top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"የልደቴ ቀን"



ከወራት በፊት የልደቴ ቀን ነበር ፅሀፉን ማንበብ እንጂ ስንተኛው አመት ብሎ መጠየቅ አይቻልም !

ከአመታት በፊት እንደተነገረኝ ከሆነ ዓመተ ምህረት ሰአቱን በዘነጋሁበት:: ቀኑን እና ወሩን በማስታውሰው እለት ነበር ወደዚች ምድር በምርጦቹ ወላጆቼ ሰበብነት የተቀላቀልኩት። ቀኑን እና ወሩን ብቻ ማስታወሴ አይፈረድብኝም:: በፊት በፊት የተወለድኩበትን አመተ ምህረት አስታውሰው ነበር:: ከአመታት በፊት ግን ለእረፍት ሐገር በገባሁበት አንድ አስደንጋጭ ክስተት የተወለድኩበትን ዓመተ ምህረት እንድዘነጋ አድርጎኛል። የመዘንጋቱ ችግር ፈውስ ለማግኘት በሚል እንደ መረመረኝ ዶ/ር ከሆነ ደግሞ ዳግመኛ እንደማላስታውሰው የመርዶውን ዜና አብስሮኛል።

አጋጣሚው እንዲህ ነበር ለትንሽ ጉዳይ ወደ ቡታጀራ መሄድ ፈልጌ አውቶቡስ ተራ ሄድኩኝ በደረስኩበት ሰአት ቡታጀራ ለሚጭነው ሚኒ ባስ የመጀመሪያ ሰው ነበርኩና አመቺ የምለውን ቦታ መርጬ ተቀመጥኩ አንድ ሁለት እያለ መኪናው አንድ ሰው ብቻ ቀረው እንዳጋጣሚ ግን መጨረሻ ላይ የመጡት ሁለት ጥንዶች ነበሩ ረዳቱ ሊመልሳቸው አልፈለገም እና አንገቱን ገባ አድርጎ ከተመለከተ በዃላ ከተቀመጥነው መካከል በአይኑ ወደኔ እየተመለከተ ``ፋዘር እባኮት ትንሽ ጠጋ ይበሉ ላስቸግሮት``አለ በጣም ደነገጥኩ ተናደድኩም የልጁን አቋም ደጋግሜ ባየው እኔን አንቱ ሊያስብል የሚችል ልዩነት አጣሁ። ፊቴን አጨፍግጌ ተጠጋሁተ የተጠጋሁት ልጅ ሳይታዘበኝ አይቀርም `` ምን በሰው መኪና እንዲህ ያደርገዋል ያባቱ መሰለው`` ያለም መሰለኝ ፋዘር ጠጋ በሉ የምትለዋ ቃል አዕምሮዬ ላይ በየደቂቃው ታቃጭላለች አሁን ከኔ እና ከሱ ማን ይበልጣል ብዬ ተሳፉሪውን ልጠይቅ ፈለግኩ `` አንቱ ኖት`` ቢሉኝ ብዬ ይበልጡኑ ፈራሁ ለመጀመሪያ ጊዜ እራሴን በመሰታወት የማየት ጉጉት አደረብኝ ግን ከየት ይምጣ መኪናው ጉዞውን ጀምሮዋል ሁሉም ከጎኑ ካለው ጋር የወጋል እኔ ረዳቱ በሰጠኝ የቤት ስራ እንደ ተጠመድኩ በሃሳብ መጀመሪያ ወደዚህ ምድር የመጣሁባትን ቀን እያሰብኩ መቀነስ መደመሩን ተያያዝኩት ውጤቱ ላይ ሳልደርስ… "ፉዘር ቡታጀራ ደርሰናል እባክዎትን ይውረዱ" ይሄኔ ነው መሸሽ አልኩ በውስጤ ከመነሻዬ እስከ መድረሻ በአንቱታ… ከመኪናው እንደወረድኩ ወደ አንድ ካፌ ነበር ያመራሁት ወደ ውስጥ ዘልቄ መሰታወት ወደ አየሁበት ጥግ ላይ ተቀመጥኩ እራሴን በመስታወቱ ደጋግሜ ብመለከትም ከረዳቱ ጋ የአንቱታ ያህል ልዩነት አጣሁ በሁለታችን መካከል የአገኘሁት ልዩነት የኔ መመለጥ እና የሱ ፍሪዝ መሆን ብቻ ነው መመለጥን ከማጣት በላይ ጠላሁት ለረጅም ሰአት መሰታወቱ ላይ አፈጠጥኩ እንደ አኳሗኔ ከሆነ ጊነስ ቡክ ላይ እራስን ለረጅም ሰዓታት በመስታውት በመመልከት ሪከርዱን ለኔ ሊሰጠኝ ይገባል አልኩ።

ከሄድኩበት የሀሳብ ጉዞ የአሰተናጋጃዋ "ምን ልታዘዝ ፋዘር" መለሰኝ መስታወት አልኩ በሀሳቤ የነበረው ቃል አፈትልኮ "አባት ይሄ ካፌ እንጂ የውበት እቃ መሸጫ አይደለም" ከማለቷ ውሀ ስጪኝ ብዬ የውስጤን ሳላስባንን ውሃዬን ተቀብዬ ወደ ጉዳዬ አቀናሁ:: ከዛን ቀን ጀምሮ ነው የተወለድኩበትን ዓመተ ምህረት የረሳሁት:: ለካ እኛ ሀበሾች እድሜያችንን እና አንቱታን የምንፈራው የተወለድንበት ጊዜ በጨመረ ቁጥር ወደ ሞት እየተጠጋን ስለሚመስለን ነው:: ብቻ ምንም ሆነ ምን በዚያን ቀን ነበር እኔ እና ይቺህ አለም የተዋወቅነው በዚች አጭር እድሜ ብዙ ነገር አይቻለሁ:: ሰው ከማሳቅ እስከ ማሳቀቅ:: ከማስቸገር እስከ እሰከ መቸገር:: ምርጥ ምርጥ ቤተሰቦችን ጓደኞችን እንዲሁም የአብራኬ ክፋይ የሆኑ ልጆችን አፍርቼበታለሁ። አቡ ኪያ፣ ነፍሴ ከድር፣ ሀጂ እና ሼሆቹ የሚሉ ተቀጥያዎችን ተሽልሜበታለሁ።

ኡመር አህመድ

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ


22 views0 comments
bottom of page