top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የፌዴራሊዝሙ ትኩሳት እስከ የት? (በሳዲቅ አህመድ ኡስማን)

Updated: Jul 4, 2020



በፌዴራሊዝሙ ትኩሳት ተጨናንቆ ፥ ደም ተቃባ መስቃንና ማረቆ! ዜጎች ባገሪቱ ውስጥ እንዳሻቸው ተንቀሳቅሰው የመኖርና የመስራት መብታቸው የፌዴራል ስርዓቱ የሚያከብረው ቢሆንም በብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ስም የገነነው ዘረኝነት ለአገሪቷ ስጋት ሆኗል። በሶማሊ ክልል ዉስጥ ልዩ ፖሊስን አደራጅቶ የነበረው የአብዲ ኢሌ መንግስት ዜጎችን መግደሉና ማፈናቀሉ ሳያንሰው ህገወጥ በሆነ መልኩ እገነጠላለሁ ብሎ ሲያስፈራራ በነሐሴ 01/2010 አብዲ ኢሌና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ልብ ይሏል። በክልሎች ውስጥ ያለው የስልጣን መዋቅር ዘርን መስረት ያደረገ ሆኗል።ፌዴራል ክልሎች በዘር ተካለዋል።ሰዎች በዘራቸው ምክንያት ሲፈናቀሉ፣ሲገደሉና ንብረታቸውን ሲያጡ የፌዴራል ስርዓቱ እንደ አምቡላንስ ፈጥኖ ደርሶላቸዋልን?የክልል ይገባኛል ባይነት፣የዞን ይገባኛል ባይነት፣የወረዳ ይገባኛል ባይነት፣የቀበሌ ይገባኛል ባይነት በፌዴራሊዝም ስርዓት ዉስጥ የተጠመዱ ፈንጂዎች ቢሆኑም «የለም በዘር መደራጀቱ ይሰራል» የሚሉ ድምጾች ጎልተው ይሰማሉ። ዲሞክራሲንና ህግን መሰረት ያላደረገ ፌዴራሊዝም ስርዓት ምን ያህል ዉጤታማ ይሆናል? የሚለው ታላቅ ዉይይት የሚያሻው ነው።ስር እየሰደደ የመጣው ዘረኝነት እልባት ካላገኘ ኢትዮጵያ ስጋት ላይ መሆኗ አይካድም። ዘርን መሰረት ባደረገ አወቃቅቀር በማንነትና በይገባኛል ባይነት እየተናጠች ያለችዋን ደቡብ ክልል በመቃኘት የሰሞኑን የመስቃንና ማረቆ ወረዳ ግጭት እንዳሳለን። #በ1997ቱ_ምርጫ_በመስቃን_ወረዳ_የተሸነፈው_ኢህአዴግ ኢህአዴግ የሚባለውን የፖለቲካ ፓርቲ ህዝቡ አልተቀበለውም።በ1997ቱ መርጫ በመስቃን ወረዳ ኢህአዴግ ሽንፈትን ተጎናጽፏል።ቅንጅት በወረዳው ተወዳድሮ ኢህአዴግን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቷል።ኢህአዴግ ቅንጅትን ወንጀለኛ አድርጎ፣መሪዎችን ሲያስርና 200 ሰዎችን ሲገደል የመስቃን ወረዳ የቅዋሜ ፖለቲካ አብሮ መጠቃት ጀመረ። ቅንጅትን ወክለው በመስቃን ወረዳ ተወዳድረው ከነበሩት ወጣቶች መካከል አቶ መሐመድ አህመድ ኬረታ ወልቂጤ ከተማ አልቤርጎ ዉስጥ ሞቶ ተገኝቷል።በመስቃን ወረዳ የቅንጅት የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪ የነበረው አቶ ፋንቱ ሰለሞን ለህክምና ምርመራ አዲስ አበበባ አቅንቶ በእሬሳ ሳጥን ተመልሷል።ክስተቱ የቅዋሜ ፖለቲካን ለሚያራምዱ የወረዳው ተወላጆች የማስጠንቀቂያ ደዎል ሆኗል። ኢህአዴግን መቃወም ያስፈራም ነበር። በ1997 ኢህአዴግን በመቃወም ከተወዳደሩት ወጣቶች መካከል ሰናይት ለማ ሙሳ አገርን ለቃ ተሰዳለች በማለት የሚያስረዱት የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች ቀሪው አቶ መሐመድ ሐሰን አሽባሪ የሚባለው ፍረጃ እንዳይጣልበት በመስጋት በፖለቲካዉ ምህዳር ዉስጥ የነበረው ሚና ለአመታት ደብዛዛ ነበር ሲሉ ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ ዉስጥ የአንድ ፓርቲ የበላይነት ሰማይ ጠቀስ ሆነ።ህወሃት በሜቴክና በኢፈርት ባደለባቸው ጀነራሎቹ የሚቆጣጠረው የጦር ሐይል የኢትዮጵያን ህዝብ በፖለቲካዊ ቀምበር ጠምዶት የነጻነት ምሉእነትን አመከነው።አገር የዜጎች ሁሉ መሆኗ ቀርቶ «ከደደቢት» ጫካ ተነስተው አዲስ አበባ የደረሱ የጥቂት የህወሃት ዘራፊዎች ሆነች።በአምባገነናዊነት የከነፈው ህወሃት ተንደርድሮ በኢትዮጵያዊያን የእምነት ተቋም ዉስጥ ገባ። ለህወሃት ነገሮች አልጋባልጋ እልነበሩም «ድምጻችን ይሰማ የሚባል» ኬላ ገጠመው።የድምጻችን ይሰማ የለውጥ ቅላጼ ተመመ።የዚህን ሰላማዊ ትግል ዘለበት ወልቂጤ፣ወራቤና ሻሸመኔን የመሰሉ ከተሞች ሲያጠልቁ ቡታጅራ ዘግይታ ነበር። በ1997 የቅንጅት ምርጫ በፖለቲካዊ ቶርቸር ፍዳቸውን ያዩት የቡታጅራ ከተማ ወጣቶች ዳግም በመነሳት ያንን የድምጻችን ይሰማ የለውጥ ቅላጼ ማዜም አልቻሉም።ከወረዳ እስከ ዞን፣ከዞን እስከ ክልል በኢህአዲጋዊ-አፍቅሮት የናጠጡ፣ በስልጣን ምህዋር ውስጥ በዉዴታም ይሁን በግዴታ የተወነጨፉ፣በህወሃታዊ ወጥመድና በጥቅም የተጠለፉ ፖለቲከኞች የመስቃንን ወረዳ ህዝብ አሽመደመዱት።ህዝቡን ለኢህአዴግ ሰግዶ-አዳሪ ይሆን ዘንድ በጅ አዙር ጠየቁት። ህዝቡ እምቢኝ አለ።አነገትን ደፍቶ ከመኖር አንገትን ቀና አድርጎ አገራዊ ለውጥን ማምጣቱን መረጠ።ይህ እምቢተኝነት የመስቃን ወረዳ ህዝብን ዋጋ አስከፈለው።ከደቡቧ መዲና ሐዋሳ እስከ አንዲት የገጠር ቀበሌ ባለው አስተዳደራዊ መዋቅር ዉስጥ ሴራ ይሸረብበት ገባ።የመስቃን ወረዳ የቆዳ ስፋትን ለመሸራርፍ መሞከሩ፣ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የሴራ ጸብን መጫሩ፣ ቤት ንበረት መውደሙ፣ሰዎች መገደላቸውና መፈናቀላቸው የዚሁ የሴራ ፖለቲካ አካል ነው ሲሉ የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች ያስረዳሉ። #ድንገተኛው_የቡታጅራ_ተቃዉሞ_እና_ዶክተር_አብይን_ለመደገፍየተደረው_ሰልፍ ጥር 23/2008 በቡታጅራ ከተማ ዉስጥ የተቃዉሞ ሰልፍ ተደረገ።ለመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች ቀኗ ታሪካዊ ነበረች።የድምጻችን ይሰማ ትግል ተልእኮውን ለቄሮና ፋኖ ሲያሻግር በደቡብ ክልል ዉስጥ ካሉት ታዋቂ ከተሞች በመቅደም ቡታጅራ «እምቢኝ» ማለቷን አበሰረች።ከ1997ቱ ፖለቲካዊ ምት በሗላ የተስተዋለ ቅዋሜ በመሆኑ ለአንድ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት ላደሩ ኢህአዴጋዉያን ተቃዉሞው ጥሩ ስሜት አልፈጥረም። ፖሊሶች ህዝቡን መቆጣጠር ተስኖአቸዉ በህዝብ ቁጥጥር ስር የዋሉበት አጋጣሚ እንደነበር የሰልፉ ታዳሚዎች አስረድተዋል። ለመደብደብ የሞከሩ ፖሊሶች ተደበደቡ።