top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ባለምጡቅ አዕምሮው ታዳጊ ሃምዛ ሃሚድ ዛሬም መብራትን ያለ ገመድ ማሰራጨት ቻለበርካቶች በተገኙበት ስራውን በማቅረብ አንቱታን አትርፏል፡፡ ኢንተርኔት ዋይፋይ ላይ አዲስ ግኝት ይፋ አድርጓል

በጨለማ ውስጥ ያለውን የኅበረተሰብ ክፍል ብርሃን የሚያሳይ የምርምር ሥራ በአንድ ታዳጊ በጎንደር ዩኒቨርሰቲ ተሞክሯል፡፡የምርምር ውጤቱ ባለቤት ሃምዛ ሃሚድ ይባላል፤ በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ መካነ ብርሃን ከተማ ነው የተወለደው፡፡ ሃምዛ ከልጅነቱ ጀምሮ እጆቹ አዲስ ነገር ለመፍጠር የታደሉ እንደሆነ በቅርብ የሚውቁት ይመሰክራሉ፡፡

ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ አዳዲስ ሥራዎችንና አስደናቂ ተሰጦውን ማሳየት የጀመረው ሃምዛ ሃሚድ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ በአካባቢው ካገኛቸው የኤሌክትሮኒክስ ቁርጥራጮች የድምጽ ማጉያ (ማይክራፎን) በመሥራት ለትምህርት ቤቱ አበርክቶ ነበር፡፡

ሃምዛ የድምጽ ማጉያውን በሠራበት ወቅት መንቀሳቀስ የቻለች የአውሮፕላን ሞዴል ሠርቶ እንደነበርም ተናግሯል፡፡በቅርቡ ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ እና በርካቶችን ያስደነቀ ሥራ ይፋ አድርጓል፡፡

የኤሌክትሪክ መብራትን እንደሕልም የሚያዩትን በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ጥያቄ መልስ ሊሰጥ የሚችል ገመድ አልባ የመብራት አገልግሎት በምሁራን ፊት አበርክቷል፡፡ሃምዛ የተወለደባትን የጃናሞራ ወረዳን ጨምሮ በዙሪያው የሚገኙ የበየዳ እና ጠለምት ወረዳዎች በመብራት እጦት የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ታዲያ አዲሱ የሃምዛ የምርምር ውጤት የሚፈታው ይመስላል፡፡

የአካባቢውን የመብራት ችግር እና የመብራት ዝርጋታን ወጭ ሲያጤን ያደገው ሃምዛ ለተወለደበት አካባቢ ብቻም ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለቀሪው ዓለም ቀላል የሆነ ዘዴ አበርክቷል፡፡

ሃምዛ ይፋ ያደረገው ፈጠራው የመብራት ኃይል ያለ ኤሌክትሪክ ገመድ በሚገጠምለት ማስተላለፊያ ብቻ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዝ የሚያስችል ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያው ኃይል ከምንጩ ተነስቶ ጉዳት ሳያደርስና ገመድ ሳይፈልግ ከተገጠመለት የአሌክትሪክ መቀበያ አውታር እንደሚያደርስ ሃምዛ ተናግሯል፡፡ ያለ ገመድ የሚሄደው የኤሌክትሪክ ኃይል ከተገጠመለት ማስራጫ ደርሶ ወደየቤቱ መሠራጨት የሚችል መሆኑንም የፈጠራ ባለቤቱ ተናግሯል፡፡

ገመድ አልባ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያውን የፈጠረው ሃምዛ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔን ጨምሮ በርካታ የዩኒቨርስቲው መምህራን በተገኙበት የተሳካ ሙከራ አድርጓል፡፡

ገመድ አልባው የኤሌክትሪክ ማስተላለፍ ሙከራው 17 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትሮችን የሄደ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ሲውል ረጅም ርቀት ሊሄድ እንደሚችል ሃምዛ አስረድቷል፡፡

