• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የማይጠይቅና የማይንቀሳቀስ ጥቅም ላይ ያልዋለ አቧራ የሚሰበስብ እቃ ብቻ ነው!መጠየቅ የማናውቀውን እንድናውቅና የማንችለውን እንድንችል ያደርጋል። መጠየቅ የጎደለውን እንድንሞላና የተጣመመውን እንድናስተካክል መንገድ ይከፍታል። መጠየቅ ያላየነውን እንድናይና ያልሰማነውን እንድንሰማ ያደርጋል። መጠየቅ እውቀታችን እንዲጨምርና ችሎታችን እንዲሰፋ ያደርጋል። መጠየቅ ሰው መብቱን እንዲያውቅና ተንቀሳቅሶ እርምጃ እንዲወስድ ያገፋፋል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ፤ የማይጠይቅ የተጣመመ አያስተካክልም። የማይጠይቅ የጎደለ አይሞላም። የማይጠይቅ አያይም። የማይጠይቅ አይሰማም። የማይጠይቅ እውቀቱ አይጨምርም። የማይጠይቅ ችሎታው ከፍ አይልም። የማይጠይቅ አያድግም። የማይጠይቅ ነጻ አይደለም ወይም መሆን አይችልም። የማይጠይቅ አምናም ሆነ ዘንድሮ፤ ትላንትም ሆነ ዛሬ ያው ነው። ለውጥ የለውም፡፡

ማብራሪያ

ባጭሩና ዋናው ነጥቡ የጠየቀ ያገኛል፤ ያልጠየቀ ግን አያገኝም ነው። የጠየቁትን ለማግኘት ሁለት ነገሮች ወሳኝ ናቸው። አንደኛው አስቦ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አስቦ መጠየቅ ናቸው። አስቦ ማድረግ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የምናሳየው እንቅስቃሴ ነው። ለምሳሌ ተንቀሳቅሰን እጆቻችን እንዲሰሩ የምናደርግበት ሁኔታ ሊሆን ይችላል። አስቦ መጠየቅ ደግሞ አይኖቻችንን ገልጠን መሻሻል ያለበት ማንኛውም ነገር ላይ ልብ ስንልና አስተያየት ሲኖረን ነው። መጠየቅ ሰው ሃሳቡን መሰረት በማድረግ እራሱን ይጠይቃል። በተመሳሳይ ደግሞ ተናግሮና በአፉ ቃላት አውጥቶ ይጠይቃል። አስቦ መጠየቅ፤ ካየነውና ከሰማናው በመነሳት ከውስጣችን የሚመነጨው ሃሳብ ነው። ይህ ለምሳሌ የዚህ ህንጻ አሰራር ጥሩ ነው ወይስ አይደለም የሚል ሊሆን ይችላል። እስካሁን ድረስ በማሽን ሳይሆን በበሬ መሬት እንደት ይታረሳል ሊሆን ይችላል። እኔ ነጻ ነኝ ወይስ አይደለሁም ብለው እራስዎን የሚጠይቁት ጥያቄ ሊሆን ይችላል። በቃላት ተናግረን የምጠይቃቸው ጥያቄወች ደግሞ እንደሚታወቀው ተናግረን ሌላ ሶስተኛ አካል ስንጠይቅ ነው። ለምሳሌ የሆነ ነገር እንዴት እንደሚሰራ በራሳችን ካልቻልን ሰው ጠይቀን መፍትሄ የምንሻበት መንገድ ነው።

ባጠቃላይ ሁሉም ነገር ከሃሳብ ይፈልቃል። ከዛም ያሰብነውንና የተመኘነውን ነገር ለማግኘት መጠየቅ የግድ ነው። ካልጠየቅንና ዝም ካልን ለማግኘትና ለማወቅ የተመኘነውን ሁሉ እናጣለን። ሌላ ስውም ሊነጥቀን ይችላል፡፡ የማይጠይቅ በሃሳቡም ሆነ በአካሉ አይንቀሳቀስም። እንደ ሁኔታው ቢለያይም ሰው ሲጠይቅ ያስባል፣ ይናገራል ወይም በአካል ተንቀሳቅሶ እርምጃ ይወስዳል።

የማይንቀሳቀስ ሰው ልክ አንድ ቦታ ላይ ቁጭ ብሎ አቧራ የሚሰበስብ እቃ ጋር ይመሳሰላል። ሰውን እቃ ነው ለማለት ሳይሆን ሁኔታው መመሳሰሉን ለማሳየት ነው፡፡ አንድ ቦታ ላይ የቆየ እቃ ጥቅም ላይ ስለማይውል የሚሰበስበው አቧራ ብቻ ነው ለማለት ነው። አቧራውን እፍ ሲሉት እቃው ልክ እንደዱሮው ነው። አቧራውም የውሸት ሽፋን ስለሆነ በቀላሉ እፍ ሲሉት አየር ላይ ይበተናል።

ምንጭ - ታታሪው


10 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean