top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"እስከ ካርሙጆ" ክፍል - 4 ( የመጨረሻ)አጥፊን መቅጣት

በሁሉም የሰው ልጅ የህይወት አለሞች ውስጥ የሚወደሱ መልካም ስራዎች ይኖራሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መፈጸም የሌለባቸው፣ በነውር የሚቆጠሩ አሉ፡፡ እነዚህን ነውር ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች በማንኛውም የሰው ልጅ የህይወት ዓለም እንደሚኖሩ ሁሉ በዳሰነች ብሄረሰብም ውስጥ አልፎ አልፎ መገኘታቸው አይቀርም፡፡

የዳሰነች ብሄረሰብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላዊ ዕምነት አለው፡፡ ይህ ባህላዊ ዕምነት የሚከናወነው የዕምነቱ መሪ ሆኖ በተመረጠ ሰው አማካኝነት ነው፡፡

የብሄረሰቡ አባላት፣ ወንዶች ብቻ፣ ወደዚህ የዕምነት አባት ቤት ይሄዳሉ፡፡ የእምነት አባቱ የቤት እመቤት ግን ከሌሎቹ የብሄረሰቡ ሴቶች በተለየ መንገድ ለአምልኮ በሄዱት ተባዕቶች መካከል የመገኘትና እንግዶቿን የማስተናገድ ፍቃድ አላት፡፡ የመጡትን ወንዶች ቅቤ ትቀባለች፡፡

ተባዕቶቹ አምልኮውን ለመፈጸም በሄዱበት ዕለት ወደቤታቸው አይመለሱም፡፡ እዚያው ነው ያሚያድሩት፡፡ በሬ ወይም ፍየል ታርዶላቸው፡፡

በዚሁ ወቅት በዕምነቱ መሪ አማካኝነት ለፈጣሪ ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ ዝናብ ዘንቦ ሳር እንዲበቅልና ከብቶች እንዲጠግቡ፡፤ የከብቶች ቁጥር እንዲበዛ፡፡ የኦሞ ወንዝ በደንብ እንዲሞላ፡፡ ሞልቶ ከተረፈ በኋላ መልሶ በሚሸሽበት ወቅት በኦሞ ዳርቻዎች ላይ ማሽላ ተዘርቶ ይበቅል ዘንድ ነው መለማመኑ፡፡

የዳሰነች ብሄረሰብ የአምልኮ ስርዓት በሚያከናውንበት ወቅት ይቅርታም ይሰጣል፡፡ በብሄረሰቡ ውስጥ ያልተፈቀዱ ተግባሮችን በማከናወን ጥፋት የፈፀመ ሰው በዚሁ ወቅት ቀርቦ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡

ቀርቦ የፈፀማቸውን ስህተቶች ተናዞ ይቅርታ ከጠየቀ ፣የትኛውንም ዓይነት ጥፋት ፈጽሞ የተገኘ ቢሆን እንኳ ምህረት አይከለከልም፡፡ (ሀገራችንን የዘረፉ ሰዎች ግን ዞረው አስፈራሪዎች የመሆናቸውን ነገር ከግምት አስገቡልኝ፡፡)

ችግሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ ሳይገኝ የቀረና ይቅርታ ያልጠየቀ እንደሆነ፡፡ ጥፋቱ በብሄረሰቡ አባቶች ታይቶና ጥፋት መሆኑ ተረጋግጦ ለእድሜ አቻዎቹ መረጃ ይሰጣል፡፡ አቻዎቹ የበረሃ ልምጭ ቆርጠው ይገርፉታል፡፡ በዚህ አይቆምም፡፡ እንደ ጥፋቱ ክብደት ተጨማሪ ቅጣቶች ይጠብቁታል፡፡ ለጥፋቱ መሰረዝ በካሳ መልክ ፍየል ይታረድና ግራና ቀኝ በተተከሉ ባላዎች ላይ በተጋደመ እንጨት ላይ የታረደውን ፍየል ስጋ በብልት በብልቱ ያንጠለጥላል፡፡ ከስሩ ዕሳት ነዶ ፣ጭስና ነበልባሉን ጨርሶ በጋመ ፍምነት በቀረው፣ የተንጠለጠለው ስጋ እንዲበስል ይደረጋል፡፡ “ወጠሌ” ይሉታል፡፡ የተንጠለጠለውን ስጋ በጋመውም የማብሰል ግዴታ ያለበት አጥፊው ሰው ነው፡፡

