top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ሊነጋጋ ሲል በእጅጉ ይጨልማል!AbdulMalik Hussain

በአብዛኛው በቡታጅራ ከተማ ኣካባቢ ለተወልድንው ይህ በማረቆና በመስቃን ማህበረሰብ የተፈጠረው ያለመግባባት "የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሃዘንሽ ቅጥ ኣጣ ከቤትሽ ኣልወጣ" እንደሚባለው ሆኖብናል። በመላ ሃገሪቱ ይህ ሁሉ ደም መቃባት ያመጣው የዛ የሃያሰባት ኣመት በተንኮል የተሞላው የወያኔ የሰዎችን መስፈሪያና መኖሪያ ሲያልፉም መቀበሪያ ቦታ በዘር በጎሳ መከፋፈሉ ነው።

ምንም እንኳን ናይ ቀዳማይ ጠ/ም ወዲ መለስ መቃብር ዉስጥ ሆኖ ነው ይህን ሁሉ በሃገሪቱ ዉስጥ ትርምስ የሚፈጥረው ማለት ባያስደፍርም ትቶት የሄደው ክፉ የከፋፍለህ ግዛው ኣስተዳደር ሃሳብ ግን የዶ/ር ኣብይ ኣህመድ ኣስተዳደር ስር የሰደደ ለውጥ አስኪያመጣ እዚህም እዚያም ማቁዋሰሉ ኣይቀሬ ነው። ህዝባችን መገንዘብ የተሳነው ነገር ቢኖር ኣጥፊዉንና ሰይጣኑ መለስ ዜናዊ ዘርቶበት የሄደዉን የጥላቻ፣ የጥፋትና የእልቂት የኣስተዳደር በደል ለምን የመለስ ኣስተዳደር ቀጥተኛ ተቃራኒ በሆነው በታታሪው በየዋሁና እሩህሩሁ የዶ/ር ኣብይ ኣህመድ ኣገርና ህዝብን ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከረሃብና መከራ ወደ ተረጋገጥ እድገትና ብልፅግና የሚለዉጥ ኣስተዳደራዊ ለውጥ መቀየር ኣለመቻሉ ነው።

ሁላችንም በገሃድ እንደምናውቀው ኣካባቢያችን የሚታወቀው በሰፊ ለም መሬቱ ወይም በወርቅና ነዳጁ ሳይሆን በህዝቡ ታታሪ ሰራተኛነቱና የእድገት ተምሳሌትነቱ እንጂ። ወቅቱ የሚጠዪቀው ለእድገትና ኑሮዉን ማሻሻል የሚፈልግ ትውልድ ነው እንጂ በጦርና በቢላዋ የወገኑን ሆድ ወግቶ ሆድቃዉን የሚዘረግፍ ትውልድ ኣይደለም።

እስኪ በዚህ በሰለጠነ ዘመን የሰው ልጅ ኣምላኩ ኣስዉቦ የፈጠረዉን ወንድሙን ወይም እህቱን በመግደል እንደምን ደስታን ይጎናፀፋል? ያሳፍራል እንጂ። እስኪ ኣስተውሉ ሰው እንዴት ከቤቱ እንዲሰደድ ተፈርዶበት ለኳስ ማንከባለያ ኣዉጫጭኝ ለመሰብሰቢያ በተሰራ ቦታ/ስቴዲየም ከነቤተሰቡ ተበትኖ እዚያው በልቶ እዚያው ሰግዶ አዚያው ተፀዳድቶ ገመናው እንኳን መሸፈኛ ቦታ ይነሳዋል? ታዲያ ይህ ኣስከፊ ሰቆቃዊ ኑሮ በወገንህ ፈፅመህ ጤናማ እንቅልፍ ይተኛልሃል?

ኧረ ጎበዝ ቆም ብልህ ኣስብ ጊዜው እኮ ሃያአንደኛው ከፍለዘመን ወደመጠናቀቂያው ነው። ዛሬ ወቅቱ የሚጠይቀው ኣእምሮን በሚገባ ኣሰርቶ በስልጣኔ ሌሎች ከደረሱበት ለመድረስ መፍጨርጨርን ነው። ለዚህ ደግሞ እንዲያግዘን ኣላህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኣብይ ኣህመድን ኣምጥቶልናል። እርሱ ታላቋን ኢትዮዽያን ወደነበረችበት የእድገት ማማ ለመመለስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እንቅልፍ ኣልባ ሆኖ ይደክማል በኣንፃሩ ግን ቡታጅራና ኣካባቢዋ ላይ የወያኔ ቅጥረኛው የርሱን ራእይ ለማሳካት ከመሮጥ ይልቅ የማረቆና የመስቃን ተዋልዶና ተዋዶ የኖረውን ማህበረሰብ ደም ያቃባል። ጃል ተመከር ከዚህ እርኩስ ስራህ በመታቀብ የህዝባችንን ሰላም መልስ። ለኢትዮዽያችን ከመቼዉም ጊዜ በላይ የብሩህ ተስፋና መልካም ዘመን በዶ/ር ኣብይ ኣህመድ ኣስተዳደር እየመጣ ስለሆነ ይህን ተስፋ አንዳያይ ኣትንፈገው።

ለተጎዱት ወገኖቻችን መርጃ የሆነዉን ግሎባል ፈንድሬይዚንግ በቅርቡ ይፋ ለማድረግ በሰፊው እየሰራንበት እንገኛልን

“መግደል የተሸናፊነት ዋናው መገለጫ ነዉ”!

ኣብዱልማሊክ ሁሴን

Maryland, USA


20 views0 comments
bottom of page