ለመተኮስና ለመግደል የሞከሩ ታጣቂ ፖሊሶች መሳሪያቸውን ተቀሙ። በተቃዉሞው ሰልፍ ላይ ህዝባዊ እሮሮ ተሰማ። «መንግስት ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነዉን መሬት እየቀማ ለኢንቨስተሮች ይሰጥብናል። ተወልደን ባደግነበት ቀዬ እንድንፈናቀል ተደርገናል።መንግስት ዘንድ ለአቤቱታ የተላኩ የህዝብ ወኪሎች ታስረዋል። የአዲስ አበባውን ማስተር ፕላን የሚመስል የማፈናቀያ ቅጽ ለኛ ተዘጋጅቶልናል» ያሉት ሰልፈኞች ህወሃት ይመራዋል ያሉትን መንግስት «...ሌባ...ሌባ...» ሲሉ ተደምጠው ነበር። ይህ የቅዋሜ መንፈስ በከተማና በገጠሩ ዉስጥ ዘለገ።ህዝቡ አጋጣሚን ጠባቂ ሆነ።ጠ/ሚ ሐይለማሪያም ደሳለኝ በየካቲት 08/2010 ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።ዶ/ር አብይ አህመድ በቦታቸው ተተኩ።ይህ በመስቃን ወረዳ ዉስጥ ላሉ ነዋሪዎች «የተስፋ ብስራት» ቢሆንም ጥርስ የነከሱ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት ምን ያደርጉ ይሆን? የሚል ጥያቄ አብሮ ተነስቶ ነበር። ሰኔ 16/2010 በጠ/ሚ አብይ አህመድ ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉ የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎችን አስቆጣ። የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች በዘር፣በሐይማኖት ሳይለያዩ በሰኔ 23/2010 ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።ሰላማዊ ሰልፉ በኢትዮጵያ ከተሞች ተደረጉ ከተባሉት ሰልፎች መካከል በትልቅነቱ የሚወሳ ነበር።ህዝቡ ለተጎጅዎች ደም ለግሶ ታሪክን ሰርቷል።ያ ሰልፍ በቡታጅራ ከተማና በመስቃን ወረዳ ለሚገኙ ለውጥ ፈላጊ ወገኖች ጥርስ ቢያስነክስባቸውም «ተደምረናል» በሚሉት ቀመር ለውጡን ደጋፊ ሆኑ። #የመስከረምና_የህዳር_ሁከት_እንዴት? አዲሱ አመት አዲስ ተስፋን ሰንቆ ነበር። ለ27 አመታት በኢትዮጵያዉያን ጫንቃ ላይ ተደላድሎ የሻገተው ህወሃታዊ አገዛዝ በዲሞክራሲ ይለወጥ ዘንድ አዲሱ አመት ላይ የለውጥ ካስማ መተከሉ ቀጥሏል። የመደመሩ ስሌት ገባን ያሉ፣የመደመሩን ስሌት እናሰላለን ያሉ የደቡብ ክልል ነዋሪዎች በተስፋ ወደፊት መጓዛቸውን ቀጠሉ። የተተከለውን የለውጥ ካስማ የሚነቅሉ፣ በቢሮክራሲው ዉስጥ የተጠቀጠቁ አስመሳዮች ህዝቡን እረፍት ነሱት።የህብረ-ብሔሮች መገኛ፣ልዩነትን በአንድነትን ለማዋሃድ ተምሳሊት ሆና የቆየችዋ ደቡብ ክልል በርስ በርስ ግጭት መናጧ ቀጠለ። ቀደም ሲል በጉራጌና በቀቤና ቤተሰቦች መካከል ግጭት ሲነሳ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ወደ ወልቂጤ ማምራታቸውን አይዘነጋም። ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሐዋሳ ዉስጥ በሲዳማ እና በወላይታ ቤተሰቦች መካከል የተነሳው ግጭትን ለማብረድ ጠ/ሚው ሐዋሳ በመሄድ የማስታረቅ ስራን ሰርተዋል።