top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የስነ ልቦናዊ ጤንነት መለኪያዎች



የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ (ከአልታ ምርምር፣ሥልጠናና ካውንስሊንግ) ሥነልቦናዊ ጤንነት ምንድነው?

ስነ ልቦናዊ ጤንነት ስንል አንድ ሰው በስነልቦና አቋሙ ሊደርስበት የሚገባው የስሜት፣የአስተሳሰብና የባህሪ ደረጃ ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው ማህበረሰብ ሊከወንና ማህበረሰቡ ሊቀበለው የሚችለው ስነ ልቦናዊ አቋም ነው። ጤናማ ሲባል በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ መካከለኛ የሆነው (average) ነገር ሲወሰድ ነው። ይህንን ትርጉም ለመረዳት ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ምን አይነት ስሜት፤አስተሳሰብና ባህሪ እንዳላቸው ለማየት እንሞክራለን፡፡

የስነ ልቦናዊ ጤንነት መለኪያዎች ምንድናቸው? 1. ራስን መውደድ(በመጠኑ ሲሆን)-Self-love (but not self-infatuation) ራስን መቀበልንና ራስን መውደድን ወይም ለራስ ዋጋ መስጠትን ያመለክታል። ይህ ማለት ግን ከመጠን ያለፈ ራስን መውደድን ወይም ከመጠን ያለፈ ለራስ ዋጋ መስጠትን(self centeredness) አያካትትም። በመጠነኛ ደረጃ ለራስ ዋጋ መስጠት(basic self esteem) አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ከመጠን ያለፈ ለራስ ዋጋና ክብር መስጠት(unconditional self esteem) እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ራስን መውደድ፣ በራስ ፍላጎት መያዝ (self infatuation) ለስነ ልቦናዊ ጤንነት አይመከርም። ስለዚህም ስነ ልቦናቸው ጤናማ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ይወዳሉ ወይም ማንነታቸውን ይቀበላሉ፤ ነገር ግን ራሳቸውን ከመጠን በላይ አይወዱም ወይም ከልክ ያለፈ ክብር ለራሳቸው አይሰጡም፡፡

2. ራስን ማወቅ-Self-knowledge ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ እውነተኛ ስሜቶቻቸውንና የውስጥ ፍላጎቶቻቸውን ይረዳሉ። ሁልጊዜ ራሳቸውን የመፈተሻ ጊዜ አላቸው፡፡ ሶቅራጠስ የተባለው የግሪክ ፈላስፋ “ራስህን እወቅ” (know yourself) ከሚለው ሃሳቡ ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡ አንዳንድ የስነ ልቦና ባለሙያዎች፤ ራስን መፈተሽንና ራስን ማወቅን ትኩረት ሰጥተው እንዲመለከቱ “ደንበኞቻቸውን” ያበረታታሉ።

ራስን ስለማወቅ ካነሳን የ ጆሃሪ ‘መስኮት’ን (Johari window) ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ስብዕናችን አራት ክፍሎች እንዳሉት የሚጠቁም ሲሆን አንደኛው እኛ የምናውቀው ሰዎችም የሚያውቁት ማንነታችን ነው(open or free area)፡፡ ይሄ እንግዲህ የተገለጠ ማንነታችን ነው፡፡ ሁለተኛው እኛ የማናውቀው፣ ሌሎች ግን የሚያውቁት ማንነት ነው(blind area ይባላል):: ሌላው እኛ ከሌሎች የደበቅነው ምስጢራችን ነው (hidden area) ይህም ማለት እኛ እናውቀዋለን፤ ሌሎች ግን አያውቁትም፡፡ የመጨረሻው እኛም ሌሎችም የማናውቀው ማንነታችን ነው (unknown area)፡፡ ይህ የመጨረሻው በተለይ በገጠመኞች ወይም በካውንስሊንግ ወይም በስልጠናዎች ብቅ የሚልና ለእኛና ለሌሎች የሚገለጥ ማንነት ነው። ያልተገለጠው አቅማችንም (potential) እዚህ አራተኛው የማንነታችን ክፍል ውስጥ ተደብቆ ነው የሚገኘው፡፡

አንድ የስነልቦና ባለሙያ “ደንበኛው” ስለራሱ እንዲያውቅና አቅሙን እንዲያወጣ ይረዳዋል። ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ያውቃሉ፣ይረዳሉ፡፡ 3. በራስ መተማመንና ራስን መግዛት-Self-confidence and self control ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች በራሳቸው መተማመን አላቸው። በግላቸው መስራት ያለባቸውን ማንንም ሳይፈልጉ ይሰራሉ፤ ከሌሎች ጋር ሆነው መስራት ያለባቸውንም ነገር ሃሳባቸውን በግልፅ በማቅረብ አብረው ይሰራሉ፡፡ ድርጊታቸውንና አካሄዳቸውን እንደሚቆጣጠሩት ያምናሉ፡፡ የብዙ ሰዎች ችግር የበታችኝነት ስሜት ነው፡፡ ሰዎች የበታችነት ስሜት እየተሰማቸው ከሄደ፣ ነገሮችን ሁሉ ከውጫዊ ምክኒያቶች ጋር የማያያዝ አባዜ ይጠናወታቸዋል፡፡ ይህም ማለት ገዢ ምልከታቸው (locus of control) ውጫዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሁለት አይነት ገዢ ምልከታዎች አሉ፡፡ እነዚህም የውስጥ (internal) እና የውጪ (External) ገዢ ምልከታዎች ይባላሉ:: የሰዎች ባህሪ በእነዚህ ሁለት ምልከታዎች ከፍተኛ ተፅእኖ ይደርስበታል፡፡ የእነዚህ ሁለት ገዢ ምልከታዎች ምንነትና በሰዎች አኗኗር ላይ የሚፈጥሩት ተፅእኖ ቀላል አይደለም፡፡

የውስጥ ገዢ ምልከታ(internal locus of control) ያላቸው ሰዎች በህይወታቸው ያሉ ስኬቶች የራሳቸው ጥረትና ውሳኔ ውጤቶች እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ባይሳካላቸው ደግሞ አስፈላጊውን ጥረት ባለማድረጋቸው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህም ምክኒያት በህይወታቸው ለሚሆነው ነገር ሃላፊነትን ይወስዳሉ። እነዚህ ሰዎች የራሳቸው እሴትና እምነት ንግግራቸውንና ድርጊታቸውን ይወስናል። ለደረሱበትና ለሚገጥሟቸው ነገሮች አግባብ የሆነ ሃላፊነትን ይወስዳሉ።

የውጪ ገዢ ምልከታ (external locus of control) ያላቸው ሰዎች በህይወት የሚገጥሟቸው ስኬቶች ወይም ውጤቶች የተገኙት በእድል ወይም ከነሱ በላይ በሆነና ከበረታ አካል እንደሆነ ያምናሉ(ለምሳሌ በማህበረሰቡ፣ በተቀጠሩበት ድርጅት፣ ወዘተ)፡፡ በዚህ ምክኒያት ለውድቀታቸውና ላልተሳካላቻው ነገር ሃላፊነትን አይወስዱም፡፡ ሃላፊነቱ የሌላው አካል ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም ምክኒያት ለንግግራቸውና ለድርጊታቸው መሰረታዊ ምክኒያት የሌሎች ስሜት፣አመለካከትና እምነት ነው። “ የእናቴ መቀነት አደናቅፎ ጣለኝ” እንደማለት ሰበበኛ ይሆናሉ፡፡ እኔ ግብ ስላላስቀመጥኩ፣ እኔ በትጋት ስላልሰራሁ፣ ላስቀመጥኩት ግብ እቅድ አውጥቼ ስላልተንቀሳቀስኩ፣ የሚፈለግብኝን ትኩረት ስላልሰጠሁ ወዘተ ይሄ ሆነብኝ አይሉም ማለት ነው፡፡ በተቃራኒውም ለድላቸው ወይም ለስኬታቸው የእነሱ ወሳኝ ሚና እንዳለ ስለማያምኑ፣ ራሳቸውን በመሸለም ደስታን አያጣጥሙም ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ራሳቸውን የሚገዙ ሰዎች በተንኳሽና ምላሽ (stimulus-Response) አያያዛቸው ይታወቃሉ፡፡ተንኳሾች (Stimulus) በቃልና በድርጊት ወደ እኛ የሚመጡ ምላሽን (Response) የሚጎተጉቱ ወይም የሚፈልጉ ነገሮች ናቸው፡፡

ስቲቨን ኮቬይ የተባሉ ሰው ስለ ተንኳሽና ምላሽ ፅንሰ ሃሳብ በሰፊው ያብራራሉ፡፡ እኚህ ሰው እንደሚሉት፤ በተንኳሽና ምላሽ መካከል አንድ የማሰቢያ ነፃነት ስፍራ (space) አለ፡፡ ወደ ህይወታችን ተንኳሽ ሲመጣ ምላሹ ጥሩ ወይም መጥፎ እንዲሆን የምንወስነው በዚህ የማሰቢያ ነጻነት መጠቀም ስንችል ነው በማለት ያስረዳሉ።

አንድ ተመሳሳይ ተንኳሽ ወደ ሁለት ሰዎች በአንድ ጊዜ፣ በተመሳሳይ ቦታና ሁኔታ ቢመጣ የሁለቱ ሰዎች በተንኳሹ መጎዳት ወይም መጠቀም የሚወሰነው በአመዛኙ በተንኳሹ ተፈጥሮ ሳይሆን ለተንኳሹ በሚሰጡት ምላሽ ነው፡፡ ለዚህም ነው በዚህ የተንኳሽና ምላሽ ፅንሰ ሃሳብ ትንታኔ፣ ሰው ተንኳሽ ሲገጥመው ለአፍታ “ቆም ብሎ” ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ የሚገባው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው ተንኳሹን መቆጣጠር አለመቻላችንና መቆጣጠር የምንችለው ምላሻችንን መሆኑን ነው፡፡

በአመዛኙ ባህሪያችንን (የምንናገረውንና የምናደርገውን) የሚወስነው ወደ እኛ የሚመጣው ተንኳሽ ሳይሆን ለተንኳሹ የምንሰጠው ምላሽ መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ተንኳሽ ሲመጣ ወይም ሊመጣ እንደሚችል ስንገምት የማሰቢያ ጊዜ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ራስን የመግዛት አቅማችንን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በመጽሃፍ ቅዱስም ላይ ከተማን ከሚገዛ ራሱን የሚገዛ እንደሚበልጥ ተፅፏል፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ከንቲባ ከመሆን ራስን መግዛት ምን አይነት ልዕልና እንደሆነ ነው፡፡

ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች በራሳቸው ይተማመናሉ ራሳቸውንም ይገዛሉ። 4. ግልፅ የሆነና መጠነኛ ተስፋ ያለበት የተጨባጭነትን እይታ-A clear (though slightly optimistic) perception of reality ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ገሃዱን ወይም ተጨባጩን ዓለም የሚያዩበት መንገድ ትንሽ ተስፋ ጠብ ያለበት ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ተጨባጭነት (reality) ምንድነው? በሚለው ነገር ስምምነት አለ፡፡

ከዚህ ስምምነት በተለየ መልኩ ማፈንገጥ ስነ ልቦናዊ ችግር ነው ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያለው ሰው ስለ ራሱ አቅም(potenial) እና ስለ ወደፊት ህይወቱ መጠነኛ “አረንጓዴ መብራት” ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም ተስፋ ማለት ነው-ከተጨባጩ ትንሽ አንድ እርምጃ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ ባይኖር ህይወት ምን ትመስል ነበር? ለማሰብ ያስቸግራል፡፡

5. ድፍረትና ነገሮችን መቋቋም መቻል-Courage and resilience ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያለው ሰው የራሱን ፍርሃት የመቋቋምና ሃላፊነትን የመውሰድ ድፍረት አለው። አስፈላጊ ሲሆንም ምክኒያታዊነት ላይ የተመሰረተ ሪስክ ይወስዳል። አዲስን ሁኔታ መላመድ ይችላል፡፡ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎችም (crises situations) ውስጥ ለመውጣት አቅም አለው። በተጨማሪም ጉድለቶችና ችግሮች በኑሮ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ በማወቅ ድክመቶችንና ችግሮችን ተቀብሎ ለማሻሻል ወይም ለመፍታት ይጥራል እንጂ አንዳች ጉድ እንደመጣበት አያስብም፡፡ ከወደቁበት ተነስተው፣አቧራቸውን አራግፈው ሁሉን እንደ አዲስ እንደሚጀምሩ ሰዎች ነገሮችን የመቋቋም ችሎታ አለው፡፡ 6. ሚዛናዊነት-Balance and Moderation ሚዛናዊ ህይወት መኖር የስነ ልቦናዊ ጤንነት መኖር መገለጫ ነው፡፡ ስራና ጨዋታን፣ሳቅንና ለቅሶን፣ ስሜታዊነትንና ምክንያታዊነትን፣ ንፉግነትንና ለጋስነትን ወዘተ… ሚዛናዊ በማድረግ መኖር ጥበብም እንደሆነ ይነገራል፡፡ “ብልህ ሰው እንቁላሎቹን ሁሉ በአንድ ቅርጫት ውስጥ አያስቀምጥም” የሚለው አባባል ከሚዛናዊነት ጋር አብሮ ይሄዳል። አርስቶትል የተባለው የግሪክ ፈላስፋ፤ “ጥበብ ያለበት ምርጫ ሁለቱን ተቃራኒ ፅንፎች ትቶ መካከለኛውን መምረጥ ነው” ይላል። አብርሃም ማስሎውም(Abreham Maslow) ግለሰቦች ከተፃራሪ ፍላጎታቸው አንዱን ከመምረጥ ተቆጥበው ሁለቱን ማስታረቅ ይጠበቅባቸዋል ይላል፡፡ ኪነር (Kinnier) በበኩሉ፤ መካከለኛን መንገድ በመምረጥ ግጭቶቻቸውን የሚፈቱ ሰዎች ፅንፍን ከሚይዙ ሰዎች ይልቅ ደስተኞች ናቸው ይላል፡፡ የሳይኮሎጂ አባት ተብሎ የሚጠቀሰውም ፍሮይድ(Freud) በግል ፍላጎትና በማህበረሰብ ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ ሚዛናዊነትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ሚዛናዊ ናቸው፡፡ 7. ሌሎችን መውደድ-Love of others ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ሌሎችን ይወዳሉ፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ትዕዛዝ፣ ሁለት የስነ ልቦና ጤንነት አመልካቾችን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ከላይ በአንደኛ ደረጃ የጠቀስነውን ራስን መውደድና ይኸኛውን – ሌሎችን መውደድን። ሰው ራሱን ወድዶ ሌሎችን የማይወድ ከሆነ፣ የስነ ልቦና ጤንነቱ የተሟላ አይደለም፡፡ ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች፤ ለሌሎች ሰዎችና ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ደህንነት(welfare) ለመጠንቀቅ አቅምና ፍላጎት አላቸው፡፡ ባርባራ ስትሪሳንድ (Barbara Streisand) “ ሰዎችን የሚፈልጉ ሰዎች በዓለም ላይ በጣም ጤናማ ሰዎች ናቸው” ይላሉ።

የዓዕምሮ ጤንነት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች፤ በቤተሰብና በማህበረሰብ መታቀፍና የመውደድ አቅም መኖር እንዲሁም ሌላውን ሰው መቅረብ፣ የስነ ልቦና ጤንነት ቅድመ ሁኔታ ነው ብለው ያምናሉ። 8. ህይወትን መውደድ-Love of Life እርስዎ የተለያዩ የህይወት ገፅታዎችን ይወዳሉ? የስነ ልቦና ጤንነት ያላቸው ሰዎች ህይወት የያዘችውን የተለያዩ ገፅታዎች ያደንቃሉ፤ ደግሞም ይደሰቱበታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ንቁ፣ጉጉና በተለያዩ የህይወት ገፅታዎች የሚደነቁ ናቸው፡፡ ህይወትንም ለመማር፣ ለማደግና ከሌሎች ጋር የተለያዩ ነገሮችን አብሮ ለመካፈል እድል የምትሰጥ ናት ብለው ይደሰቱባታል፡፡ እነዚህ ሰዎች “ እግዚአብሄር የሰራት ቀን ይህቺ ናት፤ ሃሴትን እናድርግ፤ በእርሷም ደስ ይበለን” እያሉ በማለዳ ተነስተው ወደ ተሰጣቸው ቀን የሚገቡ ይመስላሉ።

9. በዓላማ መኖር-Purpose of life ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች በዓላማ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ትርጉም ያለውና ግብ ያለው ኑሮ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በኑሮ ውስጥ ትርጉም አጥቶ መኖር ደስታን ያሳጣል፣ተስፋንም ያጨልማል፡፡ “ማሞ ቂሎ” መንገድ ጀምሮ ሲሄድ ሲሄድ፣ አንድ መንታ መንገድ ላይ ደረሰና ቆመ፡፡ በአጋጣሚ “ስንዝሮን” አገኘውና “ የትኛውን መንገድ ልከተል?” አለው ስንዝሮም “ የት ለመሄድ ፈልገህ ነው?” ማሞ ቂሎም “ አይ አላውቀውም” ብሎ መለሰለት፡፡ስንዝሮም ቀበል አደረገና “ የትኛውንም መንገድ ብትከተል ያደርስሃል፡፡” አለውና ጥሎት ሄደ ይባላል፡፡ ዓላማ ይዞ የማይኖር ሰው፣ ልክ እንደ ማሞ ቂሎ መሄዱን እንጂ የት መድረስ እንደሚፈልግ አያውቀውም፡፡ አንዳንድ ሰው የት እንደሚሄድ ሳያውቅ፣በቀን ውስጥ ማንን እንደሚያገኝ ሳይወስን ከቤት የሚወጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ወደ ሳሪስ መንገድ ጀምሮ ድንገት መኪና ሲያገኝ መዳረሻው ፒያሳ ሊሆን ይችላል፡፡ “ ራዕይ የሌለው ህዝብ መረን ይወጣል” ተብሎ ተፅፎ የለ! የተከበራችሁ አንባቢያን፡- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ላይ የስነልቦና ችግር እንዳላቸውና በየዓመቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የስነ ልቦና ጤንነት መገለጫዎች በመገንዘብና የአዕምሮ ደህንነታችንን በመጠበቅ የተሻለ ስብዕና ባለቤት እንሁን፡፡

ምንጭ፥ -አዲስ አድማስ (Wednesday, July 2014 )


19 views0 comments
bottom of page