ሃምዛ ያለ ኢንተርኔት ገመድ የሚሠራ ‹‹የዋይ-ፋይ›› አገልግሎትም የተሳካ ሙከራ አደርጓል፡፡

ይህ ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት በየቦታው የሚባክኑ ሞገዶችን (ሲግናሎችን) በመሰብስብ በየትኛውም የኢንተርኔት አገልግሎት በሌለበት ቦታ መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ነው ሃምዛ የተናገረው፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ዋና አስተባበሪ አቶ ግርማ ወርቄ ስለሃምዛ እና ሥራዎቹ ‹‹የተለየ ተሰጥኦ አለው፤ ሥራዎቹ በሙሉ በሙከራ የተረጋገጡ ናቸው›› ብለዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል እገዛ እየተደረገለት ፈጠራዎቹን እየሠራ እንደሆነም አቶ ግርማ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሃምዛ ለአለፉት ጥቂት ዓመታት በክረምት እና ባሉት የእረፍት ጊዜያት ከመደበኛ ትምህርቱ ጋር በማይገጭበት መልኩ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየመጣ ይሠራ ነበር፤ አሁንም እየሠራ ነው›› በማለት እየተደረገለት ያለውን እገዛ አብራርተዋል፡፡

በሂደትም ለኢትዮጵያ ስጋት የሆናትን የትራፊክ አደጋ ሊቀንስ የሚችል አዲስ መሳሪያ ይፋ አደረገ፡፡ በሰዓት መልክ ተስርቶ ከእጅ ላይ የሚለበስ እና የመኪና አደጋን የሚከላከል፣ ተሸከርካሪ ከተሸከርካሪ እንዳይጋጭ የሚያደርግ፣ አሽከርካሪዎች እያሽከረከሩ ስልክ እንዳያወሩ የስልካቸውን ኔት ወርክ የሚዘጋ፣ መኪናው ከተፈቀደለት አቅም በላይ ሲጭን ለትራፊክ ፖሊስ መልዕክት የሚያደርስ እና በትራፊኩ እና በሹፌሩ መካከል ያለውን ሙስና ሊያስቆም የሚችል (መኪናው ከተፈቀደለት በላይ ሲጭን እንዳይሄድ የሚያደርግ) መሳሪያ፣ አሽከርካሪው ከተፈቀደለት የፍጥነት መጠን በላይ ሲያሽከረክር ለትራፊክ የሚናገር (መኪናውን የሚያቆም)፣ የመንግሥት መኪናዎች ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጭ ሌላ ቦታ እንዳይሄዱ የሚያደርግ እና ሌሎችን ችግሮችን ሊፈቱ የሚችል አዲስ ቴክኖሎጂ ሠርቷል፡፡ ባለሙዎች በተገኙበትም የተሳካ ሙከራ አድርጓል፡፡ ሃምዛ በ2010ዓ.ም የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሰቲ መግቢያ ፈተና ወስዶ አጥጋቢ ውጤት አስመዝግቧል፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሕንድስና ዘርፍ እንደተመደበም አውቋል፡፡

ከዞን እሰከ ፌዴራል ድርስ ሽልማቶችን እንደወሰደ የሚናገረው ሃምዛ መልካም ግንኙነት ባለው እና መደበኛ ትምህርቱን ለመማር በሚዘጋጅበት በጎንደር ዩኒቨርስቲ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ይሄን ፈጠራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቆረጥ የተቆረጠበትን ቦታ ያለ ምንም ስህተት የሚጠቁም መሳሪያ ሃምዛ መፍጠሩንም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል አስተባበሪው አቶ ግርማ ነግረውናል፡፡

ተማሪው ተመራማሪ ሃምዛ ሃሚድ ለደረሰባቸው የፈጠራ ሥራዎች ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የባለቤትነት ማረጋገጫ ለማግኘት ሂደት መጀመሩንም አቶ ግርማ አስታውቀውናል፡፡

-ታርቆ ክንዴ


59 views0 comments
bottom of page