top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አስተዳደራዊ ብልሹነት በመስቃንና ማረቆው ግጭት



በሁለቱም ወገን እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል።ከ200 ሰዎች በላይ ቆስለዋል።ማእከላዊ መንግስቱ አትኩሮት አልሰጠውም። የመገናኛ ብዙሗን ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› ብለዋል።ይህንን ግጭት የዘገቡት የመገናኛ ብዙሗን የተፋለሰ፣ሚዛናዊ ያልሆነ፣ ተበዳዩን መልሶ በዳይ የሚያደርግ ዘገባን አቅርበዋል ሲሉ የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች ይከሳሉ።ጉዳዩን ለማጣራት በማረቆ ብሎም በመስቃን ወረዳ ያሉ እማኞች፣የጥቃቱ ሰለባዎች፣የመንግስት ባለስልጣናትና ያገር ሽማግሌዎችን አናግረናል።

የገዥ መደቦች የቀበሩት ዘመን ተሻጋሪ ቦምብ

ግጭቱ ታሪካዊ ነው።ግጭቱ የገዥ መደቦች የቀበሩት ዘመን ተሻጋሪ ቦምብ ነው።መስቃንና ማረቆዎች የተለያዩ ጦርነቶችን አካሂደዋል።ጦርነት አሸናፊ የለውምና የጦርነትን ኪሳራን በታሪካዊ ሒደት ዉስጥ ሁለቱም ወገኞች ተጋርተዋል።መስቃንና ማረቆ ደም ተቃብተዋል-ታርቀዋልም። ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋል፣ቋንቋን ሐይማኖትን ተጋርተዋል።ሁለቱም ድርቅን፣ርሃብን መከራን፣ሐዘንንና ደስታን ተጋርተዋል። ያንን የዘመናት ቁርሾ ለመሻር በጋብቻ ተጣምረው፣ በፍቅር ተሳስረው ወደ በቤተሰባዊ የወል ህይወት ቀይረዋል። «ከእንግዲህ በሗላ መጋጨቱና ደም መፋሰሱ ማንንም የማይጠቅም የራስን እጅ በራስ ከመቁረጥ የማይለይ ነው!» የሚል የሽማግሌዎች ድምጽ ዛሬም ያስተጋባል።

በቀድሞው ስርዓተ-ማህበር የመጠሪያ የስያሜ ችግሮች እንደነበሩ የታሪክ ምስክሮች ይተርካሉ። ወረዳው«ማረቆና መስቃን ወይስ መስቃንና ማረቆ?» በርበሬው «የማረቆ በርበሬ ወይስ የመስቃን በርበሬ?»ካልያም «የማረቆና የመስቃን በርበሬ?» እነዚህ ከማንነት ጋር የተያያዙ ብሔረሰቦችን የሚያተናኩሱ ጥያቄዎች በገዢ መተደቦች የጭቆና እጅ ተዘግነው በህዝቡ ዉስጥ እንዲሰርጹ የተደረጉ መርዞች ናቸው። ህዝቡ ግን በጋብቻና በባህላዊ እሴቶቹ ተጣምሮ፣ ሰላሙን እንደን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ መኖሩን ቀጥሎ ነበር።

የመስከረም 03/2011 ግጭትና መንስኤው

ታሪካዊና ወቅታዊ ሒደቶችን ያጤኑት አቶ መሐመድ የመስከረም 03/2011 ግጭት መንስኤ ያስረዳሉ።እንዲህም ይላሉ «የመስቃን ወረዳ ህዝብ በሚፈልገው መሪ ተመርቶ አያውቅም። አስተዳደራዊ ሸፍጥ ሲሰሩ የነበሩ የወረዳና የቡታጅራ ከተማ የአመራር አካላት ህዝብ አንቅሮ ተፍቷቸዋል።እነዚሁ ሸፍጠኞች በህዝብ ግፊት ከወንበራቸው ላይ ተንገዳግደው ተነሱ።አቶ ሚፍታ ሸምሱ የወርዳ አስተዳዳሪ፣አቶ አህመድ ኑሪ (ጎበዜ በቅጽል ስማቸው) የቡታጅራ ክንቲባ እንዲሆኑ ተወሰነ» ይህ ህዝባዊ ዉሳኔና ዲሞክራሲያዊ ሒደት ያስደሰታቸው የእንሴኖ ከተማ ያሉ የመስቃን ተወላጆች ደስታቸውን ሲገልጹ ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃት ተሰነዘረባቸው ሲሉ አቶ መሐመድ ይገልጻሉ።

