top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ሰይጣን ብሄር የለውም"ሰላም አለም ከመፈጠሯ በፊት ነበር። ሰላም አለም ከተፈጠረች በኋላም ነበር፡፡

ተፈጥሮ ህይወት ያላቸውን ነገሮች ህይወት የሌላቸውን ነገሮች ካበጀች በኋላም ሰላም ነበረች፡፡ ህይወት ያላቸው ነገሮች፣ በተለይም በራሳቸው የሀሳብ ፈቃድ እንዲኖሩ ተፈጥሮ የፈቀደችላቸው ፍጡራን፣ ከተከሰቱም በኋላ በምንኖርባት ዓለማችን ላይ ሰላም ነበረች፡፡

አለም ከተፈጠረችም፣ ይኖሩባት ዘንድ ፍጡራንን ከተሸከመች በኋላም ሰላም ነበረች፡፡የሀይማኖት አስተምሮዎችም ይህንን እውነት ይገልፁልናል፡፡ በታሪክ ውስጥ ሰላም የቀደመ ነባራዊ ገጿ እየተበላሸ የመጣው፣ የሰው ልጅም ይሁን እንደእርሱ ተቀራራቢ የማገናዘብ አቅም ያላቸው ፍጡራን፣ ሰላማዊ በሆነችው ዓለማችን በፈቃዳቸው እንዲመላለሱ ነፃነት በተሰጣቸው ጊዜ ስለመሆኑ የሀይማኖት ሊሂቃኑም ይሁኑ ቅዱሳት መፃህፍቱ ይናገራሉ፡፡

በዚህች አለም ላይ ለሰው ልጅ ነፃነት የሰጡት ሁለት ፈቃዳዊ የመኖር መንገዶች ወይም የመመላለስ ዓይነቶች ክፋትና መልካምነት ናቸው፡፡ መሰይጠንና መሰልጠን ፡፡ በተለይም ከህያዋን ሁሉ እጅግ የማገናዘብ ተፈጥሮ የሰው የሰው ልጅ ነፃነቱን ከተቀዳጅ በኋላ በሁለቱም መንገዶች ላይ እየኖረ ወይም እየተመላለሰ ነው፡፡ በመልካምነት መንገድ ሲመላለስ ሰላም አብራው ትጓዛለች፡፡ በክፍት መንገድ ስራመድ ደግሞ ተቃራኒው ይሆናል፡፡ ሰላምን ያጣል፡፡

በሰው ልጅ በመልካምነት እና በክፋት መንገዶች መመላለሶች ምክንያት በዓለማችን ላይ የሚታየው የሰላም እጦት ወይም ሰላማዊ ዓለም መኖር መነሻው የእያንዳንዱ ሰው አይምሮ ነው፡፡ ምንጩ የሰው ልጅ ሀሳብ ነው -በሌላ አነጋገር፡፡ ምንጩ የሰው ልጅ የአይምሮ ስክነት (Calminess) ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሰይጣን ብሄር የለውም ፡፡

አንድ ሰው በቤቱ ውስጥ ለሚኖረው ሰላም አስተዋጽኦ አለው፡፡ አይምሮው የሰከነ እና በአስተውሎት የታቀኘ ከሆነ ከርሱ የሰከነ አይምሮ የሚነሳው ሀይል አካባቢውንም የሰላም ሀይል ያፈስበታል፡፡

ለምሳሌ ያህል ፀጥ ያለ ባህር ውስጥ አንድ ጠጠር ወርውር፣ የወረወርከው ጠጠር ከጠለቀበት ስፍራ የተነሱ የማዕበል ቅርድዶች አካባቢውን በሙሉ በመከታተል ይሸፍኑታል፡፡

የሰላም ጉዳይም ተመሳሳይ ነው:: የአንድ ሰው ስክነት አካባቢውን ያሰክነዋል፡፡ የአንድ ሰው የክፋትና ተግባር ደግሞ፣ ያካባቢውን ሰላም ፀጥ ያለውን ባህር በምቱ ምክንያት ዙሪያውን ተራ በተራ በሚከታተሉት የበማዕበል ቅርድዶች እንደመነቃነቁ አካባቢውን ሊያውክ፣ ዱላው እስከባህሩ ዳርቻ ድረስ ሊመዘዝ ይችላል፡፡ ከዳርቻው ዘሎ ሊወጣም ችላል ፡፡ ድንበር ይሻገራል ፡፡

በሌላ አነጋገር ግለሰብ ወደ ቤተሰብ፣ የቤተሰብ፣ ወደ ጎረቤት፣ የጎረቤት ወደ አካባቢ፣ ወደ ክልል፣ ወደ ሀገር፣ የቀጠና፣ የአህጉር ፣ የዓለም ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህም የሰላም ምንጩ በየግለሰቦች ውስጥ ያለው የአይምሮ ስከነት ድምር ነው ወደሚል ድምዳሜ ይወስደናል፡፡ ዞሮ ዞሮ አለም ሰላሟን ማጣት የጀመረችው ሰው በፈቃደ ሀሳቡ፣ በምርጫው መኖር በጀመረ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሰው ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ከሰው ጋር ተቀራራቢም ይሁን በየደረጃው የማገናዘብ ልክ ፣ ፈቃዳዊ የኑሮ ምርጫቸውን መከተል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፡፡

የሀይማኖት አስተምህሮዎች እንደሚገልፁት የሰው ልጅ መጀመሪያ ከሁሉም ህልው ፍጡራን ጋር በደስታ ነበር የሚኖረው፡፡ ከርሱ ጋር ሲኖሩ ያጠቁኛል የሚል ስጋትመ ፍርሀትም አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያውን የክፋት ሀሳብ፣ ርኩስ መንፈስ ካሰበ ወዲህ ባሉት ጊዜያት በሰው ልጆች መካከል ሰላም ጠፋ ፡፡

ጥንት፣ በመጀመሪያው ዘመን ፣ እኚህ አሁን ዱር አደርና አዳኝ የሆኑት እንስሳት እንኳ አድና መብላት የሚባለውን ነገር አያውቁትም ነበር፡፡

ሁሉም ምገባቸው ሳርና ሌሎች እጽዋት እንደነበሩ ይተርካሉ- አበው የሀይማኖት አባቶችም፤ ቅዱሳት መፃህፍትም፡፡ ከአንዳንዶቹ አራዊቶች መካከል የአዳም አቅም ደካማ ሆኖ ሳለ እንኳ በዚያን ጊዜ አላደኑትም፡፡ በሰላም ፣ ተስማምተውና ተዋህደው ነበር ህይወታቸውን የሚገፉት፡፡

የሰው ልጅ በክፋት መንገድ መመለስ ከጀመረ በኋላስ፡፡ መልካምነትን ጥሎ መልካም ባልሆነ መንገድ መጓዝን ምርጫ ባደረገ ጊዜስ፡፡ ሰላሙን አጣ፡፡ ይኸው የሰላም እጦት በምርጫ ምክንያት እየቀጠለ ሄደ፡፡ ቃኤል አቤልን ገደለ፡፡

ቃኤል አቤልን ከገደለ በኋላ ግን በመልካም መንገድ የሚመላለሱ ሰዎችን በመፍራት ህሊናው፣ አይምሮው ተቃውሷል፡፡ ጭንቀት እላዩ ላይ ተከመረበት፡፡ ግራ መጋባት መረበሽ ፣መቅበዝበዝ ፣ መንከራተት እጣፈንታዎቹ ሆኑ፡፡ መልካም ባልሆነው መንገድ መራመድ ሲጀምር የሰው ልጅ እነዚህን የስነልቦና ቀውሶች ወደዚህ አለም በገዛ ዕጁ ስቦ አመጣ፡፡ ሰላሙን ከራሱ አሸሸ በገዛ -ፈቃዱ፡፡

ስክነት(Calmness) መገለጫ መንገዶቹ ሁለት ናቸው፡- በውስጣችን ይገለፃል፡፡ ከውስጣችን ባሻገርም በውጫያዊ ፣ በአካላችን ላይ ይገለፃል፡፡

በሁለት መንገዶች በኩል የሚገለፀው የሰው ልጅ ስክነት አሀዶች (Elements) አሉት፡-

የመጀመሪያው የውስጥ ስከነት ነው፡፡ የውስጥ ስክነት ማለት ደግሞ ከስሜታዊ ነገሮች ነፃ መሆን፣ ከጭንቀት ነፃ መሆን፣ የልቦና መረጋጋት እንዲሁም ረጋ ብሎ በማስብ ይገለፃል፡፡