በሳጃ ከተማ ውስጥ በየምና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል የተነሳው ግጭት ዘግናኝ እንደነበር የሚታወስ ነው። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ዉስጥ በጉሙዝ፣በኦሮሞና በአማራ ተወላጆች መካከል የነገሰው ዉጥረት ለንጹሗን ዜጎች መሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።በሶማሊና በኦሮሚያ ክልልሎች በተነሱት የዘር ግጭቶች የደረሰው ጥፋት ከባድ ነው። በአዲስ እበባ እቅራቢያ ቡራዩ ዉስጥ በመስከረም መባቻ በንጹሗን ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት ሲፈጸም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች የርስ በርስ እልቂት ዜጎች እንዲሞቱ፣ንብረት እንዲወድም፣አብረው የኖሩ የማረቆና የመስቃን ቤተሰቦች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኖ ነበር።የመስከረሙ ጥቃት በህዳር ተደገመ።በመስከረሙና በህዳሩ ጥቃት በድምሩ ከ50 ሰዎች በላይ ሞቱ፣ቁጥራቸው እስከ 400 መቶ የሚደርስ ሰዎች ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው፣የወደመው ንብረት የገንዘብ ተመኑ ምን ያህል እንደሆነ ያልተገለጸ ቢሆንም አሃዙ ብዙ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።ጥቃቱ ሰዎች ብቻ ሳይሆን እንስሳትም የተሰቃዩበት ነው። የመስቃንና ማረቆ ግጭት የከፋ ቢሆንም፤ ከሌሎች የደቡብ ክልል ግጭቶች የሚለየው በማእከላዊ መንግስት ተገቢውን አትኩሮት አለማግኘቱ ነው። #የፌዴራሊዝሙ_ትኩሳት የፌዴራሊዝሙ ትኩሳት በመላው ኢትዮጵያ ተሰራጭቷል።በኢትዮጵያ ዉስጥ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት በየቦታው እየበዛ ነው። ኢትዮጵያ ያላትን ነባራዊ ሁናቴ አጢኖ በርግጥ የፌዴራሊዝሙ ስርዓት አዋጭ ነውን? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያስገድል። እነ ለገሰ ዜናዊ ጫካ ሲገቡ የታጠኑበት ዘርን መሰረት ያደረገ የመገንጠል አጠፋሪስ ሽታው ሳይጠፋ እራሱን በፌዴራሊዝም ስርዓት ዉስጥ ዘልቋል።አብረው የሚኖሩ ዜጎች ያንን የደደቢት የመገንጠል ሽታ እያሸተቱት መቃቃሩ በዝቷል። እነ ለገሰ ዜናዊ በተመስጥኦ ያጠነኑት የነ ጆሴፍ እስታሊን የማንነት ፖለቲካዊ ግሽበት በአውሮፓ ዉስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ህይወት እንዲጠፋ ሰበብ መሆኑን ማጤኑ ግድ ነው።በዘር፣በማንነት መልከዓምድራዊ አቀማመጥ ላይ ሶሻሊዝምን ደርባ የነበረችው ታላቋ ሩስያ በፕሬዝዳንቷ ሚካኢኤል ጎርባቾቭ የተበታተኑ አገራት ብትሆንም ከዚህ በሗላ ደደቢት ጫካ ዉስጥ ዘርን መሰረት ባደረገ ፖለቲካዊ ልክፍት የተለከፉት ህወሃቶች ምን ያህል ንጹህ ዜጋ በፌዴራሊዝም ስም እንደሚገበርላቸው የታወቀ ነገር የለም።