስ የሚያም ከሆነ የዲስክ ችግር ሊሆን ይችላል። በተለይ ስናጎነብስ የሚያመን ህመም ከሶስት ቀን በላይ ከቆየ፣ ተጎንብሰን ስንጠማዘዝ የሚያመን ከሆነ እንዲሁም ህመሙ ከጀርባ በተጨማሪም ወደ እግር የሚሄድ እና በእግራችን ጀርባ በኩል የመደንዘዝ ስሜት ከተሰማን፣ እንደ አንድ መስመር ወደ ታች የሚወርድ የህመም ስሜት፣ ቁጭ ባሉበት እግርን ቀጥ አድርጎ ሲዘረጉ በጀርባቸው ወይም በእግራቸው ላይ ህመም የሚሰማ ከሆነ ችግሩ ነርቭ ላይ ጫና የሚፈጥር የዲስክ ችግር ነው ተብሎ ይገመታል። ምልክቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው ትክክለኛነቱን የምናረጋግጠው በምርመራ ነው። በመጎንበስ ጊዜ የህመም ስሜት የሚፈጥሩ የጀርባ ህመሞች በጣም ጥቂት ናቸው።

ጥያቄ፡- የዲስክ በሽታ ህክምና የሚያስፈልገው መቼ ነው? ህክምናውስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ችግሩን የማያም እና የሚያም ብለን ከፍለነዋል። የማያመው የዲስክ ችግር ጉዳት ካላደረሰ እና ምልክት ከሌለው መታከም አይገባውም። የሚያመውን የዲስክ ችግር ስንመለከት አብዛኞቹ መጠነኛ እብጠት ናቸው።

ብዙውን ጊዜ መካከለኛ የዲስክ እብጠት ሆኖ በስፓይናልኮርድ ዙሪያ ባሉ ነርቮች ላይ የተጫኑ ይሆናሉ። እነዚህ በአብዛኛው በመደበኛ ፊዚዮቴራፒ እና ሌሎች ቀዶ ጥገና ባልሆነ ህክምናዎች ይድናሉ። በጣም ጥቂቶቹ ግን በስፓይናልኮርዱ ወይም በነርቭ ስሩ ላይ በደንብ ጫና ያሳደሩ እና የተወሰነ የሰውነት ክፍልን ለማዘዝ የሚያስችግሩ ይሆናሉ። በዚህን ጊዜ ዋናው አማራጭ ቀዶ ጥገና ይሆናል። ስለዚህ እንደ ችግሩ መጠን እና ክብደት በቀላል ማስታገሻ እስከ ቀዶ ጥገና የደረሰ ህክምና ይሰጣል።

ጥያቄ፡- ችግሩ እየከፋ ሲሄድ ሽንትና ሰገራን ለመቆጣጠር እስከመቸገር ሊያደርስ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ በተጨማሪ ችግሩ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ተጓዳኝ ችግሮችስ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ችግሩ ከበድ ያለ ከሆነ እና ስፓይናልኮርደ ወይም ነርቭ ላይ ብዙ ጫና ያሳደረ ከሆነ እየቆየ ሲሄድ በነርቭ መስመሮቹ ላይ የማይድን አደጋ ያደርሳል። ብዙ ጊዜ መጫኑ ያንን ቦታ ሊያቆስለው ይችላል። ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር የሚያቅተው መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ስለሆነ በፍጥነት ወደ ህክምና መሄድ ያስፈልጋል። ህመሙ ከሶስት ተከታታይ ቀናት በላይ ዝም ብሎ የሚቀጥል መጠነኛ ጉዳት እንኳን ቢሆን ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል። ችግሩ ከባድ ከሆነ ግን እንደ መጠነኛው ጊዜ የሚሰጠው ሳይሆን ወደ ትክክለኛው ቦታ ሄዶ የነርቭ ቀዶ ጥገና በማድረግ ህመሙ ስር እንዳይሰድ ማድረግ ይገባል።

