top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"እንብላ! እንደምንለው ሁሉ እንስራ!" ብንል ኖሮ የት እንደርስ ነበር? (ክፍል- 02)



የመጀመሪያው ጽሁፍ "መብላትና መጋበዝ" ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ ክፍል ደግሞ በተለይ "የአስተሳሰብ ስራ" ላይ ያተኩራል። የመጀመሪያውን"መብላትና መጋበዝ" እዚህ ያገኙታል። የአስተሳሰብ ስራን ትንሽ በምሳሌ ላስረዳ። ስራ ሲባል አንደኛው የሃሳብ ስራ ሲሆን ካሰብን በኋላ በመናገር ወይም በማሰብ ብቻ የምንሰራው ስራ ነው። ይህ የሃሳብ ስራ ለምሳሌ ምክር መስጠት ሊሆን ይችላል። ሰውና ፈጣሪ አምላካችንን ማክበር ሊሆን ይችላል። በህይወታችን ላይ ምን እንደምንፈልግ ቀድም ብሎ ማወቅ ሊሆን ይችላል። እቅድ ማውጣት ሊሆን ይችላል። የምንፈልገውንና የምንወደውን ነገር እንዳናጣ እጅ ሳንሰጥ ዝግጁ እንድንሆን የሚያደርገን ሃሳብ ሊሆን ይችላል። በራሳችን እንድንተማመን የምናስበውና የምንወስነው ውሳኔ ሊሆን ይችላል። በሃሳባዊ ስራ ወስነን የምንወስደው እርምጃ ደግሞ አካላዊ ስራ ነው። ሆኖም ግን ውሳኔ የምንወስነውና እርምጃ የምንወስደው ከሃሳባችን ተነስተን ነው። ከላይ ባጭሩ የዘረዘርኳቸው ሃሳባዊ ስራወች ናቸው። በሚቀጥለው ዙር አካላዊ ስራ ምን እንደሆነ አቀርባለሁ። ዛሬ ስለ ሃሳባዊ ስራ አብረን እናያለን።

አንድ መቶ እጅ ትክክል የሚባል ነገር ስለሌለ ይህ ጽሁፍ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቢነካም ሁሉንም አይመለከተም። ነገር ግን የአንዲትን ሃገር እጣና ፋንታ የብዙሃኑ አስተሳሰብ ይወስነዋል። ምናልባት አንዳንድ ምክንያታዊ ሆነው ግን ጠንከር ያሉ አባባሎች ቢኖሩም ሰወች እንዲሰማቸው ለማድረግ እንጂ እንዲያማቸው አስቤ አይደለም።

በእኔ ትዝብትና እይታ ብዙወቻችን ኢትዩጵያውያን የግል ሃሳባችንን ማንሸራሸር ይከብደናል። ሁለተኛ ደግሞ ከሌላ ሰው የተሻለ ሃሳብ ለመቀበል ወይም ሂስ ለመስጠት ይከብደናል። ዝም እንላለን። ዝም ስንል ታዲያ የአስተሳሰብ ስራ አልሰራንም ማለት ነው። በተለይ ተፈታታኝ ሃሳብ ከመጣ ሃሳቡን ለመመርመርና ተመጣጣኝ አሉታዊ መልስ ወይም ሂስ ለመስጠት ሲቸግረን አስተውያለሁ። ምክንያቱም ሃሳቡ በግላችን ከምናስበውና ከምንመኘው ጋር ዝምድና እንዲኖረው እንፈልጋለን። በዚህም የተነሳ ሃሳቡን ለመቀበል ወይም ለመመርመር ስለምንቸገር እከሌ አውቅልሃለሁ አለኝ። እከሌ የተሻለ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ይሞክራል ማለት የተለመደ ነው። ይህንን በምናስብ ጊዜ የበታችነት እንዲሰማን ያደርጋል። ከሁሉም የሚሻለው ግን በኢትዮጵያዊነቴ ምን አድርጌ ጠቃሚ ልሁን ብሎ ሰው እራሱን ቢጠይቅና ቢመረምር አስተሳሰቡ ይሰፋል የሚል እምነት አለኝ።

ባጠቃላይ አነጋገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ማንም የሚወስድበት የለም። የትም ሃገር ውስጥ ቢሆን በአንዲት ሃገር ዜጋ መካከል ሰው የሚለያየው በባህሪው፣ በሃሳቡና በድርጊቱ ነው። የሰው ልጅ በመልኩ፣ በጾታውና በዘሩ መመንዘር የለበትም። የአንድ ግለሰብ ዜግነት ዝቅ የሚልበት ምክንያት የለም። ይህንን በምሳሌ ላስረዳ። ለምሳሌ ሌላ ሃገርም ውስጥ ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰነፍና ጎበዝ ሰው አለ። ሌባና ሃቀኛ ሰው አለ። ወንጀለኛና ወንጀል የማይሰራ ሰው አለ። ክፉና ደግ ሰው አለ። ፈሪና ጀግና ሰው አለ። ደፋርና ዝምተኛ ሰው አለ። በእድሜና በእውቀት ትንሽና ትልቅ አለ። ሁሉንም ነገር ማወቅ ባይቻልም እንደሁኔታው የተሻለና አነስ ያለ የሚያውቅ አለ። ስህተት የሚሰራና ትክክል የሚያደርግ ሰው አለ። ኢትዮጵያ ሃኪም፣ መሃንዲስ፣ ሳይንቲስት፣ ፈላስፋ፣ ጥበበኛ፣ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ አስተማሪ ወዘተ ልጆች አሏት። ምሳሌወቹ ብዙ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

