top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"እንብላ!" እንደምንለው ሁሉ "እንስራ!" ብንል ኖሮ የት እንደርስ ነበር? "አካላዊ ስራ"



የመጀመሪያው ዙር ላይ ስለ "ምግብና አመጋገብ" ነበር። ሁለተኛው ዙር ላይ ስለ "የአስተሳሰብ ስራ" ነበር። አሁን ሶስተኛው ላይ ደግሞ "አካላዊ ስራ" የሚለውን እናያለን።

ለማስታወስ ያህል ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት ስራ ሲባል ሃሳባዊና አካላዊ ናቸው። ሰው ካሰበና ከወሰነ በኋላ ዝም ካላለ በስተቀር እርምጃ ይወስዳል። ይህ እርምጃ ሃሳብን ወደ ትርጉምና ቅርጽ ይለውጠዋል። ብዙውን ጊዜ የሃሳብ ውጤቶች የሚገኙት በአካላዊ ስራ ነው። አካላዊ ስራ ለምሳሌ መጻፍ፣ መገንባት፣ መጠገን፣ ማምረት ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ሃገራችን ውስጥ ከከተሜው ይልቅ አርሶ አደሩ የበለጠ ይሰራል ብሎ ማመን ስህተት አይሆንም። ከተሜ ስል በተለይ የተማረውን ኢትዮጵያዊ ክፍል ማለቴ ነው።

ይህ ጽሁፍ የሚመለከተው ዲያስፖራውንና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ከተሜ ብቻ ነው። ከተሜ ስል ሁሉንም ከተሜ ባይሆንም አብዣኛውን ግን ይመለከታል። ትንሽ ለማስታወስ ያህል አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት የሚያጠቃን "ሃሳባዊና አካላዊ" ስራወችን አጣምረን በደንብ ስለማንሰራቸው ነው። የጃፓኖች ጭንቅላት፣ ጀርመኖች የሚሰሩት እቃ፣ ብራዚሎች የሚጫወቱት እግር ኳስ፣ የኖርዌይ ሃብትና የአኗኗር እርዳታ፣ የቻይና ባጭር ጊዜ ውስጥ ማደግ፣ የአሜሪካኖች ሃይል፣ የእንክሊዞች እንግሊዘኛ፣ ወዘተ የሚነገርላቸው ባጭሩ ስለሰሩ ብቻ ነው። እኛም ኢትዮጵያውያን ስለምናውቀው እናወጋላቸዋለን።

እኛ ግን በጥንቶቹ እናትና አባቶቻችንን ምክንያት አሁንም ይባርክልንና ከሌሎቹ ሃገሮች የማይተናነስ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ቋንቋ የመሳሰሉት አሉን። ያሁኑ የኛ ትልቁ ችግር የዱሮውን የሆነና ያልሆነ እያስታወስን ለመበቀል ወይም ለመኩራት መሞከራችን ነው። መበቀል ለሚፈልጉ የኔ አስተያየት አሁን ያለው ሌላ ትውልድ ነው። መኩራት ለሚፈልጉ የኔ አስተያየት አሁን ጊዜው የመኩሪያ ብቻ ሳይሆን የስራ ጊዜ ነው።

ጥሩ ባህል አለን እንላለን? ኢትዮጵያዊ ጨዋ ነው እንላለን? ስለ ባህልና ጨዋነት ባልከራከርም የኔ ጥያቄ "እሺ፤ ጥሩ ባህል ያለንና ጨዋወች ከሆን ለምን ወደኋላ ቀረን?" ከልምድ እንደማየው ብዙ ኢትዮጵያውያን ሰራቸው ነካ ነካ ስለሆነ ነው። አንደኛ ስራችን እቅድ ያንሰዋል። እቅድ ስለሚያንሰው ስራወችን በሂሳብ አንሰራቸውም።

ይህንን በምሳሌ ላስረዳ። ብዙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በየአጋጣሚው ሰርቻለሁ። በየአጋጣሚው ስብሰባወችና ዝግጅቶች ሄጃለሁ። ሰዓት አይከበርም። ሲጀመርም ጥሩ አጀንዳ ስለማይኖር ልቅ ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ ስብሰባወች ዘግይተው ያልቃሉ። ጥያቄወችና አስተያየቶች ይደጋገማሉ። ድብልቅ ቋንቋ መናገር የተለመደ ነው። ጭቅጭቅ ሊኖር ይችላል። ስብሰባውን ተቆጣጥሮ የሚነዳና የሚጨርስ መሪ ማግኘት ብርቅ ነው። ቅድመ ዝግጅት ስለማይኖር የሆነ ነገር በተደጋጋሚ አይሰራም። አቤት ሲያሰለች። በዚህ ምክንያት የሚቀሩ ሰወች አውቃለሁ።

ሰዓት እንዲከበር መጀመሪያ አዘጋጆች ተዘጋጅተው በቦታው መገኘትና በመጣው ሰው መጀመር ስራቸው ነው። በዚሁ ከቀጠለ ይለመዳል ይመስለኛል። ስራ ላይ አልዋለም እንጂ በርካታ የማውቃቸው ሰወችም በዚህ ይስማማሉ። አዘጋጅ አጀንዳውን አዘጋጅቶ በአጀንዳውና በሰዓቱ መሰረት ስብሰባውን ማካዜድና በሰዓቱ መጨረስ ስራው ነው። ስብሰባው ዘግይቶ እንዳያልቅ የስብሰባው መሪ ስብሰባውን መስመር ማስያዝ ስራው ነው። ጥያቄወችና አስተያየቶች ሲደጋገሙ የስብሰባው መሪ ማስረዳትና ወደፊት መሄድ ስራው ነው። በተቻለ መጠን ቋንቋ አጥርቶ መናገር እራስን መቆጣጠር ሃሳባዊና የአፍ አካላዊ ስራ ነው። ጭቅጭቅ እንዳይነሳ የስብሰባው መሪ ሃላፊነት አለበት። ድንገት የተበላሸ ነገር ካልሆነ በስተቀር ቴክኒካዊ ነገሮች በቅድሚያ እንዲሰሩ የስብሰባ ጠሪወች ስራ ነው። የስብሰባ ጠሪወች ገና ያልመጣውን ከመጠበቅ ይልቅ በመጣላቸው ሰው መጀመርና የመጣለቸውን ሰው ማክበር ስራቸው ነው።

ሌሎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ጥያቄወች ደግሞ ትኬት ግዛኝ፣ ቶምቦላ ግዛኝ፣ የሆነ ነገር ስራልኝ፣ በህብረት የሚሰራ ስራ ላይ ጥያቄ ተጠይቆ ወይም መልስ ካገኙ በኋላ ጸጥ ማለት፣ የሆነ ሃላፊነት ወስዶ ምንም መረጃ አለመስጠት፣ ደንበኞችን ለመንከባከብ መርሳት፣ መሪ ሲሆኑ አብሮ ከመስራት ይልቅ ማዘዝ ብቻ ላይ ማተጎር ወዘተ ናቸው። ምሳሌወቹ ብዙ ናቸው።

ትኬት ግዛኝ ብሎ የትእዛዝ ጥያቄ ከመጠየቅ፤ የዚህ አይነት የሚሸጥ ቲኬት ስላለኝ ገስተሃል ወይ ብሎ መጠየቅ የሻጩ ስራ ነው። የሆነ ነገር ስራልኝ ከማለት እኔ ይህን ሞክሬ አልሰራልኝ አለ እና ልትረዳኝ ትችላለህ ወይ ብሎ መጠየቅ የተሻለ ነው። መጀመሪያ ሰው እራሱ ለመስራት መሞከር አለበት። አብሮ የሚሰራ ስራ ላይ አስተያየት ስጡበት ወይም በዚህ ቀን ስብሰባ ስላለ መልስ ስጡ ሲባል አስተያየት ካልተሰጠበትና መልስ ከሌለ ስራ አይሰራም። ሰው ሃላፊነት ከወሰደ በየጊዜው አባላትን መረጃ መስጠትና ማመስገን የሃላፊው ስራ ነው።

ምናልባት ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች ለሰወች ቀላል ሊመስላቸው ይችላል። ቀላል ይሁኑም ከባድ አብዛኛወቻችን ስራወችን በደንብ እንደማንሰራ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ህብረተሰቡ ውስጥ አብሬ ስለምኖር የጻፍኩት ውሸት አይደለም። ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ መጀመሪያ ሰወች በትንሹም ነገር መለማመድ አለባቸው ይመስለኛል። ለዚህም ነው መጀመሪያ እናታችን ማህጸን ውስጥ እንጸነሳለን፣ ዘጠኝ ወሮች አካባቢ ማህጸን ውስጥ እናድጋለን፣ እንወለዳለን፣ ጡት እንጠባለን፣ መብላት እንጀምራለን፣ እናድጋለን። ይህን ለውጥ የምናሳየው የተፈጥሮ ሂሳብ ስለሆነ ነው። ከዛም በኋላ ህጻናት መዋያ እንሄዳለን፣ ት/ቤት እንገባለን፣ ሙያ እንማራለን፣ ስራ እናገኛለን፣ ቤተሰብ እንመሰርታለን ወዘተ። ይህ ለውጥ ደግሞ ህይወታችንን ለማሻሻል የምናደርገው ለውጥ ሂሳብ ነው። ምሳሌው ከጊዜ ጋር የሚደርሱ ለውጦችን ለማሳየት ነው።

ስራ የምንሰራ ይመስለናል እንጂ ስራወች በሂሳብና በእቅድ አይሰሩም። ለዚህም ነው ከጊዜ ጋር ለውጥ የማናየው። ይህ ጽሁፍ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የመስራትና የመብላት ባህሪያችንን ለመግለጽና የመፍትሄ ሃሳብ ተሰጠበት እንጂ ማንንም በደመወዝ ተቀጥሮ የሚሰራውን ስራ አይመለከትም።

ምንጭ - ታታሪው


5 views0 comments
bottom of page