top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ወዳጅና ጓደኛዎ ማነው? ወዳጅነት መስጠትና መቀበል ነው። (ክፍል አንድ)



ወዳጅ በተለያየ መንገድ ሊተረጎም ይችላል። ዋናው መንፈሱ ግን ወዳጅ ማለት የልብን ለመንገር የሚታመን ሰው ሲሆን ነው። ክፉም ሆነ ደግ ሲደርስ አብሮ ተካፋይ ወይም ከጎን የሚቆም ሰው ሲሆን ነው። ወዳጅነት ከልጅነት ጀመሮ የቆየ ሊሆን ይችላል። ከብዙ አመታት ትውውቅና መተሳሰብ የመጣ ሊሆን ይችላል። አጋጣሚ የፈጠረው ወዳጅነት ሊሆን ይችላል። በጋራ ጉዳይና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። ወዳጅ ለማፍራት ምክንያቱና አጋጣሚው ብዙ ነው። ከስራ ቦታ፣ ከት/ቤት ወዘተ ሊጀምር ይችላል። ሆኖም ግን የልብ ወዳጅ ለማፍራት ቀላል አይደለም።

ወዳጅነት አብሮ በመብላትና በመጠጣት በቀጥታ አይገኝም። ይህንማ ሁሉም ያደርገዋል። ብዙ ሰው አብሮ ይበላል። ብዙ ሰው አብሮ ይጸልያል። ብዙ ሰው አብሮ ይሰራል። ብዙ ሰው አብሮ ት/ቤት ውስጥ ይማራል። ብዙ ሰው ጎረቤት አለው። ሁሉም ሰው ለሁሉም ሰው ወዳጅ ይሆናል ማለቴ ሳይሆን፤ ሰውና ሰው የሚገናኝበት መንገድ ብዙ መሆኑን ለመጥቀስ ነው።

እንደሚመስለኝ ወዳጅነት የመስጠትና የመቀበል ጉዳይ ነው። በተለይ ከማግኘትና ከመጠበቅ ይልቅ አብዣኛው ሰው መስጠት ላይ ቢያተኩር ሁኔታውን ያቀለዋል። ሳይሰጡ ማግኘት ያስቸግራል። መስጠት ስል ደግሞ ቁሳቁስ ወይም ገንዘብ ማለቴ አይደለም። ቁሳቁስና ገንዘብ ሰውን አይገዛውም። ወዳጅም አያፈራም። ፍቅርም አያመጣም። መስጠት ስል ለምሳሌ ክብር ከመጠበቅ ይልቅ መጀመሪያ ሌላውን ሰው ማክበር ሊሆን ይችላል። ፈገግታ ከመጠበቅ ይልቅ እራስን ፈገግ ማድረግ ሊሆን ይችላል። ሰላምታ ከመጠበቅ ይልቅ መጀመሪያ እራስ ፈገግ ብሎ ሰውን ሰላም ማለት ሊሆን ይችላል። በቃል መገኘት ሊሆን ይችላል። ለወዳጅ ተብሎ ጊዜ መጠቀም ሊሆን ይችላል። ወዳጅን መጠየቅ፣ ማሰብና መውደድን ማሳየት ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ላይ ሌላ የተለየ ኮተት የሌለበት ካልሆነ በስተቀር አንድ ሰው ሲወዱት፣ ሲያስቡለትና ሲጠይቁት ዋጋ የማይሰጥበት ምክንያት የለም።

አንዳንድ ሰወች በተደጋጋሚ ሲያስቡላቸውና ሲጠይቋቸው ብዙም አይጥማቸውም። ሰው ጥቅም የፈለገ ሊመስላቸው ይችላል። ይጠራጠራሉ። ተቀብለው ጸጥ ይላሉ። እንደዚህ አይነት ምልክት ከታየ ችክ ማለት አያስፈልግም። መተውና ህይወትን መቀጠል ይሻላል። በወዳጅነት መካከል ቅሬታ ሊፈጥሩ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹ መጠራጠር፣ አፍራሽ ነገር ማሰብና ጥቃቅን ነገሮችን መከታተል ናቸው። እነዚህን ሁኔታወች እንደት ማሻሻል እንደሚቻል ሁለተኛው ክፍል ላይ አቀርባለሁ። ባጠቃላይ ወዳጅነት በመስጠትና በመቀበል የሚገኝ ስለሆነ በራስዎ የሚፈጥሩት ነው።

ምንጭ - ታታሪ


15 views0 comments
bottom of page