ጥያቄ፡- ከጥንቃቄ ጉድለት የሚመጣውን የዲስክ ችግር መከላከል የሚቻልባቸው ጥንቃቄዎችስ ምድን ናቸው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት የሚመጣውን ችግር በቀጥታ መቆጣጠር አይቻልም። ምናልባት ራሳችንን ከአደጋዎች በመጠበቅ ተጋላጭነታችንን መቀነስ እንችላለን። በአብዛኛው የዲስክ ችግር የሚመጣው ጥንቃቄ ከጎደለው እንቅስቃሴ ነው። በተለይ እድሜያችን ከ20 እስከ 50 አመት የሆነ ሰዎች ከተኛንበት እግራችን እንደተዘረጋ ቁጭ ለማለት መሞከር፣ ተጣጥፎ እና ተጠማዝዞ የሚሰራ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ መጠምዘዝ እና መጎንበስን የሚፈልጉ የስራ አይነቶችን (በተለይ ሸክም ተሸክሞ) ማከናወን ለዲስክ ማበጥ እና መፍረጥ አጋላጭ ናቸው። እቃ ስናነሳ በተቻለ መጠን ከመጎንበስ ይልቅ እግራችንን አጥፈን ቁጥጥ ብለን ማንሳት፣ ጠዋት ከመኝታ ከተነሳን በኋላ ፊታችንን ለመታጠብ እንኳን ወዲያው ከመጎንበስ ይልቅ የተወሰነ ጊዜ ቀና ብለን መቆየት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ትንሽ ህመም ወይም ስሜት ያለው መጎንበስ እና መታጠፍ ካለ ያንን ማቆም ያስፈልጋል። ተከታታይነት ያለው እና ከሶስት ቀናት በላይ የሚቆይ የጀርባ ህመም ስሜት ካለ በአፋጣኝ ወደህክምና መሄድ ያስፈልጋል።

ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ህመሞች ሲያጋጥሙ በሰው እጅ የመታሸት ልምድ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው። በህክምናው ምን ያህል ተቀባይነት አለው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- መታሸት ተፈጥሯዊ ነው። ስለዚህ ታሽተን የሚያድነን ከሆነ ችግር የለውም። ነገር ግን ስንታሽ ህመሙን የሚያብሰው ከሆነ ችግር ይፈጥራል። ሁለተኛ ደግሞ የሚደርሰው ጫና ነው። መታሸቱ በጉልበት ሳይሆን በመጠኑ ማሻሸት ችግር ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን ታሽቶም ህመሙ ከፍተኛ ከሆነ፣ እቅስቃሴ የሚከለክል ከሆነ፣ ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል፣ እግር ላይ መደንዘዝ እና በድን መሆን፣ አንድ ጣትን እንኳን ማንቀሳቀስ የሚያቅት ከሆነ ምንም ማድረግ አይመከርም። ምክንያቱ ህመሙ ከዲስክ ውጪ የሆነ የጀርባ ህመም ሊሆን ይችላል። ጀርባችን አንዱ የካንሰር መሰራጨት ቦታ ነው። በተጨማሪም እድሜያቸው በጣም የገፋ ሰዎች በጣም ቀላል በሆነ እንቅስቃሴ አጥንታቸው ሊሰበር ይችላል። ያ የተሰበረ አጥንት ሲታሽ ወይም ሲገፋ የባሰ እየተለያየ ስለሚሄድ ስፓይናልኮርዳቸው ተቆርጦ የማይድን ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። ስለዚህ ወደ ህክምና በመሄድ ምንነቱ ሳይታወቅ ወደ መታሸት መሄዱ የባሰ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ይጠይቃል።

ጥያቄ፡- በሀገራችን ያለው ህክምና ምን ይመስላል? ተደራሽነቱስ?

ዶ/ር ኃይሉ፡- የባለሞያ ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በሀገራችን አሁን 17 ያህል የፊዚዮቴራፒ ሀኪሞች አሉ። ነገር ግን የባለሞያም ችግር አለ። ለማህበረሰቡም በቂ የሆነ መረጃ አላደረስንም። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንዱ ተጠቃሚ ደግሞ መረጃውም እያለው በሚፈለገው መንገድ ያለመጠቀም ሁኔታ አለ። ህክምናው ምልልስ ስለሚጠይቅ እና ታክሞ ወዲያው ስለማያበቃ መሰልቸት አለ። በመንግስት ሆስፒታሎች በጣም በዝቅተኛ ዋጋ አገልግሎቱን ማግኘት ቢቻልም ብዙዎች ሲገለገሉ አይታይም።

(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ)


230 views0 comments
bottom of page