top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ለቆዳ ውበትና ጤንነት የሚጠቅሙ 16 የምግብ አይነቶች1. እስፒናች

እስፒናች ቆስጣ መሰል ቅጠል ያለው የአትክልት ዘር ሲሆን ቅጠሎቹ ከቆስጣ አነስ ይላሉ፡፡ እስፒናች በዋነንነት በውሰጡ የቫይታሚን ኤ (ቤታ ካሮቲን) እና ሲ ክምችት ያለው ሲሆን እነዚህ ሁለቱም ዓይነት ቫይታሚኖች የአንቲኦክሲዳንት አይነት ባህሪ ስላላቸው ቆዳችንንም ሆነ ሰውነታችንን በአጠቃላይ ከፍሪ ራዲካሎች ይከላከላሉ፡፡ ከማዕድናት ደግሞ ማግኒዥያም፣ ሴሌኒየም፣ እና ዚንክን ይዟል፡፡ እነዚህ ማዕድናቶች ደግሞ ለቆዳ መወጠር፣ ለደም ዝውውር፣ ለቆዳ ወዝ ቁጥጥር ወዘተ ትልቅ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡

2. ኪያር

ኪያወር በውስጡ ለቆዳ ውበት እና ጤንነት እጅግ በጣም የሚጠቅም ሲሊካ የሚባል ማዕድን ይዟል፡፡ ሲሊካ የቆዳን መዋቅር (Structure) የሚሰራውን ክፍል (Extra cellular matrix) እና ኮላጂንን በማምረትና ትክክለኛ የተፈጥሮ ጥንካሬ እንዲኖረው ከማድረግ በተቸማሪ በትክክል ስራውንም እንዲሰራ የሚረዳ ማዕድን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኪያርን አዘውትሮ መመገብ እና የኪያር የፊት ማስክ መቀባት ቆዳን ብሩህ እና አንፀባራቂ የሆነ ውበት ያላብሰዋል፡፡ የቆዳን እርጅናም ያዘገያል፡፡

3. ቀዩ፣ ቢጫውና ብርቱካናማው የፈረንጅ ቃሪያ

የፈረንጅ ቃሪያ በተለያዩ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች የታጨቀ ነው፡፡ ቀዩን ብንወስድ ይህንን የራሱን ቀለም የሰጠው ንጥረ ነገር ፍላቮይንይድስ ይባላል፡፡ ፍላይቮኖይንድስ በጣም ጠንካራ የአንታይኦክሲዳንት አይነት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤታ ካሮቲን የሚባለው የአን ታይኦክሲዳንት አይነት ባህሪ ያለው ቫይታሚንን የያዘ ሲሆን ይህም በቆዳችን ስባማ ክፍል ውስጥ ሟሙቶ ቦታ በመያዝ ይቀመጣል፡፡ በዚህም ምክንያት የቆዳን ህዋሳት ከፍሪ ራዲካል ለመከላከል ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቆዳን የመለወጥ ባህሪውን የመጠበቅ እና ሞላ ያለ እና ውብ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

4. አቮካዶ

አቮካዶን በሚመለከት ብዙ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት አላቸው፡፡ ይኸውም አቮካዶ ቅባትነት ስላለው ለጤና ጥሩ አይደለም ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስህተት ነው፡፡ ሁሉም የቅባት አይነቶች ለጤና ጥሩ አይደሉም የሚል ካለ ይህም ስህተት ነው፡፡ ለጤና ከመስማማት አልፈው መድሃኒት የሚሆኑ በተፈጥሮ የሚገኙ የቅባት አይነቶች አሉ፡፡ እንደዚሁም ለጤና የሚስማሙ የቅባት አይነቶች አሉ፡፡ ለጤና ከሚስማሙ የቅባት አይነቶች ውስጥ የሚገኙ ለጤና በጣም ተስማሚ የሆኑ ፋቲ አሲዶች ቆዳን የማለስለስ፣ የማጥራት እና ሙሉ የማድረግ ችሎታ አላቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የቫይታሚን ኢ ይዞታው ከፍተኛ ስለሆነ የቆዳን ህዋሶች ከፍሪ ራዲካሎች ጥቃት ይከላከላል፡፡ እንደሚታወቀው ፍሪ ራዲካሎች በተደጋጋሚ ከህዋሶቻችን ጋር በመጋጨት ነጻ ኤሌክትሮን ለመስረቅ የሚታገሉ ሽፍቶች ሲሆኑ በዚህ ሂደት እኛን በቀላሉ እንድናረጅ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ ቆዳ ያለ ጊዜው ቶሎ እንዲያረጅ ያደርጋሉ፡፡ የቫይታሚን ኢ ስራ ደግሞ በአንታይኦክሲዳንትነት ባህሪው ምክንያት ይህንን የፍሪ ራዲካሎችን ውርጅብኝ በመከላከል የቆዳን በቶሎ እና በፍጥነት ማርጀትን መቀነስ ነው፡፡

5. የስጎ ቅጠል

የስቆ ቅጠል ወይም ፓርስሊ በውስጡ በጣም ብዙ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ይይዛል፡፡ የቫይታሚን ሲ ይዘቱ በተለይ ከፍተኛ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በውስጡ የያዘው ጠቃሚ ዘይት በባህሪው የማሸናት ችሎታ ስላለው ይህ ደግሞ በውሃ ውስጥ የሚሟሙ ቆሻሻዎች እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡ የኩላሊት ስራንም ቀልጣፋ ማድረግ የሚችል ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች እንደ ሊቲዮለን የመሳሰሉ የአንታይኦክሲዳንት አይነቶችን በውስጡ ይዟል፡፡

6. ሽንኩርት (ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ባሮ፣ ፈሮ፣ ቻይቭስ)

ሽንኩርቶች አንድ የጋራ የሆነ የማዕድን ይዘት አላቸው፡፡ እርሱም ሰልፈር ነው፡፡ ሰልፈር የተባለው ማዕድን ደግሞ ቆዳ እንዳይሸበሸብ እና እንዲወጠር የሚያደርጉትን ኮላጅንን እና የቆዳችን መዋቅር የተሰራበት ረብ መሰል ክፍልን ለመስራት የሚያገለግል ነው፡፡ ስለዚህ በቂ የሆነ ኮላጅንና ይህ መሰል መዋቅር መመረት ከቻለ እና በጥሩ ሁኔታ ካለ ቆዳችን ውጥር ያለና ውብ ይሆናል፡፡

7. እንስላል

እንስላል ለምግብ መፈጨት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሲሆን ዘሩ፣ ቅጠሉ፣ ስሩም ጭምር ጠቀሜታ ላይ መዋል የሚችል የአትክልት አይነት ነው፡፡ እንስላል ልክ እንደ ስጎ ቅጠል ሁሉ የማሸናት ባህሪ አለው፡፡ ይህ ደግሞ ከሰውነታችን መውጣት ያለባቸውን በውሃ ውስጥ የሚሟሙ ቆሻሻዎችን በብዛት እና ቶሎ ቶሎ እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡ ቆሻሻ ከሰውነታችን በበቂ ሁኔታ ተወገደ ማለት ደግሞ የቆዳ ጥራት እና ፍካት ይጨምራል ማለት ነው፡፡

8 ቲማቲም

ቲማቲም የተለያዩ አንቲኦክሲዳት አይነቶችን ለምሳሌ ቤታካሮቲን፣ ላይኮፔን እና ፍላቮይንይድስ (flavonoids)ን አጭቆ ይዞ ሊፈነዳ የደረሰ የምግብ አይነት ነው፡፡ ስለዚህ ቲማቲም ህዋሶቻችንን ከፍሪ ራዲካል ጥቃት ሊታደግ የሚችል በቀላሉ የሚገኝ አትክልት ነው፡፡ በመሆኑም ቲማቲም ባለው አንታይኦክሲዳንት ብዛት እና አይነት ሳቢያ የቆዳን እርጅና ፍጥነትን የመቀነስ ችሎታ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮላጂንን ጥንካሬ እና የመለጠጥ ችሎታ የመጨመር ኃይል ስላለው የቆዳ መሸብሸብን ፍጥነት ይቀንሳል፡፡

9. ቀይ ስር

ቀይ ስር በውስጡ ቤታ ሳያኒን የተባለ ቅመም የያዘ ሲሆን ይህ ቅመም ለቀይ ስር ደማቅ ሀምራዊ ቀለም መያዝ ምክንያትም ነው፡፡ ይህ ቅመም በዋነኛነት ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ የጉበትን ቆሻሻ የማስወገድ ሥራ ማገዝ ነው፡፡ ይህም ማለት በሰውነት ውስጥ የሚገኙ መርዛማ የሆኑ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ የሚጠቅም ሲሆን መርዛማ ቆሻሻዎችን በመሰባበር ከሰውነት እንዲወገዱ ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዚያክሳቲን የተባለ አንታይኦክሲዳንት በመያዙ ህዋሶቻችንን ከፍሪ ራዲካሎች ሊታደግልን ይችላል፡፡ ይህ በአንጻሩ ቆዳ ቶሎ እንዳይሸበሸብ፣ ውብ እና ህይወት ያለው እንዲሆን ያደርጋል፡፡

ይህ የሚያሳየው እንግዲህ የሰውነትን የተፈጥሮም ይሁን ከውጭ ወደ ውስጥ የገቡትን ቆሻሻዎች በአግባቡ እንዲወገዱ ስናደርግ በቆዳችን ጥራት፣ ውበት እና ጤንነት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው፡፡

10. ስኳር ድንች

ስኳር ድንች በውስጡ ቆዳ አፍቃሪ የሆነውን የአንቲኦክሲዳንት አይነት ቤታ ካሮቲንን በብዛት የያዘ ነው፡፡ ቤታ ካሮቲን ደግሞ በተደጋጋሚ በብዛት እንደተመለከትነው በቆዳችን ስባማ ክፍል ውስጥ በመጠራቀም የቆዳችንን ኮላጂንን እና ኢላስቲን የተባሉ ቆዳን የመለጠጥ እና የመወጣር ባህሪን የሚያላብሱ ክፍሎችን ከፍሪ ራዲካሎች ጥቃት ይከላከላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቆዳ ቶሎ እንዳይሸበሸብ እና እንዳያረጅ ያግዛል፡፡ ሌላው ቤታ ካሮቲን በ‹‹አንቲ ኢንፍላማቶሪ›› ባህሪው ምክንያት የቆዳን መቅላት፣ ማበጥ እና ህመም የማከም ችሎታ አለው፡፡

11. አጃ

አጃ የቫይታሚን ቢ ቤተሰቦችን አሰባስቦ የያዘ የምግብ አይነት ነው፡፡ የቫይታሚን ቢ አይነቶችን ሰብስቦ መያዙ በቆዳ ውስጥ ለሚከናወኑ ሥራዎች ለምሳሌ፣ ለቀልጣፋ የደም ዝውውር፣ ለቆዳ ውበት እና ለቁስል መዳን እንዲሁም የወዝ መጠን ቁጥጥር ወዘተ በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ምግብ የቫይታሚን ቢ አይነቶችን በውስጡ ከያዘ ቆዳ በተሟላ ሁኔታ ስራውን እንዲያከናውን፣ ውብ እና ጤናማ እንዲሆን ይረዳል፡፡

12. ተልባ

ተልባ ኦሜጋ ስሪ ፋቲ አሲድ በውስጡ የያዘ በመሆኑ ቆዳን የማለስለስ፣ የቆዳ መቅላትና ማበጥ እንዲሁም ህመምን መከላከል የሚችል ምን አለፋችሁ ሁለገብ የምግብ አይነት ነው፡፡

ስለዚህ ተልባን በምግባችን ውስጥ አካተን መመገብ ስንጀምርና ስናዘወትር ወዙ የሚያምር፣ ለስላሳ እና ሙሉ የሆነ ቆዳ እንዲኖረን በከፍተኛ ሁኔታ ይረዳናል፡፡

13. የዱባ ፍሬ

የዱባ ፍሬ ለቆዳ ጤንነት እና ውበት ከሚጠቅሙ ማዕድናት ውስጥ ዚንክን የያዘ ሲሆን የበሽታ መከላል አቅምን ከፍ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም እንደ ብጉርና በኢንፌክሽን አማካኝነት የሚፈጠሩ የቆዳ ችግሮችን ይዋጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኦሜጋ 3 እና 6 ፋታ አሲድን በውስጡ ይይዛል፡፡

14. የሾርባ ቅጠል ግንድ

የሾርባ ቅጠል በውስጡ የተለያዩ አይነት ማዕድናትን የያዘ ሲሆን ለመጠቀስ ያህል ፖታሲየም፣ ሶዲየም፣ ማግኒዥየም ወዘተ… ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ማዕድናት ሰውነታችን የሚያስፈልገውን መጠን ያህል ፈሳሽ ለቆዳ ውበት መጠበቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የቆዳ እርጥበት መጠን ሲጠበቅ ወዙ፣ ውጥረቱ፣ ሙሉነቱ፣ አንጸባራቂነቱ፣ ፍካቱ ሁሉ ጎልቶ የቆዳውን ውበት ያሳያል፡፡

15. ሽንብራ

ሽንብራ በውስጡ ዚንክ የሚባል ንጥረ ነገር የያዘ ሲሆን የቆዳን ወዝ መጠን ለመቆጣጠር እና ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ዚንክ የቆዳ ወዝ ሲበዛም ሆነ ሲያንስ ሚዛኑን የጠበቀ የወዝ መጠን የወዝ ዕጢዎች እንዲያመነጩ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ሌላው በሽንብራ ውስጥ የሚገኝ ጠቃሚ ነገር ደግሞ ፋይበር ነው፡፡ ፋይበር ደግሞ እንደሚታወቀው አንጀትን ለማፅዳት ይጠቅማል፡፡ ይህም ማለት የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ቆሻሻ ቶሎ ቶሎ እንዲወገድ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ይህ ቆሻሻ በአንጀት ውስጥ በቆየ ቁጥር እነዚህ መርዞች በደም ስር ውስጥ ተመልሰው ሰርገው በመግባት ወደ ሰውነታችን ይሰራጫሉ፡፡ የዚህ ሁኔታ ውጤት ደግሞ ጤንነታችንን ከማወኩ በተጨማሪ ቆዳችንን ህይወት የሌለው እና አመዳም፣ ድካም የተላበሰ አይነት ፊት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ይህ የሚያመለክተው ቆሻሻ ለሰውነታችን በፍጥነት በተወገደ ቁጥር የተሻለ የቆዳ ጤንነት እና ጥራት ይኖረናል፡፡

16. ጥቁር ቦለቄ

የቦለቄ ዘሮች ብዙ አይነት ናቸው፡፡ ቀይ፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ ዥንጉርጉር የመሳሰሉት ሲሆኑ ሁሉም የየራሳቸው ጥቅም አላቸው፡፡ ጥቁሩ ቦለቄ ለብቻው መነሳቱ ከቆዳ አንፃር ያለውን ጥቅም ለማስረዳት ነው እንጂ ሁሉም አይነት ቦለቄዎች የሚሰጡት ጥቅም ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡

በእኛ በኢትጵያዊያን ዘንድ ግን እንደውም ጭራሹኑ ዞር ብሎ የሚያያቸው ያን ያህል ነው፡፡ በእርግጥ የሸክላ ማሰሮዎችን ለማስጌጥ ተጠቅመውበት አይቻለሁኝ፡፡ እጅግ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ፈጠራውን በጣም ባደንቅም እውነቱን ለመናገር የተሰማኝ ስሜት ግን አንድ ትንሽ ልጅ ሳያውቅ በጣም በውድ ዋጋ የገዛችሁትን አንድ ንብረት አግኝቶ በሌላችሁበት ሲጫወትበት ብታገኙት የሚሰማችሁን አይነት ነው፡፡

ጥቁር ቦለቄ በአንደኛ ደረጃ የቫይታሚን ቢ ቤተሰቦችን በውስጡ አጭቆ የያዘ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቆዳን በተለያየ መልኩ መርዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ዚንክ የተባለውን ማዕድን በውስጡ ይዟል፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ዚንክ ደግሞ የቆዳ ወዝ ሚዛኑ እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የቆዳን ኢንፌክሽ የሚያስከትሉ የቆዳ ችግሮችን ለመከላከልም ይጠቅማል፡፡

ጥቁር ቦለቄ ሽፋኑ ጥቁር እንዲሆን ያደረገው በውስጡ የያዘው አንቶሳያሊን የተሰኘ የአንቲኦክሲዳንት አይነት ነው፡፡ ይህ አንቲ ኦክሲዳናት ደግሞ በቀዩ ወይን ውስጥ ከሚገኘው አንቲኦክሲዳንት ጋር አንድ አይነት ሲሆን በዋናነት የቆዳን መቅላትና ማበጥ ብሎም ህመም የሚያስከትሉ የቆዳ ችግሮችን ለመከላከል እና ለማከም ይረዳል፡፡

ሌላው ጥቅሙ ደግሞ የማይሟሟ የፋይበር አይነት መያዙ ነው፡፡ ይህ ፋይበር በሌሎች ጥራጥሬዎች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም በጥቁር ቦለቄ ውስጥ የሚገኘው ግን ለየት ያለ ነው፡፡ በአንጀታችን ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች ይህንን ፋይበር ሲያገኙት በቀላሉ እንዲብላላ በማድረግ ቡትሪክ አሲድ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ቡትሪክ አሲድ ደግሞ የአንጀትን ግድግዳ የማደስ ችሎታ አለው፡፡ በተጨማሪም ቆሻሻ ከአንጀታችን ውስጥ በፍጥነት እንዲወገድ የማድረግና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች በቀላሉ በአንጀት ግድግዳ እንዲመጠጡ የማድረግ ችሎታ አለው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተደጋግፈው ውጤቱ ቆዳችን ላይ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ ይኸውም ጥርት፣ ፍክት፣ ውጥር ያለ፣ ውብና ጤናማ ቆዳ ነው፡፡

ምንጭ - ማህደረ ጤ


86 views0 comments
bottom of page