top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"የሰው ዓመል ዘጠኝ" ሌባው መነኩሴ



አናታስዩስ በግብፅ ውስጥ የሚገኝ ገዳም አበምኔት ፣ አስተዳዳሪ ናቸው ፡፡ በዚህ ፣ እሳቸው በሚያስተዳድሩት ገዳም ውስጥ እጅግ ጥንታዊ የሆኑ ፣ ነገር ግን ጥቂት ቅጂዎች ብቻ ያሏቸው መፃህፍት ነበሩ ፡፡

አንድ ዕለት እነዚህን ጥንታዊ መፃህፍት የመጎብኘት ዕድል ያጋጠመው አንድ መነኩሴ ከመፃህፍቱ መካከል ዕጅግ ምርጥ የሆነውን ሰርቆ ፣ በጉያው ደብቆ ወጣ ፡፡

አበምኔቱ መፅሐፉ ሲሰረቅ አይተዋል ፡፡ ቢሆንም ምንም የተናገሩት ነገር የለም ፡፡ ሰው ልከውም መፅሐፉን መልስ አላሉትም ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰውየው በድንጋጤ መፅሓፉን አልወሰድኩም ይላል የሚል ስጋት ይዟቸው ነው ፡፡ ከዚያም በላይ በሌብነቱ ላይ አልወሰድኩም በማለት የክህደት ተግባር ፈፅሞ በሀጢያት ላይ ሀጢያት ይደመርበታል ብለው አስበዋል ፡፡

መነኩሴው ግን ብቸኛውን መፅሐፍ የሚገዛ ሰው ማፈላለግ ጀምሯል ፡፡በድብቅ አፈላልጎ አንድ የሚገዛው ሰው አገኘ ፡፡ ገዢው ሰው ባለፀጋ ነው ፡፡

ከዚህ በኋላ ባለፀጋው መፅሐፉ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያወጣ ማጥናት እንዲችል መፅሐፉን ለአንድ ቀን ይሰጠው ዘንድ መነኩሴውን ጠየቀው ፡፡ በጠየቀው መሰረት መነኩሴው መፅሐፉን ለባለፀጋው ሰው ሰጠው ፡፡

ባለፀጋው ሰው መፅሐፉን ተቀብሎ በቀጥታ የመጣው ወደ ገዳሙ ነው ፡፡ ገዳም መጥቶ መፅሐፉ ዋጋ ያወጣ እንደሁ ፣አያወጣ እንደሁ ለአናታስዩስ ጠየቃቸው ፡፡ መፅሐፉን ገና እንዳዩት ነው ለይተው ያወቁት ፡፡ ብቸኛ መፅሐፍ ነውና ፡፡ ያወቁት ቢሆንም ግን ምንም ቃል አልተነፈሱም ፡፡

ባለፀጋው ሰው ፣ ‘‘ አንድ መነኩሴ ነው ሊሸጥልኝ ያመጣው ፡፡ በወርቅ እንድለውጠው ነው የጠየቀኝ ፡፡ እርሶ ስለዚህ መፅሐፍ ምን ያውቃሉ ? ይህ መፅሐፍ እርሱ እንደሚለው ዋጋ ያወጣል ? ’’ ፣ አላቸው ፡፡

‘‘ ከዚያም በላይ የሚያወጣ ፤ እጅግ ውድ ፣ አጅግ የከበረ መፅሐፍ ነው ’’ ፣ አሉት ፡፡ በለፀጋው ሰው አናታስዩስን አመስግኖ ተመለሰ ፡፡

በማግስቱ መነኩሴው መጣ ፡፡ ባለፀጋው ሰው መፅሐፉን ሊገዛ መዘጋጀቱንና የጠየቀውን ዋጋ ሊከፍለው መወሰኑንም ገለፀለት ፡፡ መነኩሴው አብዝቶ ተደሰተ ፡-

‘‘ ለማን አሳየኸው ? ’’ ፣ ሲልም ባለፀጋውን ጠየቀው ፡፡

‘‘ ለኣናታስዩስ ፣ ለአበምኔቱ ’’

የመነኩሴው ፊት በድንጋጤ ክው አለ ፡፡ አመዱ ቡን አለ ፡፡

‘‘ እና እ… እርሳቸው ፣ ስታሳያቸው ምን አሉህ ? ’’ ፣ ጠየቀ ፡፡

‘‘ መፅሓፉ ዋጋ ያለው መፅሐፍ መሆኑን ነገሩኝ ’’

‘‘ ሌላስ ምን አሉህ ? ’’

‘‘ሌላ ምንም ’’

መነኩሴው በሁለት ነገሮች ልቡ ተነካ ፡፡ አበምኔቱ በዚህ የተሰረቀ መፅሐፍ ተከሶ እስር ቤት እንዲጣል ፣ እስር ቤት ተወርውሮ መከራ እንዲገፋ አልፈለጉም ፡፡ ሌላም ማንም እንዲህ ያለ ትዕግስት የተሞላበት ፍቅር አልብሶት አያውቅም ፡፡

‘‘ ሀሳቤን ለውጫለሁ ፡፡ መፅሐፉን አልሸጥም ! ’’

‘‘ የጠየቅከኝን ሁለት እጥፍ አድርጌ እሰጥሃለሁ ’’

መነኩሴው ከባለፀጋው እጅ መፅሐፉን ተቀብሎ ወደ ገዳሙ ገሰገሰ ፡፡ አይኖቹ ዕንባ እያጎረፉ ፣ ያንን የከበረ መፅሐፍ ለአበምኔቱ ፣ ‘‘ እንኩ ’’ ፣ አላቸው ፡፡

‘‘ አንተው ጋ ይቆይ ፡፡ እኔ የገባኝ መፅሐፉን እንደተዋስከኝ ነበር ፡፡ ስለዚህ አንተው ጋ ይቆይ ’’ ፣ አሉት ፡፡

‘‘ ከንግዲህ የትም አልሄድም ፡፡ እርሶ እያስተማሩኝ እዚሁ እኖራለሁ ’’ ፣ አለ ፡፡

ዘመኑን በሙሉ የርሳቸውን አርያነት ተከትሎ አሳለፈ ፡፡

‘‘ የስው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ ’’


22 views0 comments
bottom of page