ሒደቱን ለረጅም ግዜ ሲከታተሉ የት አቶ ሐምዛ በምልስት ለረጅም ግዜ ሲንተከተክ የነበረውን የድንበርና የዘር ጉዳይን አጽንኦት ይሰጣሉ።በህወሃት የሚመራዉ መንግስት ከገባ በሗላ የዘራዉ የዘር ፖለቲካ ችግሩን አባባሽ ሆኗል። የዘር ፖለቲካው «ከባልሽ ባሌ ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ» እሳቤን የሰነቀ ነው።በድንበር፣በክልልና በዞን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዉስጥ ሽኩቻው መድራቱን ልብ ይሏል።የቀበሌዎች ይገባኛል ባይነት ጎልቷል።ጉዳዩን በቅርበት የሚያዉቁ ሲያስረዱ መስከረም 03/2011 በተለኮሰው የዘር ግጭት የቆየ ነው።የተበላሸ አስተዳደራዊ ተሞክሮ ያላቸው ባለስልጥናት አደፈጡ።ቂምና ከንፈርን መንከሱ ተዳፍኖ ሳይጠፋ ቆየ።ለሐያ አመታት በዉስጥ ሲንተከተክ የነበረው የመሬት ይዞታ ይገባናል ባይነት ተንፍሶ በሁለቱም ወገኖች 200 ሰዎች እንዲቆስሉ፣30 ሰዎች እንዲሞቱ መንስኤ ሆነ።ዉጥረቱ እንዳየለ መቀጠሉን ሰላም ፈላጊ የሆኑ የመስቃንና የማረቆ ተወላጆች ይገልጻሉ።

እስከ ክልል የዘለገው አስተዳደራዊ ብልሹነት

የግጭቱ መንስኤ ከዞን እስከ ክልል የዘለገ ነው።በክልል በኩል ተወንጭፈው ማእከላዊ መንግስት የደረሱ ባለስልጣናት የራሳቸውን ክልል በደምብ አይቃኙም ሲሉ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።የክልል ባለስልጥናት በዞን ዉስጥ የተሰገሰጉትን ጸረ-ህዝብ ሐይሎች የመቀነስ ስራቸውን በተገቢው መልኩ ባለማከናወናቸው አገሪቷ አገሪቷ እንዳትረጋጋ እየተደረገ ነው።በዶ/ር አብይ የመደመር ስሌት መቀነስም ግድ ነውና ጸብ-አጫሪ ሴረኞች መቀነስ አለባቸው የሚል ድምጽ ያስተጋባል።አቶ መሀመድና አቶ ሐምዛ በሐሳቡ ይስማማሉ።በሽምግልና ጉዳይ የሚንቀሳቀሱት አቶ ሸረፋ ዲሊቾም ይህንንኑ ሐሳብ ያስተጋባሉ።

27 ሰባት አመታትን ኢትዮጵያን «እግር ተወርች» የጠፈራት ህወሃት መራሹ ቡድን በህዝባዊ አመጽ ዙፋኑ ተናጋበት።በመደመር ፖለቲካዊ ስሌት በለውጥ አሳንሰር ወደ ላይ ያሻቀቡት ዶ/ር አብይ አህመድ የለውጡን ቅላጼ ሲያዥጎደጉዱት ዜማዉና ግጥሙ ያልተመቻቸው በዘመኑ ቋንቋ «የቀን ጅቦች» የሚባሉት ሴረኞች በሴራ ፖለቲካ ተሰማሩ። ይህ በመስቃንና በማረቆ ወረዳዎች ተስተውሏል።አቶ ሐምዛ ያስረዳሉ።

በለዉጡ ቅላጼ የበረገጉ፣ጥቅማቸው የተነካባቸው፣ስልጣንን በትምርትና በብቃት ሳይሆን በጅ አዙር የተቀዳጁ፣አምባገነናዊውን የህወሃት «ሰመመን» ማስቀጠል የሚሹ ወንጀለኞች በተለያየ አጋጣሚዎች ሴራቸው በህዝባዊ ጥረት ቢቀፈደድም በሰፊዋ ኢትዮጵያ ተሸሽገው ያሉት ሌሎች ሴረኞች ሁከትን ከመፍጠር አልቦዘነምና ከሐዋሳ እስከ ዉልቅጤ ባለው የስልጣን ተዋረድ ዉስጥ ያሉትን ጸረ-ህዝብ አረሞች ሐይላት የዶ/ር አብይ ግብረሐይል መንቀል አለበት በማለት የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

