• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እስከ  ካርሙጆ - ክፍል 2(ማስታወሻነቱ በለዛ ጫወታው ለማረከኝ የሀመር ወጣት ፣ አይኬ ኦይታ)

“ወስን እንጂ ድንበር የለም” (ንኡስ ርዕስ)

ካንጋቴን ከተማ፡፡ ከ7 እና 8 ዓመታት በፊት፡፡ ከጂንካ የተነሳ ሰው ካንጋቴን ከተማ ላይ ለማረፍ፡፡ ጉዞው በመኪና ከሆነ፡፡ የኦሞን ወንዝ መሻገር አለበት፡፡ የዚያን ጊዜ መሸጋገሪያው በዕጅ የሚቀዘፍ ጀልባ ነበር፡፡

ከሁለት አመት በፊት፡፡ ወንዙን የሚያሻግሩት ጀልበኞች የሉም፡፡ ምን አጠፋቸው?

ካንጋቴን ከተማን አቋርጦ ወደ ቁጥር አምስት ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት የሚያደርስ የአስፓልት መንገድ እየተገነባ ነው፡፡ ኩባንያው ወንዙን የሚያሻግር ተገጣጣሚ ድልድይ ገንብቷል፡፡ የተገነባው ጊዜያዊ ድልድይ ጀልበኞቹን ከውድድር ውጪ አድርጓቸው ጠፉ፡፡

አሁን፡፡ ተገጣጣሚው ጊዜያዊ የብረት ድልድይ ጠፍቷል፡፡ ምን አጠፋው ?

ጀልባዎቹ እና ጀልበኞቹ አይደሉም፡፡ የዘመነ እንጂ ወደኋላ የተመለሰ ነገር ስለሌለ፡፡ ተገጣጣሚው ጊዜያዊ ድልድይ በኮንክሪት ድልድይ ተገፍትሯል፡፡ ረጅም ነው ድልድዩ፡፡ ከ70 እስከ 80 ሜትር የሚደርስ፡፡

እዚህ የተንጣለለ የኮንክሪት ድልድይ ላይ ቆሞ ወደምዕራብ አቅጣጫ የሚመለከት ሰው፡፡ የመመልከቻው ሰዓት ጀንበር ስታቆለቁል የሆነ እንደሆነ፡፡ የኦሞ ወንዝ ድንበርም መስመርም የማያውቀው ፡፡ ይፈሳል፡፡ ወደማረፊያው ሩዶልፍ ሀይቅ ከነግሳንግሱ ይነጉዳል፡፡ በዚህ ሰዓት ግን ቀን በታየበት ድፍርስ ልብሱ ሳይሆን ከምታሽቆለቁለው የምሽት ጀንበር የተለገሰውን የወርቅ ካባ ደርቦ ነው፡፡ ከወንዙ እስከ ምዕራብ አድማስ፣ ባሻገር ህልም መስለው እስከሚታዩት የኬንያ ተራሮች ድረስ ወርቃማው ቀለም ተነጥፎበታል፡፡ ንጣፉ የድንበር ምልክት የለውም፡፡

በአካባቢው፣በደቡብ ኦሞ ውስጥ ከሚኖሩት ብሄር ብሄረሰቦች መካከል የኛንጋቶም ብሄረሰብ የኑሮ መልህቁን ዘርግቷል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ባሉ ሀገሮች መካከል የወሰን መስመር እንጂ ድንበር የለም የተባለው እውነት ነው፡፡

የኛንጋቶም ብሄረሰብ አሁን በድንበር ሳይሆን በመስመር ወደተለየው አካባቢ ሰፍሮ ህይወቱን መግፋት ከመጀመሩ በፊት የቀድሞ መኖሪያው ኡጋንዳ ነበረች፡፡ ኡጋንዳ ውስጥ ካርሞጆ ከተሰኘው ብሄረሰብ ነው የፈለሰው፡፡

በኛንጋቶም ብሄረሰብ አባቶች ዘንድ ስለአፈላለሱ አፈታሪክ ይነገራል፡-

ኡጋንዳ ውስጥ በሚኖሩበት፣ በዚያ ረጅም የኋሊዮሽ የዘመን ገመድ ባለው ጊዜ ፣ አንድ ኮርማ ጠፋ፡፡ ጉልበተ ብርቱ የሆኑ ሰዎችይህንን ኮርማ ፍለጋ ወጡ፡፡

የኮርማውን ዱካ እየተከተሉ ተጓዙ፡፡ እየተጓዙ፣ እየተጓዙ እስከ ኪቢሽ ወንዝ መጡ፡፡ ኮርማውን የሳርም የውሃም ጎተራ በሆነው ኪቢሽ አካባቢ አገኙት፡፡

የዚያን ጊዜ የካርሞጆ ልጆች ኪቢሽ ወንዝ አካባቢ እስኪደርሱ ድንበርም መስመርም ፣የድንበርና የመስመር ከልካይም አልነበረባቸውም፡፡ ኪቢሽ አካባቢ ለደረሱት እና የጠፋባቸውን ኮርማ ላገኙት ወጣቶች ከኮርማው መገኘት በላይ ደስታቸው አካባቢው በሳር እና በውሃ በረከቶች መባረኩ ነበር፡፡ ምክንያቱስ?

እዛ ፣ኡጋንዳ ሳርና ውሃ የሉም?

