top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ወዳጅና ጓደኛዎ ማነው? ስለ ጥቃቅን ነገሮች መከታተል - ክፍል ሦስትክፍል አንድ ላይ ወዳጅና ጓደኛ ምን እንደሆነና እንደት እንደሚገኝ ባጭሩ ቀርቧል። ክፍል ሁለት ላይ ደግሞ ወዳጅነትን ለማጠንከርና ለመጠበቅ ጥርጣሬን ማጣራትና ማስወገድ፤ ከዛም አፍራሽ ነገር ከማሰብ ይልቅ ገንቢ ስለመሆን አቅርቤአለሁ። አንደኛውና ሁለተኛውን ክፍል ከሶስተኛው ክፍል ጋር ግንኙነቱን ለማወቅ ከፈለጉ መጀመሪያ የመጀመሪያወቹን ሁለቱን ክፍሎቹን ማንበብ አለብዎት። እዚህ ሦስተኛው ክፍል ላይ ደግሞ ጥቃቅን ስህተቶችን መከታተል የቱን ያህል አፍራሽ እንደሆነና መፍትሄዎችንም አብረን እናያለን።

ጥቃቅን ስህተቶችን መከታተል ህይወትን ያከብዳል።

ሰወች ጥቃቅን ስህተቶችን በተደጋጋሚ የሚከታተሉት ለምድነው? ህይወት ማክበዳቸውን ስለማይረዱት ነው ይመስለኛል። በተቃራኒው ደግሞ ሰወች አንድ አይነት ቀላል ስህተቶችን የሚደጋግሙት ለምድነው? ካለፈው ስህተታቸው መማር ስለማይችሉና ልብ ስለማይሉ ነው።

ሰው በተፈጥሮው አውቆትም ሆነ ሳያውቀው የሚደብር ስህተትም ሆነ አመል አለው። ይህ ቀላል ስህተትና አመል ተቀባይነቱ እንደ አስተናጋጁ ይለያያል። ሆኖም ግን የወዳጅን ጥቃቅን ስህተቶች አቻችሎና ሚዛን አድርጎ መኖር ይቻላል። እንደሚመስለኝ ይህንን ሚስጥር ለብዙ ዘመን አብረው የኖሩ ባልና ሚስቶች ያውቁታል። ለብዙ አመታት በወዳጅነት የቆዩ ወዳጆች ያውቁታል። ከልጅነት ጀምሮ በጓደኝነት የቆዩ ያውቁታል።

ያሰብኩት ዋናው ነጥብ ግን ጥቃቅን ስህተቶችን በመከታተል ምክንያት የተገነባውን ሊያፈርስ እንደሚችል ለማሳየት ነው። ጥቃቅን ስህተቶች ለምሳሌ ለቤተሰብ ወተት ሳይገዙ ረስቶ ወደቤት መምጣት ሊሆን ይችላል። ወዳጅዎ ጋር ሆነው ስልክ ተደውሎልዎት በስልክ ረዘም ላለ ጊዜ ወሬ ማውራት ሊሆን ይችላል። ሁሉንም ነገር መጥቀስ ስለማይቻል ሁለት ምሳሌወች ብቻ ነው የጠቀስኩት። ስለዚህ ወተቱን በተመለከተ ወይም ወደሱቅ ተመልሶ ወዲያውኑ መግዛት ነው። ወይም ለነገ ማስተላለፍ ነው። በወተት የተነሳ ቤተሰብ ውስጥ ኬኩ በምን ሊሰራ ነው? ልጆቹ ምን ሊጠጡ ነው? እያሉ ጭቅጭቅ፣ ማጠንጠንና ማባዛት አያስፈልግም። ስልኩን በተመለከተ ወዳጅዎን ይቅርታ ብለው ባጭሩ ንግግርዎን መጨረስና በኋላ ብቻወን ሲሆኑና ጊዜ ሲኖርዎት መደወል ይሻላል። አስቸኳይ ከሆነም በቅድሚያ ለወዳጅዎ መንገር ይመረጣል።

ጥቃቅን አመሎች ደግሞ ለምሳሌ ሲሄዱ፣ ሲያዛጉ፣ ሲስሉ፣ ሲዘገዩ፣ ሲበሉ፣ የውሸት ፈገግታ ሲያሳዩ ወዘተ የሚያሳዩት የሰውነት ቋንቋ ሊሆን ይችላል። የህዝብ ማመላለሻ ስለዘገየ መራገም ሊሆን ይችላል። እነዚህንና ተመሳሳይ ልምዶችን በራስዎ ማሻሻል ቢችሉም ወዳጅዎም በዚህ መደንገጥ የለበትም። በዚህ ምክንያት ወዳጅነት መሻከር ወይም መቀነስ የለበትም። ሌላውን ትልቁን ስዕል ማየት ይሻላል።

ትንሿ ጥፋትና አመል ስንት አመት ሙሉ የቆየ ወዳጅነት ማፍረስ የለባትም። ስንት አመት ሙሉ የተገነባ ትዳር መበተን የለባትም። ትንሽ ነገር መከታተልና ጸጉር መሰንጠቅ ከየት ጀምሮ የት እንደሚደርስ ወዲያውኑ አይታወቅም። በምትኩ ግን ቀስ ብሎ ከወዳጅ ወይም ከቤተሰብ ጋር መነጋገርና መፍትሄ ማግኘት ይቻላል። በመነጋገር መፍትሄ የሌላቸው አንዳንድ ቀላል ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች አንዳንድ ጸባያቸውና በሚወዱት ነገር ላይ ድርድር አይፈልጉም። የነዚህን ግለሰቦች የማይጎዳ ፍላጎትና አመል ለምዶና ችሎ መኖር አንዱ ለወደጅ ወይም ለቤተሰብ የሚከፈል መጽዋትነት ነው። ለምሳሌ እርስዎ አንዳንድ ሰወች ላይ የሚደብር ጸባይ ሊያዩ ይችላሉ። በተቃራኒው ግን እርስዎም ለሌሎች የሚደብር ጸባይ ሊኖረዎት እንደሚችል ማወቁ ጥሩ ነው። ይህንን ልብ ካሉ አንዳንድ ነገሮችን ለማለፍና ለመቀበል እንዲችሉ ይረዳዎታል። እራስዎንም እንዲያዩ ያደርገዎታል። ዋናው ነጥቡ ለምሳሌ በረጅሙ ከሰው ጋር ወዳጅ ለመሆን፣ ቤተሰብዎ ውስጥ ፍቅር ለማብዛትና ከሰው ጋር አብሮ ለመስራት ከፈለጉ ጥቃቅን ጸባይ ወይም ስህተቶችን መቀበልና ማለፍ አለብዎት ማለቴ ነው። ትልቁ ስዕል ላይ ማተኮር አለብዎት። 2% እጅ እንኳን የማትሆን ስህተት ሌላውን የ 98% እጁን የለፉበትን የስንት ጊዜ ወዳጅነት መበከል የለባትም።

ምንጭ - ታታሪው


12 views0 comments
bottom of page