በሰኔ 16/2010 አብዮት አደባባይ ላይ በዶ/ር የመግደል ሙከራ መደረጉን የተቃወሙት የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች በዘር፣በሐይማኖት ሳይለያዩ በሰኔ 23/2010 ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።ሰላማዊ ሰልፉ በኢትዮጵያ ከተሞች ተደረጉ ከተባሉት ሰልፎች መካከል በትልቅነቱ የሚወሳ ነበር።ህዝቡ ለተጎጅዎች ደም ለግሶ ታሪክን ሰርቷል።ያ ሰልፍ በቡታጅራ ከተማና በመስቃን ወረዳ ለሚገኙ ለውጥ ፈላጊዎች ወገኖች ጥርስ አስነክሶባቸው ነበር።አጋጣሚው ተጠብቆ መስከረም 03/2011 ከቡታጅራ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋ እንሴኖ ዉስጥ የጥላቻ ርችት ተተኮሰ።የማረቆ ወረዳ ፖሊስ ጉዳዩን ከማብረድ ይልቅ ጥቃት ፈጻሚ ሆነ።የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ነገሩን ለማብረድ በመጣሩ ከሁለቱም ወገን የሰው ህይወት ጠፍቷል።

ዘለቂታዊ ሰላምን መስቃንና ማረቆዎች ይሻሉ

መስቃንና ማረቆዎች ገዢ መደቦች የሰጡንን ቁርሾ በፍቅር ከልሰን መኖር ጀምረናል።የአዲሱ ትዉልድ መለዮው ግጭት ሳይሆን ፍቅር ነው።የጥላቻን መርዝ በፍቅር ከልሰን በቋንቋዎችችን ተውበን፣ባህሎቻችንን ተጋርተን፣ የወረዳዎቻችንን ጸጋ ወይም የኛ «የነዳጅ ዘይት» የሆነውን በርበሬ እያመረትን እኖራለን። ፍቅር የዘመኑ መገለጫችን ነው በማለት በጣምራ ያስረዳሉ።ሐሳቡን ያነጋገርናቸው አቶ መሀመድ፣አቶ ሐምዛና አቶ ሸረፋ ይጋራሉ።

አቶ ታምራት ዲላ እያሱ የደቡብ ክልል የፋይናስ መምሪያ ዋና ሐላፊ እና የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።አቶ ታምራት «እኔ በዘር ፖለቲካ ልፈተሽ አይገባም፣ቃለ-መሐላ የፈጸምኩት ህዝብን ላገለግል ነው» ይላሉ።የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች አቶ ታምራት በክልል ደረጃ ያሉ ባለስልጣን በመሆናቸው የግጭቱ ጠንሳሽ አርሳቸው ናቸው ሲሉ ይከሳሉ።ጣቶች ሁሉ ወደ አቶ ታምራት ይቀሰራሉ።ቢሆንም የማረቆ ተወላጁ አቶ ታምራት ዲላም ይሁኑ ሌሎቹም የመስቃን ተወላጆች በጋራ ህዝቡን ያስተሳሰረው የወል ባህላዊ እሴት ክብደት፣ ፍቅርን መሰረት ያደረገ የትዉልድ መስተጻምር የሆነው ጋብቻን ጥልቀት ዘለቄታዊ ሰላምን በሁሉም ለሁሉም በማምጣቱ ረገድ ሁሉም ይስማማሉ።

አቶ ታምራት ዲላ እያሱ ችግሩን ጠንሳሽና አቀጣጣይ ናቸው የሚል ክስ የሚቀርብባቸው ቢሆንም።እርሳቸው ያስተባብላሉ።እኔ የመፍትሔ አካል መሆን የምሻ ንጹህ ሰው ነኝ።አዝኛለሁ ዉስጤ ተጎድቷልም በማለት ያስረዳሉ።

የለዉጡ ሐይል በመሆን ከዶ/ር አብይ ጎን የቆሙት የፓርላማው አፈ-ጉባኤና የደህዴን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሙፈሪኻት ካሚል ግጭቶት ሲደርሱ የሚንሰፈሰፉ፣ልብሳቸውን አውልቀው የሚያለብሱ፣አራስን በጃቸው ቅቤ የሚቀቡ ቢሆኑም በክልልላቸው በመስቃን ወረዳ ስለደረሰው ችግር ምንም አላሉም ሲሉ አቶ መሐመድ ቅሬታ ያቀርባሉ! (ወ/ሮ ሙፈሪኻት ካሚል ይህ ዘገባ ለአየር ከበቃ በኋላ ወደ መስቃን ወረዳ በማቅናት ተጎጂዎችን ጎብኝተዋል)።

ስጋቱና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች እሮሮ

ስጋት አለ።በለውጡ ዉስጥ የተሰገሰጉ ሴሬኛ ፖለቲከኞች እየደበዘዘ ያለውን የ27 አመታት ጨቋኝ ቡድን ዳግም ለማድመቅ እየሰሩ ነው።እነዚሁ ሴረኞች የማረቆ ወረዳ አርሶ አደርን በምስጢር አስታጥቀዋል።መተኮስ ያልተማረ ብዙ ነው።ህዝቡ እርስ በርሱ እንዳይተላለቅ ማእከላዊ መንግስት እጁን ሊያስገባ ይገባል የአቶ ሐምዛ ጥሪ ነው።

ምንም ግጭት ቢኖር ተማሪዎቼን አስተምራለሁ ብሎ የወጣው አስተማሪ ወደ ቤት አልተመለሰም።እናትና አባት የሌላቸውን ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድር፣የሶስት ልጆች ኣባት የሆነው አባ-ወራ ባለቤቱን ጥሎ አይቀሬውን የሞት ጽዋ ቀመሰ።ሸህሞሎ ወንድሙ ነው ሐዘኑንም ይገልጻል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ወጣት ሸህሞሎ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተደራጅቶ የከፈተው ጸጉር ማስተካከያ ቤቴ ዘርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ሳቢያ ተቃጠለብኝ፣በእንሴኖ ከተማ በደረሰው ጥቃት ተጎድቼ ህክምናን እየተከታተልኩ ነው በማለት የደረሰበትን መከራ ሳግ በሚተናነቀው ድምጽ ያስረዳል።

የተጅመረው ሽምግልናና ያካበቡት መሰናክሎች

በአካባቢው ባህል መሰረት የመስቃንና የማረቆን ግጭት ለማርገብ ሽምግልና ተጀምሯል።ጥረቱ እስይ የሚያስብል ቢሆንም አንዳንድ ባለስልጣናትና ባለሐብቶች እርቁ ጥቅማቸውን የሚነካባቸው በመሆኑ ሽምግልናው እንዳይሳካ ማሳደም ጀምረዋል ሲሉ አቶ ሸረፋ ዲሊቾ ገልጸዋል።የመስቃን ተወላጆች ክስ የሚያቀርቡባቸው አቶ ታምራት ዲላ እያሱ ሽምግልናው ይሳካ ዘንድ አቅማቸው በፈቀደው መጠን እንደሚጥሩ ቃል ቢገቡም አቶ ሀምዛ በሽምግልናው ሒደት ላይ ጥርጣሬ አላቸው።ሽምግልናን እምቢኝ ያሉ ሲሉ ለጥፋት የተዘጋጁ ነጋዴዎችና ባለስልጣናት በቆሼና በእንሴኖ ከተማዎች ይገኛሉ በማለት የአቶ ሸረፋን ሐሳብ ይደግፋሉ።

ችግሩ ተመሳሳይ ቢሆንም የመንግስት አትኩሮት አናሳ ነው

አገሪቱ ዉስጥ አንጻራዊ የሆነ ለውጥ እየመጣ ቢሆንም በፌዴራል ስራቱ ዉስጥ ባለው የግዛቤ ችግርና የአተገባበር ተግዳሮቶች ሳቢያ በየቦታው ግጭቶች ይታያሉ።የመስቃንና ማረቆ ችግር ከነዚሁ ችግሮች ተርታ የሚመደብ ቢሆንም በማእከላዊ መንግስትና በሚዲያ አትኩሮትን አላገኘም።

ወረዳችን እየተቀነሰ ነው።የወረዳችን ቀበሌዎች እየተመናመኑ ነው የሚሉት የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች በደቡብ ክልል ዉስጥ ካሉት ከተሞች በትልቅነቷ የምትታወቀው፣ ህብረ ብሄሮች በውስጧ ያቀፈቸው ቡታጅራ በዞንንና በክልል አሻጥር እንድታንስና ላገሪቱ እድገት ሚና እንዳይኖራት ትደረጋለች ሲሉ ይከሳሉ።

ከ1997 ምርጫ በኋላ ጉራጌው ስልታዊ ጥቃት ይደርስበታል

«የ1997 ምርጫን ተከትሎ የጉራጌ ማህበረሰብ መገለል ይደርስበታል» በማለት የሚናገሩት የመስቃን ተወላጆች ላለፉት 13 አመታት በህወሃት የሚመራዉ ማእከላዊ መንግስት በሴራ ፖአለቲካ አዳክሞናል፣ዘርን መሰረት ያደረገው የቀበሌዎች አወቃቀር ለዘር ማጥፋት ወንጀሎች አጋልጾናልና አትኩሮት እንሻለን ሲሉ ይጣራሉ።

አስተዳደራዊ ብልሹነት በመስቃንና ማረቆ ግጭት ታይቷል።ይህንን አስተዳደራዊ ብልሹነት መልከዓ-ምድራዊ ጥቅምን ቀንሶ፣ቋንቋን አፋልሶ፣ባህልን ከልሶ፣ህዝብን እርስ በርሱ አጫርሶ ለዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) የሚገፋፋ ነው የሚሉት የመስቃን ተወላጆች የዶ/ር አብይ መንግስት፣ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች፣የግልና የመንግስት ሚዲያዎች አትኩሮት ሰጥተውን የመፍትሔውው አካል ይሁኑ ሲሉ ይጣራሉ።ልብ ያለው ልብ ይበል!

በሳዲቅ አህመድ


42 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page