ካርሞጆዎች በሚኖሩበት የኡጋንዳ አካባቢ ድርቅ ተከስቶ ነበር፡፡ ወጣቶቹ ተመልሰው ሄዱ ፡፡ ወደ ኡጋንዳ ፡፡ ከኪቢሽ ወደ ኡጋንዳ ተመልሰው ሲሄዱ፣ ከዘመዶቻቸው ጋር መቀላቀልን የሚከለክል ወሰን ድንበርም ሰውም አልነበሩም፡፡ ለዘመኑ ሰዎች የኑሮ በረከቶች ከነጠፉበት ምድር፣ የኑሮ የህይወት በርከቶች ወደ ተትረፈረፉበት ምድር በመሄድም በመምጣትም ከልካይ ወሰን ፣ ገዳቢ ድንበር ፣ ጠባቂ ኬላም አልነበረባቸውም፡፡

የካርሞጆ ሰዎች፣ የወይፈን ዱካ ተከትለው በመምጣታቸው ምክንያት ለኑሮ የሚሆኑ በሽበሽ በረከቶች ያሉበት ምድር ስለማግኘታቸው ተናገሩ፡፡ የተወሰኑ ወገኖቻቸውን አስከትለው ዳግም ወደ ኪቢሽ ተመለሱ፡፡ እናቶችና ህፃናትም አብረውም መጡ፡፡

ከኡጋንዳ ተነስተው ወዲህ ማዶ ከመጡ በኋላ ዝሆን አድነዋል፡፡ ኩራዝ ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ ፡፡ ለመብል እንዲሆናቸው ያደኑትን ዝሆን ለምግብነት በመጠቀም በኩል ግን የሀሳብ ልዩነቶች ተፈጥረዋል፡፡ እኩሌታው የዝሆኑ ስጋ ተዘልዝሎ፣ ቋንጣ ሆኖ ይበላ አሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ቋንጣ ሳይሆን ጥሬው የዝሆኑ ስጋ በእሳት በስሎ መበላት አለበት አሉ፡፡

“ቶዎሳ” በኛንጋቶም ቋንቋ ቋንጣ ማለት ነው፡፡ “ማቶም” ማለት፣ ጥሬ ሆኖ በዕሳት የበሰለ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡“እኛ” ማለት ደግሞ መብላት ነው፡፡ ቋንጣውን እንብላ፣ “እኝቶምሳ” ፡፡ ጥሬ የበሰለ፣ “እኛ ማቶ”

“እኛ ማቶም” ያሉት፣ ኛንጋቶም፡፡ እኝቶዎሳ ያሉት ቶፓስ፡፡ በጊዜ ሂደት ይኸው ክስተት የተለያዩ ብሄረሰቦች መጠሪያ እንደሆነ ነው የኛንጋቶም የታሪክ አባቶች የሚናገሩት፡፡

አንድ የቀረ ነገር አለ፡፡ “ኡቱር” በኛንጋቶም ቋንቋ አበባ ማለት ነው፡፡ “ኡቱር ኛማ” አበባ የሚበላ፡፡ በጊዜ ሂደት ይኸው ክስተት በተመሳሳይ “ቱርካና” ለተሰኘው ብሄረሰብ መጠሪያ ሊሆን ችሏል፡፡

ከወሰንና ከድንበር በኋላ ፣ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ከተቀራመቱ በኋላ፣ በኛንጋቶም፣ በቶፖሳ፣ በካርሞጀ እና በቱርካናዎች መካከል መለያየት ሊፈጠር ችሏል፡፡ ቅኝ ገዢዎች የፈጠሯቸው ወስንና ድንበሮች ካልሆኑ በቀር በአራቱም ብሄረሰቦች መካከል የባህልና የቋንቋ ልዩነቶች የሉም፡፡ ነገር ግን ወሰንና ድንበሮቹ ካርሞጆዎችን ኡጋንዳ ውስጥ፡፡ ቶፖሳዎችን ደቡብ ሱዳን ውስጥ፡፡ ቱርካናዎችን ኬንያ ውስጥ፡፡ ኛንጋቶሞችን ኢትዮጵያ ውስጥ ከልሏቸዋል፡፡ ነገር ግን በነዚህ ህዝቦች መካከል ተራ የወሰን ግጭቶች ካልሆኑ በቀር ዛሬም ድረስ በመካከላቸው የስነ-ልቦና ስንጣቆ፣ የባህል ትርታሮዎች የሉም ማለት ይቻላል፡፡

ለዚህም ይመስላል በቅርቡ ኛንጋቶሞችንና ቱርካናዎችን ለማቀራረብ ኬንያ ውስጥ የተዘጋጀ በዓል ላይ ተካፍላ የተመለሰች አንዲት የኛንጋቶም ሴት የለበሰችው ካናቴራ ጀርባ ላይ የተፃፈው መልዕክት የሚናገረው እውነትም ይህንኑ ነው፡፡ “ Wel come to Home land” ይላል፡፡

ሁለት አገር፡፡ የሁለት አገር ወሰንና ድንበር ቢኖሩም ፡፡ ህዝቦቹ ወሰንና ድንበሩ ሳይገድባቸው አንድ ህዝብ፣ አንድ ሆነው ሁለት አገር ያላቸው እስኪመስል ድረስ የሚቀራረቡት፡፡ ወሰን እንጂ ድንበር የለሽነት ፡፡ ልክ በነፃነት እንደሚፈሰው የኦሞ ወንዝ፡፡ በነፃነት ወሰን እና ድንበር የለሹን ሰማይ ያለከልካይ እንዳሚያካልሉት የሰማይ ላይ ወፎች፣ ለኑሯቸው ዋስትና ወደሆነው ምድር፡፡ ለህልውናቸው ቤዛ ወዳገኙበት መጠለያ በየጊዜው ወዲህና ወዲያ እንደሚመላለሱት የሰማይ ወፎች ማለት ነው፡፡


28 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean