• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጉራጌዎችና ክብነት (የኑሮና የህይወት ፍልስፍናቸው) ክፍል 1

Updated: Jun 9, 2019ሀሎ ! ምነው በፌስ ቡክ ሀሎ ማለት አይቻልም እንዴ? ሀሎ ብያለሁ፡፡

መስቀል ከፊለፊታችን ወደ እኛ እኛ እየገሰገሰ ነው ፡፡ እኛም ወደ እርሱ፡፡ መቼስ መስቀል ሲታሰብና ሲነሳ ጉራጌዎች አብረው ይነሳሉ፡፡ ጉራጌዎችን ካነሳን አይቀር አከራካሪ ነገሮች አሉኝ ፡፡

የጉራጌዎች መነሻ ኤርትራ ውስጥ ጉርዓ የሚባለው ስፍራ ነው ፡፡ ጉራጌዎች ከጉርዓ ተነስተው በአዝማች ስብሀት መሪነት አሁን ወደሚገኙበት ስፈራ እንደመጡ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ የታሪክ ጠበብቱ እንደነገሩን ኩጉርዓ ተነስቶ የመጣው ሰው ሳይሆን ሰዎች ናቸው ፡፡ ያውም መሪ ያላቸው፡፡ ሰዎቹ እንደመጡ ዓይመለል በሚባል ስፍራ ነው ያረፉት ፡፡ ካረፉ በኋላ አልተነጣጠሉም ፡፡ እዚያው መጠለያዎቻቸውን ሰርተዋል፡፡ አንድ ቤት አይደለም የሰሩት ቤቶች እንጂ፡፡

አከራካሪው የኔ ሀሳብም ተከታዩ ነው ፡፡ አንዳንዶች ፣ ብሄሩን ‘‘ ጉራጌ’’ ፣ ብለው ይጠሩታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‘‘ ጉራጌዎች’’ ፣ ይላሉ፡፡ እንግዲህ የትኛው ነው ትክክለኛ መጠሪያ?

በልዩነት አምናለሁ ፡፡ በልዩነት ውስጥ ባለ ጠንካራ አንድነት ደግሞ በጅጉ አምናለሁ ፡፡ ለኔ ፣ አሁን በልዩነት ውስጥ ባለ ጠንካራ አንድነት ለማምነው ‘‘ ጉራጌዎች ’’ ፣ የሚለው ስም ትክክለኛ መጠሪያችን ነው ፡፡ ለኔ ፣ ህይወት እንዳትሰለቸኝ ልዩነትን የሰጠኝ ፈጣሪ ይመስገን ፡፡ የጉራጌዎች ቀለመ ብዝሀነት የፈጣሪ በረከት ነው ፡፡ ይህ በረከት በጠንካራ አንድነት ላይ ካልቆመ ግን እርግማን ነው ፡፡ መመረቅን ይወዳሉ ፣ እርግማንን ደግሞ በጅጉ ይፈራሉ -ጉራጌዎች፡፡

የጉራጌዎችን ቋንቋ በዘዬ ልዩነት እና ብዛት የሚስተካከለው ሌላ ቋንቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ወደ አስራሁለት ግድም ዘዬ፤ በኔ እምነት፡፡

አንዳንድ ከፍተኛ የውጭ ሀገር የቋንቋ ምሁራን(ቤንደር)ሳይቀር የጉራጌዎች ቋንቋ ከግዕዝ ተመዘዘ አይሉም ፡፡ የልቅስ የሴሜቲክ ቋንቋዎች ሁሉ አያት ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዘዬዎች ያሉት ቋንቋ ቀደምት ነው ብለው ስለሚያምኑ፡፡ የቋንቋ ጥናት ቲዎሪውም ይህንኑ ስለሚል፡፡

‘‘ ጉራጌ ’’ ፣ የሚለው ቃል ጉርዓ እና ‘‘ጌ ’’ ፣ የሚሉት ቃላቶች ጥምር ውጤት ነው ፡፡ ጉርዓ መነሻ አካባቢያቸው ነው ፡፡ በሂደት ደግሞ የሰዎቹ መጠሪያ ስም ፡፡ ‘‘ጌ’’ ማለት ደግሞ ቤት ነው ፡፡

እንደዚህ ከሆነ ነገሩ ጉራጌ ማለት የጉርዓ- ቤት ይሆናል ማለት ነው ፡፡ በዘዬ ብዛትም ይሁን በታሪካዊ ስያሜ ተጠየቅ (ሎጂክ) ካየነው መጠሪያችን ጉራጌ ሳይሆን ‘‘ ጉራጌዎች ’’ ነው ማለት ነው ፡፡ አይደለም የምትሉ ካላችሁ፣ በምክንያት ተከራከሩኝ ፡፡ ቁጣና ስድብ ግን አይቻልም ፡፡ መከራከርና ማሳመን እንጂ፡፡

አሁን ደግሞ ወደ አንድ ታሪካዊ እውነት ልውሰዳችሁ፡-

ጉራጌ ዞን ውስጥ እዣ ወረዳ ፣ አትርፎ ጊዮርጊስ የሚባል ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት የጊዮርጊስ በዓል የሚከብረው በ23 ነው፡፡ ነገር ግን አትርፎ ጊዮርጊስ የሚነግሰው ህዳር 18 ነው ፡፡ ለምን ?

የዓድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ የታወጀው በ18 ስለነበር ፡፡ በወቅቱ በአካባቢው የኖሩ የነበሩ ጉራጌዎች አዋጁ ደርሷቸው ለክተቱ ተንቀሳቅሰዋል ፡፡ ሲንቀሳቀሱ ከቀያቸው አፈር ዘግነው ይዘዋል፡፡ አፈሩን ዘግነው ወደ አውደ ውጊያው የሄዱት ለሀገራችን ክብር ግንባሩ ላይ ሆነን ስንዋጋ ብንወድቅ ካገሬው አፈር ጋር የወሰድነው አፈር ተቀላቅሎ እንቀበርበት ፣ ይህም ላገራችን ክብር ተደምረን የመሞታችን፣ለባንዲራችን ክብር የማለፋችን ፣ የአንድነታችን ማስታወሻ ይሁን ብለው ነው ፡፡

‘‘አትርፎ ’’ ፣ የሚለው ስያሜም ታሪካዊ ምክንያት አለው ፡፡ ዘማቾቹ ከአካባቢያቸው ተነስተው ሲሄዱ ‘‘ አትርፎ’’ ፣ አትርፋቸው ፣ በሚል ምርቃት ተሸኝተዋል፡፡

የአድዋን ጦርነት ድል አድርገው ፣ ከዕልቂትም ተርፈው ሲመለሱ ፣ የጊዮርጊስ ታቦትን ወደ ስፍራው ይዘው በመመለስ ‘‘ አትርፎ ጊዮርጊስን ’’ ፣ አቁመዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ክብሩ በተለየ መልኩ ፣ የክተት አዋጁ በታወጀበት ዕለት፣ህዳር 18 የሚነግሰው ፡፡

በነገራችን ላይ በአድዋ ጦርነት ወቅት ፣ አድዋ ላይ ተተክሎ ፣ ግዳይ የጣሉ ጀግኖች ተሰባስበው የፎከሩበትን ድንኳን አስፈትለው ያሰፉት የአፄ ሚኒልክ ስራ ቤት ሀላፊ የነበሩት ፣ ጉራጌዋ እማሆይ ደስታ ጣድየ ናቸው ፡፡

ክፍል 2 ወደ ተነገወዲያ ገፅ ዞሯል….

(በደራሲና ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ)

40 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean