top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እስከ ካርሙጆ - ክፍል ሶስት


ትውልድና ስነምግባር


በኛንጋቶም ብሄረሰብ ዘንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ አስተዳደጉ ላይ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ፡፡ ህፃኑ አንድ ዓመት እስኪሞላው ድረስ እንክብካቤውን የሚያገኘው ዘጠኝ ወር በማህፀኗ ከተሸከመችው፣ አምጣ በመውለድ ወደዚህ አለም ከቀላቀለችው እናቱ ነው፡፡

ህፃኑ አድጎ እድሜው ለከብት ጥበቃ ሲደርስ የአባቱን እግር ተከትሎ ወደ ግጦሽ መስክ ይወጣል፡፡ ይህ እንግዲህ ከብት መጠበቅ ብቸኛው አማራጭ በሆነባቸው ዘመናት ነው፡፡ ጋሼ አሪክ እንደሚናገሩት ግን አሁን፣ በዚህ ዘመን፣ የትምህርት ቤት ደጃፎችን አልፎ ቀለም የመቅሰም ዕድሎችም አሉት፡፡

ያባቱን እግር ተከትሎ ለከብቶች ጥበቃ የሚወጣው ህፃን መጀመሪያ አካባቢ ውሎዎቹ ከጥጆችና ግልገሎች ጋር ነው፡፡ ከጥጆችና ግልገሎች ጋር አየቦረቀ የሚያድገው ህጻን፣ ወደ ወጣትነት ሲሸጋገር፣ ከእድሜ አቻና ተቀራራቢዎች ጋር ተደምሮ ስያሜ ይወጣለታል፡፡ በኛንጋቶሞች የኢትዮጵያን መሬት ከረገጡ በኋላ ትውልድ ስያሜዎች እየተሰጡት ነው ዛሬ ላይ ደረሰው፡፡

በኛንጋቶም ብሄረሰብ ዘንድ እያንዳንዱ ትውልድ ስያሜ የሚያገኝበት ስርዓት አለ፡፡ የመጀመሪያው ትውልድ ቀዳሚዎቹ የሰው ዘሮች፣ ይህችን ምድር ቀድመው የረገጡቱ፣ በብሄረሰቡ አጠራር “ ngisekop -” ይሰኛሉ፡፡

ቀዳሚዎቹ የኛንጋቶም የሰው ዘሮች ወደዚህች ምድር ብቻቸውን አልተከሰቱም፡፡ ሁሉም የሰው ዘሮች ከሰማይ እንደወረዱ ኛንጋቶሞች ያምናሉ፡፡ ነገሩ እንደዚህ ነው በኛንጋቶሞች እምነት መሰረት ፡-

ከምድር እስከ ሰማይ በፈጣሪ አማካኝነት ገመድ ተዘረጋ፡፡ በዚህ በተዘረጋ ገመድ በመንሸራተት ወይም ተንጠልጥሎ በመውረድ ነው ሁሉም የሰው ዘሮች መሬትን መርገጥ የቻሉት፡፡ ጉራጌውም፣ ኦሮሞውም፣ ሐመሩም፣ አማራውም፣ ትግሬውም፣….፡፡ ሁሉንም በአንድ ሌሊት ነው ፈጣሪ ወደዚህች ምድር በልዩነት ያወረዳቸው፡፡ የየራሳቸውን ማንነት እና ቋንቋም እንደያዙ ጭምር፡፡

ከዚህ የብሄረሰቡ ሀተታ ተፈጥሮ የምንረዳው ነገር አለ፡፡ ብሄረሰቡ በዚህ የእምነት አስተሳሰቡ መነጽር ሲታይ ልዩነትን የሚቀበል ስለመሆኑ ፡፡ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ እና የተፈጥሮ ፀጋዎችም ስለመሆናቸው ነው የሚነግረን፡፡

በዚሁ የልዩነት ተፈጥሯዊ ክስተት ምክንያት ከተፈጠሩት መካከልም የኛንጋቶም ብሄረሰብ ራሱን ይደምራል፡፡ በዚህም የራሱን ማንነት እና ቋንቋ ይዞ ከሰማይ እስከ ምድር በተዘረጋው ወፍራም ገመድ ተንጠላጥለው መሬት ላይ ያረፉት የመጀመሪያዎቹ የኛንጋቶሞች የትውልድ መጠሪያ ኒፓላጆም ወይም ቀዳሚዎች የሚል ስያሜ እንዳለው ነው የሚነገረው፡፡ ከዚህ ትውልድ ቀጥሎ በኛንጋቶም ብሄረሰብ ታሪክ ውስጥ ያለፈው፡፡ “ ngisekop -” በኩር ወይም የቆዳ ልብስ ለባሾች ናቸው፡፡ ይህ ትውልድ ከአደን የሚያገኘውን የእንስሳት ቆዳ ለብሶ በመገኘቱም ነው ስያሜውን መለያው ያደረገው፡፡

በኛንጋቶም ብሄረሰብ ዘንድ፣ ከተናጥል ኑሮ ማህበራዊ ኑሮን መስርቶ ህይወት መግፋት የተጀመረው ከኒፓላጆም ቀጥሎ ባለው ትውልድ ዘመን ነው፡፡ “ ngimoru ” በማህበር፣ ተሰባስቦ በመንደር የመኖርና ጋብቻ እየመሰረቱ በአብሮነት ህይወትን መግፋት የተጀመረበት የታሪክ ወቅት ሆኖ በኛንጋቶም አባቶች ዘንድ ይነሳል፡፡

ከዚህ በኋላ የመጣው ትውልድ “እሞር” ተራራ ላይ የኖሩቱ የሚል እንድምታ አለው፡፡ ኑሯቸው ከተራራ ተራራ በመንቀሳቀስ ላይ የተገነባ በመሆኑ ነው ይህ ስያሜ ሊሰጥ የቻለው፡፡ ጠንካሮች፣ ተዋጊዎችም ጭምር ነበሩ፡፡

ኝሞሩዎች፣ ዝሆኖቹን ወይም በብሄረሰቡ አጠራር “ngitome-” ዎችን ወልደዋል፡፡ በዚህ ትውልድ ዘመንም ነው ሀብት ማከማቸት፣ሀብት መፍጠር ለህልውና የጀርባ አጥንት ስለመሆኑ ከፍ ያለ አስተሳሰብ የተያዘበት፡፡ ይህንኑ አስተሳሰብ ተከትሎም ሀብት የፈጠሩ የብሄረሰቡ አባላት በዝሆን ጥርስ ማጌጥን መለያቸው አድርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ነው ዝሆኖቹ የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሀብት ያከማቸ ትውልድ በመሆኑ ከቀደሙት ይልቅ በሰውነት ግዝፈቱ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም እንደዝሆን ጩኸት ሁሉ በድምፆቻቸው ከፍታ፣ ሲናገሩ በሚያሰሙት የጎላ ድምጽ ሀይል፣ ጠላቶቻቸውን የሚያስደነግጡ ጭምር ነበሩ፡፡

ዝሆኖቹ ፣ (nginggorukopir) ሰጎኖቹን ወልደዋል፡፡ ሰጎኖች በተክለ ሰውነታቸው ከዝሆኖቹ ጋር የሚነፃጸሩ አይደለም፡፡ ቀጫጭኖች ናቸው፡፡ ነገር ግን በቅልጥፍና እና እንደሰጎን ሁሉ ባላቸው የሩጫ ሀይል ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ እንደሰጎን ፈጣኖች ናቸው፡፡ ይኸው ፍጥነታቸው የሚበሉትን ነገር አድኖ ለመያዝ ሀይል ሆኗቸዋል፡፡ በወቅቱ ለተከሰቱት የተፈጥሮ ችግሮችም ይህንኑ ተከትሎ የመጣውን የምግብ እጦት መቋቋም ችለዋል፡፡

ከሰጎኖቹ አብራክ ተወልደዋል(gningolotiang) ዋልያዎቹ፡፡ ዋልያዎቹ ተለይተው የሚታወቁት እንደፍየል ከልሳናቸው የቀጠነ ድምፅ ይወጣቸው ነበር ፡፡ እርስ በርስ መግባባት የሌለው፣ መደማመጥ የጎደለው ነበርም መለያ ባህሪያቸው ፡፡ የእርስ በርስ መጯጯሁ ብቻ ሳይሆን ይህ ትውልድ ለአባቶቹም መታዘዝ የሌለው ፣ የአባቶቹን ምክር የማዳመጥ ስክነት የጎደለው በመሆኑ ነው ስያሜው የተሰጠው፡፡

ጎሽ የሚባለው እንስሳ በቆሰለ ጊዜ፣ ከተጨማሪ የመቁሰል አደጋ ለማምለጥ ወደፊት ይሮጣል፡፡ ለማምለጥ ይሩጥ እንጂ ዳግም ወደኋላ የመመለስና በጠላቱ ላይ መልሶ ጥቃት የመፈጸም ተግባር የማከናወን ባህሪ አለው፡፡ ይህንን የሚያደርገውም ጥቃት የፈጸመብኝ አካል አሁንም ይከተለኛል፣ እየተከተለኝ ነው የሚል ባህሪ ባለቤት በመሆኑ ነው፡፡ የሰጎኖቹ አባቶች ተንበርክከው በድካማቸው ሀይል ያመጧቸው ትውልዶች መጠሪያም የዚሁ ጠባይ ባለቤቶች በመሆናቸው ምክንያት ይኸው ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እና ይህ ትውልድ በብሄረሰቡ ታሪክ ውስጥ እንደ አደጋም ነው ተደርጎ የሚወሰደው፡፡

የዛሬው ትውልድ መጠሪያ ሳላ ነው፡፡ ሳላዎች፣ ተግባቢዎች፣ ከሌሎች የብሄረሰቡ አባላት ካልሆኑ ሰዎች ጋር በፍፁም መግባባት፣ በፍፁም ፍቅር፣ እንደ ሳላ ሁሉ በየዋህነት ፀባይ በሞላው የግንኙነት መሠረት ላይ የቆሙ ናቸው፡፡


14 views0 comments
bottom of page