ወትሮ የስጋው ማብሰያ ፍም የሚቆሰቆሰው በረጅም እንጨት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በአጭር የጎድን አጥንት ነው፡፡ ፍም የነካው አጥንት የመፋጀቱንልክ የቀመሰ ያውቀዋል ፡፡ አጥፊው በአጭሩ የጎድን አጥንት እየቆሰቆሰ የነደደው ፍም ቢያቃጥለውና በተቃጠልኩኝ ምክንያት ፊቱን ቢያጠቁር ወይም ቢያጨማድድ፣ ወይም ደግሞ ድምጽ ቢያወጣ ይገረፋል፡፡ ሲቆሰቁስ ከስር የጋመው ፍም አናት ላይ የተንጠለጠለው ስጋ ስብ እንባ ቢያስወርደው እና እንባው ቆስቋሹ ጥፋተኛ ዕጅ ላይ ጠብ ቢል ፣ጠብ አለብኝ ብሎ ፊቱን ቢከሰክስ አሁንም ቅጣት ይደመርበታል፡፡

አንዲህ ያለው የጥፋተኛ ቅጣት ፋይዳው ምንድነው ? ጥፋተኛው ከቅጣቱ በኋላ “ እኔ እንዲህ አይነት ጥፋት ፈጽሜ ፣ ይቅርታ ሳልጠይቅ ቀርቼ ሲቆጣ በፈጣሪ ዕገዛ ነው የተረፍኩት:: እናንተ እንዳታጠፋ፣ እንደኔ ዓይነት ቅጣት እንዳታተርፉ…” እያለ ፣ ለአቻዎቹና ለቀረባቸው ሁሉ ይናገራል፡፡ ይህን በማድረጉ ሌሎች ከጥፋተኝነት ሀሳብና ተግባር ሸሽተው ይኖራሉ፡፡ ሰው ሰላም ይሆናል፡፡

እኔ ግን ሰሞኑን ሰላም አጥቻለሁ ፡፡ በአንድ ጓደኛዬ ቋንቋ ባትሪ ‘‘ አፍልቻለሁ’’

ምን ማለት መሰላችሁ እጅግ ተናድጃለሁ ፡፡ ተናድጃለሁ የሚለው ቃል አይመጥነውም ፡፡ ጭርር ብያለሁ፡፡ እንደዚህ ያንጫረሩኝ እነዚህ ሀገርን ከነነፍሷ የዘረፉት ተጠርጣሪዎች ሰዎች ናቸው ፡፡

የዘረፉትን የሀብት መጠን ሳስብ ፣ ገና በሌሎች ተቋማትም የተመዘበረውንና ለህዝብ ይፋ ያልሆነውን ሳስብ ደግሞ ባትሪዬ አሁን ካለው በላይ አፍልቶ እንዳልሞት ፡፡ ዘረፋው ባይኖር ኖሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከበርቴ ነበርኮ! ፡፡ እኔስ ኢትዮጵያዊ አይደለሁ፡፡ ይምንጨረጨረው ከኪሴ የወሰዱ እየመሰለኝ ፡፡ የምን መሰለኝ ነው ፡፡ ነው!!!

መዝረፋቸው በፍርድ ቤት እንደተረጋገጠ ከኪሴ ያወለቁትን ብር፣ ድርሻዬን ይመልሱልኝ!!


17 views0 comments
bottom of page