top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጉራጌዎችና ክብነት (የኑሮና የህይወት ፍልስፍናቸው) - ክፍል 2

Updated: Jun 9, 2019


ቤት አሰራር እና መገልገያ ቁሳቁሶች(ክቦች)


Getu Shanqo

ጉራጌዎች ቤታቸው ክብ ነው ፡፡ ሌሎች የአትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችም ቤታቸውን ክብ አድረገው ይሰራሉ ፡፡ እንደጉራጌዎች ግን ለክብ ባህላዊ ቤቶቻቸው ግንባታ ትልቅ አሴት የሚያፈሱ ያሉ አይመስሉኝም ፡፡ ሶስት ትውልድ ድረስ የሚኖርበትን ቤት ክብ አድርገው ያንፃሉ፡፡ ክቡ የቤታቸው ምሶሶ እድሜው በዝናብ እንዳይቀጭ ክብ ቆርቀሮ አናቱ ላይ ይደፉለታል ፡፡ ክብ ኮፍያ ያለው ምሶሶ በሉት ፡፡

ከከምሶሶው አናት ወረድ ብሎ ያለው የሳር ክፍክፍም ክብ ክብ ደረጃዎች ያሉት ሆኖ ነው የሚታነፀው ፡፡ ክብ ሆኖ የተሰራው ቤታቸው ብቻውን አይደለም የሚቆመው ፡፡ ከሌሎች ክብ ቤቶች ጋር ተካቦ ነው፡፡ ቤታቸውን አካበው በመኖር ፣ ተካበው ህይወታቸውን ይገፈሉ እንጂ ተበታትነው አይደለም፡፡ ብትን ብትን የለም!

ወደ ውስጥ ፣ ወደ ቤታቸው ግቡ፡፡ ክብ ምድጃ ታገኛላችሁ፡፡ ክቡ ምድጃ ላይ ፣ ተለቅ ተለቅ ያሉ ክብ ክብ ጉልቻዎች ፣‘‘ ጎንዝየ’’ ፣ ክብ ሰርተው ታያላችሁ ፡፡ ዓይኖቻችሁ ወደ ውስጥ ፣ ወደ ምድጃው ስር የዘለቁ እንደሆን ደግሞ ሌሎች ትናንሽ ጉልቻዎች ክብ ሰርተው አሉ፡፡ እንደደረጃቸው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ትንሽ ክብ የሸክላ ድስት ስትመጣ ፣ ትናንሾቹ ክብ ጉልቻዎች፡፡ ትልቅ ጀበና ፣ ሲመጣ ትላልቆቹ፡፡

በነገራችን ላይ በሰው ቁመት የሚነሳ ትልቅ ጀበና ያለው ጉራጌዎች ጋ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ኣኻ! የጉራጌዎች ጀበና ነገር ከተነሳ ፡፡ የጀበናው አንገት ያንባር ጌጦች ያሉት ነው - አንገቱ ላይ በጥበበኞቹ የተለጠፉ(ሲልድ የሆኑ)፡፡ የጀበናውን አንገት ክብ በክብ አርገውታል - እደ ጥበበኞቹ፡፡

ክብ ጀበና በክብ ጉልቻዎች ላይ እንደሚጣድ ሁሉ ክብ መድጃና ጉልቻዎቹ ላይ በክብ ምጣድ ላይ የሚጋገረው የእንሰት ቂጣ ራሱ ከብ ሆኖ ነው ፡፡ እንሰቱ ራሱ ክብ በሆነ ጉድጓድ ውስጥ ተተክሎ ፣ ከተፋቀ በኋላ ክብ በሆነ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮና በስሎ ነው ለምግብነት የሚውለው፡፡

የቤታቸውን ግድግዳ ተመልከቱ፡፡ ክብ ክብ ቄንጠኛ የባህል ምግብ መመገቢያ ቁሳቁሶች ክብ ስርተው በስርዓት ተሰድረዋል፡፡ ክብ ክብ ሆነው ከተሰደሩት ቁሳቁሶች መካከል የቡና ቁርስ ማቅረቢያውን የስንደዶ ስፌት ፣ ሌማት፣ተመልከቱት ፡፡

ቀጥ ፣ ቀጥ ያሉትን ስንደዶዎች በመጠምዘዝ በክብ ላይ ክብ በመደመር አበጅተውታል፡፡ ቀጥ ያለውን እና ብቻውን የቆመውን ስንደዶ ሳይቀር ወደራሳቸው የሕወት እና የኑሮ ፍልስፍና በመቀየር ክብ እንዲሆንና ከሌሎች ስንደዶዎች ጋር እንዲካበብ በጥበባቸው ይገሩታል፡፡ በዚህ ስንደዶን የመግራት ጥበባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ክቦች ሲደምሩም ቆይተው ህይወት እንዳትሰለቸን ደግሞ በቀለማት ህብር አንቆጥቁጠው ፣ሳርን ሳይቀር አሰልጥነው ፣ ይሸልሙናል፡፡ቤታቸው ውስጥ ተካቦ መቀመጫዎችን ፣ ክብ ወንበሮችን እንዲሁ ታገኛላችሁ፡፡

ህይወት ለጉራጌዎች ክብነት፣ ክብብነት ነው ፡፡ የኑሮ ይትበሀል ለጉራጌዎች ክብብ ፣ ክብብነት፡፡ እኔ እንግዲህ ጥቂት ቁሶችን ነው የጠቀስኩላችሁ፡፡ እናንተ ደግሞ ከንግዲህ በኋላ ያትኩሮት መነፅሮቻቻሁን አንስታችሁ ተመለከቱ ፡፡ ጉራጌዎች ጋ ብዙ ክብ የባህል ቁሳቁሶች ታያላችሁ፡፡ ክብ ህይወቶችን ትመዘግባላችሁ፡፡

ማህበራዊ ክብነት (ሰርግ፣ በዓላት፣ ፍትህ፣ ፣ ልደት..)

የክርስትና ዕምነት ተከታይ ለሆኑ ለጉራጌዎች የመስቀል በዓል እና ሰርግ ታናሽና ታላቅ ናቸው ፡፡ በአብዛኛው ይክርስትና እምነት ተከታይ ለሆኑ ጉራጌዎች የዿጉሜ ማወይም የመስከረም ሰንበቶች ለጉራጌዎች የሰርግ ቀናት ናቸው ፡፡ ስርጉን ለማጀብ ከተለያዩ የኢትዮጵያ መሬቶች ለስራ የተበተኑ ለመሞሸርም ፣ ሙሽሮችን ለማጀብ፣ ለመካበብ ይሰባሰባሉ፡፡ በክብ ቤቶቻቸው ውስጥ ተካበው በክብ ዕቃዎች የተዘጋጁ ምግቦችን ክብ ሰርተው ይመገባሉ፡፡ ክትፎ ከሆነም ምግቡ ፣ ፉት ፣ ፉት ሲያረጉት መብላት ሳይሆን መጠጣት ይመስላል ፡፡

ዘፈኖቻቸውም በክብ ስርዓት ነው የሚመሩት፡፡ የሴቶቹን የዓጨፋፈር ስልት ተመልከቱ፡፡ ክብ ሰርተው ፣ እጆቻቸውን በወገባቸው ዙሪያ አሻግረው፣ ክብ መተቃቀፍ አበጅተው ነው፡፡ ለምሳሌ ‘‘ የወሬናኻ ጎሽ … ኣኻ …’’ ፣ ነሸጥ አርኝ !

ክብ ሰርተው ከሚዘፍኑት ሴቶች መካከል ምናልባት ትዳር የመሰረተች ሴት ብትገኝ ፡፡ ወገቧን በመታጠቂያ ወይም በጥበብ ነጠላ ከባዋላች፡፡ መሀል ሆና ዘፈኑን የምታወጣው ሴት ራሷ፣ ክብ ከበሮ እየተመተመች ክብ ትዞራለች፡፡

ሙሽራውም እኮ የክብነት ምልክት አርፎበታል፡፡ የራስ ቅሉ በነጭ ሻሽ ተከቧል፡፡ ሙሽራዋም ክብብ ፣ ክንብንብ ትላለች፡፡ ክብነት ፣ ጉራጌዎችና ህይወት !!

በሙሽርነት ጊዜዋም ወደ አዳብና ስትሄድ ተካባ ነውኮ፡፡

የመስቀል በኣል ከመምጣቱ አስቀድም ክብ ደመራ ይቆማል ፡፡ ደመራው በሚለኮስበት ዕለትም ክብ ሰርቶ መጨፈር ነው ፡፡ ጉራጌዎች የመስቀልን በዓል በእለቱም ይሁን ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ተካበው ይደሰቱበታል ፡፡ ብቻ መብል የለም ፡፡ ይእድሜ እኩዮች በየተራ ወደየቤታቸው እየተጠራሩ በክብ መመገቢያ ዕቃዎች ዙሪያ ክብ ሰርተው ቤት ያፈራውን ይመገባሉ፡፡

ክቡና የተቀቀለው የበሬ ሻኛ ፣ የምርቃት ራስ ነው፡፡ አባቶች የከበቧቸውን ልጆች ፣ ‘‘እኔን ሻኛ እንዳበላችሁኝ ፣ ሻኛ ብሉ!! ….’’ ፣ ምርቃት ያዘንቡላቸዋል፡፡ እነሱም በዘነበው ይረስርሳሉ፡፡

አዳብናም መካበቢያ ነው ፡፡ አዚያ ቆለኛና ደገኛ ፣ ያኛው መንደር ከዚህኛው መንደር ይገናኛል ፡፡ ከመካበብ በላይ መተጫጨት ‘‘ መደመር ’’ ፣ አለ ፡፡

የጉራጌዎች የመካበብና የመሰባሰብ የህይወትና የኑሮ ፍልስፍና መስቀልና ላይ ብቻ አይቆምም ፡፡ የገና ሰሞን የሰማይ ላይ ልዕልት፣ ፀሐይ ፣ታረፍዳለች፡፡ በገና እለት ሴቶች ልጆች ተሰባስበው ክቡን ወንፊት ይዘው ‘‘ የገና ጀንበር የት ውለሽ ነበር…’’ ፣ እያሉ ይጠይቋታል ፣ ክቧን ፀሐይ ፡፡

እኔ ተወልጄ ባደግኩት አካባቢ ደግም በአስተርዮ ማርያም ዕለት ሌላ ክብ ትውፊታዊ ድራማ ይከወናል ፡፡ መንታ ልጆች የወለደች እናት በቤተሰቦቿና በጎረቤቶቿ ተከባ እየተዘፈነ ወደ ክብሩ ትመጣለች፡፡ ግንበሯ ዙሪያውን በሻሽ ተከቦ ፣ እንደገናም ግንባሯን ከዞረው ሻሽ በላይ ክብ ጨረቃ የመሰለ ቅቤ ተቀብታ ትታያልች፡፡

ልደትም መካበቢያ ነው ፡፡ ዕናቶች ተሰባስበውን ተካበው ፣ ባህላዊ ምግቦቻቸውን እየበሉ እየጠጡ ተካበው አራሷን ይመርቃሉ፡፡ ልደትን ያከብራሉ፡፡

አሁንም እኔ ተወልጄ ባደግኩበት አካባቢ አንድ ክብ ትእይንት አለ ፡፡ የዕስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ‘‘ ሊቃ ’’ የተሰኘ ሀይማኖታዊ ስርዓት አላቸው ፡፡ ሊቃ የሚቀመጡት በዘፈቀደ ሳይሆን በክብ ስርዓት ነው ፡፡ የሀይማኖታቸው ምልክት የሆነው ኮፍያቸው ላይ ክብ የእደጥበብ ውጤቶች አሏቸው ፡፡ እብዛኛውን ጊዜ እነዚህ በኮፍያዎቻቸው ላይ ያረፉት የክር ስፌቶች ቀለማት ህብር ኪትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተቀድተዋል ፡፡

ፍትህም ክብ ዓለም ነው - ጉራጌዎች ጋ፡፡ የተበደለን ሰው ዕንባ ለማበስ ፣ የበደለም ስለበደሉ ሲከሰስና ጉዳያቸው ጉራጌዎች ማህበራዊ ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ የብቻ ዳኝነት አይሰጥም ፡፡ ሀሳብ ይዋጣል ፡፡ ሀሳቦችን ማካለል ፣ ማሰስ እና ማካበብ አስላጊ ነው ፡፡ ዕቁብም ለመካበብ ፡፡ እድርም ፣ ‘‘ ሳቡኘት’’ ፣ ለመካበብ፡፡

ህይወት ለጉራጌዎች ክብነት ፡፡ መካበብ ...መካበብ....

ቀጣዩ ክፍል ወደ ቀጣይ ቀናት ዞሯል….

(በደራሲና ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ)

37 views0 comments
bottom of page