አሜሪካንን የመሰሉ አገራት ከእርስ በርስ ጦርነት ኪስራ ተምረው እርቀ-ሰላም አውርደው ዲሞክራሲና የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ የፌደራል መንግስትን ገንብተው ሐያል አገር በመሆን አለምን እየተቆጣጠሩ ነው። ፈዴራሊዝም በዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ከታጀበ አዋጭ መንገድ ነው የሚለው አመክንዮ ቢደመጥም መንግስታዊ መዋቅርና አደረጃጃት በዘር ከተሸነሸነ «የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ» እውን ይሆናሉን? የሚሉትን ጥያቄዎች አብረው ይነሳሉ። በአለም ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝምን ተግባሪ የሆኑ አጋራት ግጭት፣አስተዳደራዊ ብልሹነትና አለመረጋጋት ያለባቸው ሲሆኑ ይታያል። የኢትዮጵያንም የወደፊት እጣፈንታ ለመወሰን ከደደቢቶቹ ሽፍቶች ንድፈ-ሐሳብ ወጣ ብሎ አዋጭ መንገዶችን መመርመሩ ግድ ነው የሚሉ ድምጾች ተበራክተዋል። #ለፌዴራሊዝሙ_ትኩሳት_መፍትሔን_መሻት የፌዴራሊዝሙ ትኩሳት በደቡብ ክልል ዉስጥ ተሰራጭቷል።የማንነት ጥያቄ ደርቷል።ከትልቁ ስብስብ ወደ ትንሽ ስብስብ ገብቶ ዘርና በቋንቋ ተመርኩዞ እራስን ለማስተዳደር በሚደረገው ጥረት ዉስጥ ደም እስከመፋሰስ ተደርሷል።መስቃንና ማረቆ ወረዳዎች በዚህ መሬት ዉስጥ በተቀበረ የዘር ፈንጅ ተለብልበዋል።ማእከላዊ መንግስቱ ጣልቃ በመግባት በወረዳዎቹ ዉስጥ የተነሳውን ትኩሳት ማስታገስ አለበት።የተፈናቀሉ፣ንብረት የወደመባቸው፣የተዘረፉና የቤተሰብ አባል የተገደለባቸው ሰዎች የመንግስትንና የመላዉ ኢትዮጵያን እርዳታን ይሻሉ። መስቃንና ማረቆን በሚያዋስኑ ቀበሌዎች ከፈተኛ የህገወጥ መሳሪያ ዝውውር መኖሩን በእንሲአኖ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በስጋት ይናገራሉ።በመሳሪያው ዝውውር ላይ ባለስልጣናትና ባለ ሐብቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሗን እየገለጹ ነው።በህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ላይ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች፣ቡድኖችና ባለስልጣናት ላይ መንግስት አስፈላጊዉን እርምጃ መውሰድ አላበት የሚል ጥሪ እየቀረበ ነው።የመስቃንና ማረቆ ቤተሰቦችን ችግር ለመፍታት የተነሱት ያገር ሽማግሌዎች ሰላምን እንዳያሰፍኑ የተለያዩ መስናክሎች እየገጠሙቸው መሆኑን የሚገልጹ አቤቱታዎች ተበራክተዋል።መንግስት እነዚህን የሰላም ዘቦችን በማገዝ ተልእኮአቸውን ይወጡ ዘንድ አስፈላጊውን እርዳታ ማደረግ አለበት የሚል የወል ድምጽ ይሰማል። የፌዴራሊዝሙ ትኩሳት እሰከየት? ዉጤቱ በሂደት የሚታይ ይሆናል። ልብ ያለው ልብ ይበል።



26 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page