የሚያውቅ ቢያሳውቅ ለመቀበል አስቸጋሪ መሆን የለበትም። ጀግኖችን አይቶ ከፍርሃት መላቀቅ እንደ ድክመት መታየት የለበትም። ፍርሃት የያዘው የጀግናውን ተግባርና ታሪክ እያየ ከተማረ ጀግና ይሆናል። ዝምተኛው ከደፋሩ እያየ ቢማር ድፍረት ያዳብራል። ስንፍና ያለበት ከጎበዙ እያየ ቢማር የተሻለ ሰራተኛ። በልጅነታችን ትምህርት ቤት እምንሄደው ለመማርና ተምረን ጠቃሚ ለመሆን ነው። ከት/ቤት ስንወጣ ደግሞ ትምህርት ስለማያልቅ የምንኖርበት ህይወትና ህብረተሰብ ትምህርት ይሰጠናል። እያንዳንዳችን የተለያየ ጸጋ አለን። ይህ ማለት በተለያየ ችሎታና እውቀት ብንለያይም የምንሰጠውና የምንቀበለው ጸጋ አለን ማለት ነው። አንድ ሰው ሁሉንም ጸጋ ማወቅ አይችልም። የራሱን መስጠትና የሌላ መቀበል ግን ይችላል። ይህን ለማግኘትና ለመስጠት ደግሞ ልባችን ሲሰፋና አስተሳሰባችን ጥልቅ ሲሆን ነው። ልባችን ሲከፈት ይሰማናል። አይኖቻችን ሲገለጡ የወገኖቻችን ችግር ይታየናል። ከግልነት ወደ ወገናዊና ሃገራዊ እንሸጋገራለን። አስተሳሰባችን ሲሰፋና ሲጠልቅ ለውጥ ይመጣል። አንድ ቦታ ላይ አንቆምም። ከትላንቱ ይልቅ ዛሬ የተሻለ ሰው ሆነን እንገኛለን። ይህ ሁሉ የአስተሳሰብ ስራ ነው።

ይህ በማንኛውም መልኩ የሰው ልጅ መገለጫ አንዱ መንገድ ነው። ሆኖም ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሃገሩና ለወገኑ የሚያሳየው ደንታ አንድ አይነት ሊሆን አይችልም። አይናችንን ስንገለጠው የሌላው ችግር ይታየናል። አዕምሮአችንን ካዘጋጀነው የሌላው ሃሳብ ይገባናል። ልባችንን ስንከፍተው ፍቅር ይገባበታል። ብዙወቻችን ለሃገራችንና ለወገናችን ደንታ እንዲኖረን የበለጠ የልብ ውህደትና የአዕምሮ አንድነት ለማዳበር ትልቅ የሃሳብ ስራ መስራት ወሳኝ ነው።

ሃሳብ ላይ ብዙ የቀረና መስራት ያለብን ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ሃሳብ ሃይል ነው። ህይወታችን ውስጥ ብዙ የሚታዩና የሚጨበጡ ነገሮች በሙሉ መሰረታቸው ሃሳብ ላይ ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን አንድነት ሃይል ነው ይላሉ። አባባሉ ጥሩ ቢሆንም በሰፊው የሚያስረዱ ጥቂቶች ናቸው። በሃሳቡ ቢያምኑበትም ሃሳቡ ላይ ትኩረትና ልባቸውን አይሰጡትም። የሰው ልጅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ሃሳቡን ተረድቶ ሲሰራበት ነው። አንድ ሃሳብ እንኳን አንድ ግለሰብ ቀርቶ ቤተሰብ፣ ህብረተሰብና ሃገር እንዲሁም አለምን መቀየር ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሃሳቡ ሰወችን ሲገባቸውና ሲቀበሉት ነው። ከዛም ሃሳቡ ስራ ላይ ሲውልና ሲፈተን ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ለምሳሌ አንድን ሃሳብ ብንቀበለውም እንኳን እራሳችን ሳንሰራ ውጤት ማየት እንፈልጋለን። ወይም ሌሎች ስራውን እንዲሰሩት እንጠብቃለን። ትንሽ መስዋእትነት ተሰጥቷቸውና ጊዜ ወስደው ውጤት ማሳየት የሚችሉ ሃሳቦች አሉ። ባህሪና የአስተሳሰብ ስራ በግልም ይሁን በሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ሚና አላቸው። እስከሚያስፈልገው ጊዜ ድረስ ደግሞ ገትሮ ይዞ እስከ ውጤት ድረስ መቆየት በጣም ይከብደናል። ይህ እኮ ጥሩ ሃሳብ ነው ብለን ብናምንበትም በሃሳቡ ተስማምተን ወይም አሻሽለን ውጤት ለማየት አንጓጓም።

ጽሁፉን ወደ ዋናው አርዕስት ለማዛመድ ያህል የሃሳብ ውጤት የተሰናዳ ምግብ ካቀረብን በኋላ በልተን ወዲያውኑ እንደምንጠግበው አይነት አይደለም። እንብላ ብለን በአንድ ቃል ብቻ የምጨርሰው አይደለም። ሃሳቡ እንዲሰራ ጊዜና የሃሳብ ስራ ይፈልጋል።

ምንጭ - tatariw


16 views0 comments
bottom of page