ሁለተኛው የሰውነታችን ወይም የአካል ክፍሎቻችን መስከን ነው፡፡ ሁለተኛው የመጀመሪያው ተከታይ ነው፡፡ ከስሜታዊነት ነፃ ባልሆንን ጊዜ ፣በጭንቀት ባርነት ውስጥ በወደቅን ጊዜ፣ የልቦና መረጋጋትን በተነጠቅን ጊዜ፡፡ ለነዚህ የውስጥ ስክነት እጦቶች አካሎቻችን የሚሰጧቸው ምላሾች አሉ፡፡

የልባችን ሞት ይጨምራል፡፡ እጆቻችን ለዱላ ይነሳሉ፡፡ እግሮቻችን ይሮጣሉ፡፡ አይኖቻችን ያፈጣሉ፡፡

የሰውነት ስክነት ማለት እነዚህን ነገሮች በቁጥጥር ስር ከማዋል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የስሜት ህዋሶቻችን የሚነገሩንን ነገር አለማዳመጥ፡፡ እንቅስቃሴዎቻችን በርጋታ የተሞሉ እንዲሆኑ መዘዝ መቻል ነው፡፡

ሶስተኛው የነርቭ ክፍሎቻችን ስክነት ነው፡፡ የነርቮች መስከን የቁጡነትን ስሜት ከራስ ማራቅ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ንዴትን በሳቅና በደስታ ስሜት መገደል፡፡

አራተኛው አንደበትን ከሀይለ-ቃል መቆጠብ ነው፡፡ የጩኸት ድምፆችና ንግግሮችን ፣በተረጋጋጉ ድምፆችና አንደበቶች አሸንፎ መገኘት፡፡

አምስተኛው ከባህሪ ጋር ይያያዘል፡፡ በማህበራዊ ተራክቧችን ወቅት የባከነ ባህሪና ትርኢት የሆነ አቀራረብ ግንዛቤ በማድረግ ችግሮችን የመፍታት ባህሪ ባለቤት መሆን ነው፡፡

እዚህ ላይ ግን እውነተኛ ስክነት (Calmness) ምንጩ ከውስጥ ነው፡፡ ውስጣችንን ካሰከንን ሌሎቹን ማለትም ውጪያዊ የስክነት ማጣት ወይም የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች አይከሰቱም ፡፡ ካልተከሰቱ፣ እነሱን በመመከት የሚባክን ሀይልና ጉልበት የለም፡፡

ስለዚህ እውነተኛ ስከነት ያለው ሰው ሰላማዊ ነው፡፡ ከውስጡ የሚነሳው ሰላም በመላ አካሉ ላይ ስለሚገለጽ ጭምር ስታዩት ገና ይማርካችኋል፡፡ ውበቱ ወደርሱ ይስባችኋል፡፡ ታፈቅሩታላችሁ፡፡ በስክነቱ ምክንያት ከርሱ ጋር በማንኛውም ጉዳይ ቀርቦ ለመነጋገር ትወዳላችሁህ፡፡ እርሱ አውነተኛ የውስጥ ስክነቶች ያሉትና የተገለጡበት ሰው በመሆኑ ብትናደዱበት ወይም ብትበሳጩበት እንኳ የሰከነ አቀራረቡ በብስጭታችሁ ላይ ይነግሳል፡፡

የሰከነ ሰው ሰላማዊ ነው፡፡ ሰላማዊ የሆነ ሰው ደግሞ የሰከነ ነው፡፡ ጎዳና ላይ የጩኸት ድምጽ እያሰማ ሁክት አይፈጥርም፡፡ ሰውነቱን የተቆጣጠረ በመሆኑ ለግጭት አይሮጥም፡፡ እጁን ለጠብ አያነሳም፡፡ ሰዎችን በቁጣ ድምጽ አይናገርም፡፡

ምክንያቱም ችግሮችን በጉልበት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ የመፍታትን ሚስጥራዊ ሀይሎች ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

ሰላም የሚደፈርሰው በሁለት ስክነት በጎደላቸው ሰዎች መካከል እንጂ በሰከነ ሰውና ስክነት በራቀው ሰው መካከል አይደለምና፡፡

እነዚህን ቁምነገሮች ይዘን፡፡ አሁን አገራችን ፣አሁን ክልላችን፣ አሁን አካባቢያችን ውስጥ የሚታዩ የሰላም መደፍረሶች እናጢን፡፡ ወጣትነት የጉልበት ጊዜ ነው፡፡ ይህን በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ የማይገኝ አካላዊ ጉልበት በሰከነ አይምሮ መሪነት መቆጣጠር ካልቻልን ሌሎችን እንጎዳለንም እራሳችንም እንጎዳለን፡፡

ያልሰከነ አይምሮ የሚያመነጫቸው መልካም ያልሆኑ ሀሳቦች፣ እነዚህ መልካም ያልሆኑ ሀሳቦች በሰውነት ክፍሎቻችን ፣በስሜት ህዋሶቻችን፣በስሜት ህዋሶቻችን በሚታዘዙ የጩኸት ድምፆቻችንና ሀይል የተቀላቀለበት ሩጫዎቻችን በሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሰው ሊያልፉ ይችላሉ፡፡

በሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳቶች አድርሰው ቢያልፉም ዳሩ እኛ ላይ ጥለውት የሚያልፉት የስሜት ጠባሳ ግን የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ጭንቀት ፣ፍርሀት፣ በሀሳብ መባዘን፣ ከህብረተሰብ መገንጠል፣ መንከራተት፡፡ እነዚህ የውስጥ ስሜት መረበሾች ደግሞ በአካሎቻችን ላይ በሚያደርሷቸው ተፅዕኖች ህልውናችንን እስከማጣት ወደሚያደርስ ኪሳራ ይዘው ይነጉዳሉ፡፡ ልዩነቱ ይህኛው የህይወት ጊዜ ስቃይ መሆኑ ፣ መርዘሙ ነው፡፡ የቃኤል መንከራተት መሆኑ ፡፡

እናስ ምን እናድርግ? አሁን በሀገራችን ውስጥ የሚታዩትን ግጭቶች ለማስወገድና ከነዚህ የህይወት ዕዳዎች ለማምለጥ ሁላችንም ፣እያንዳንዳችን፣ በተለይም ወጣቶች ስክነት ያስፈልገናል፡፡ ስንሰክን ኪሳራችንን እንቀንሳለን፡፡ መግባባትን እንፈጥራለን፡፡ ፍቅርን እናተርፋለን፡፡ ሰላምን በመንበሩ እናነግሳለን፡፡

ይህ ከሆነ እውነተኛ ስክነትን ገንዘባችን ለማድረግ የምንከተላቸው መንገዶችስ ምን ይሁኑ? የስክነት ባለቤት ለመሆን ማከናወን የሚገቡን ነገሮች ምን ምን ይሁኑ?

የመጀመሪያው ስኩን ሰው መሆንን ማፍቀር ነው፡፡ ማወቅና መገንዘብ ያለብን ዋናው ችግሮችን በሀይል ለመፍታት ወይም ደግሞ ለጥያቄዎቻችን መልስ ፍለጋ ሀይልን ወይም ጉልበትን ምርኩዝ አድርጎ ከመንቀሳቀስ መራቅን ነው፡፡

አንድ ሰው ስክነት የሌለው ከሆነ፣ ራሱን ይረብሻል፡፡ ሌላውንም ያውካል፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ መፍትሄ ከማስገኘት ይልቅ የሰላም መደፍረስን አብዝቶ ወደማባባስ፣ ከማሸጋገር ውጪ ትርፍ አያስገኙም፡፡

ሁለተኛው ነገር የተፈጥሮ ስክነት ነው፡፡ የሰከነ ተፈጥሯዊ አካባቢ በዙሪያችን መገኘቱ ለኛም የአምሮ ሰክኖ መገኘት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ማራኪ የተፈጥሮ ገፃችን መጎበኘት፡፡ አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ፡፡ በቆሸሸ አካባቢ ምክንያት፣ በስሜት ህዋሶቻችን ላይ የሚፈጠሩ ጫናዎችን ማግለል፡፡

ሶስተኛው ነገር ሰላምና ስክነትን የሚያወርሱ ሀይማኖታዊ ስፍራዎች ማፍቀር፡፡ በነገራችን ላይ እስከቅርብ ጊዜ ባለው ፍልስፍና የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ተደርገው የሚወሰዱት ምግብ መጠለያ ለብስ ነበሩ፡፡ አራተኛው መሰረታዊ ፍላጎት ሀይማኖት እንደሆነ ስምምነት ተፈጥሮበታል፡፡ እናም ለስክነታችን ወደነዚህ ስፍራዎች መቅረብ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡

አራተኛው የልቦና ስክነት ነው፡፡ ሰዎች ባለፉ ጊዜያት የደረሱባቸውን አካላዊም ስነልቦናዊ ጉዳቶች ብቻ እያሰቡና እያመነዠኩ ከመኖር ክፉ ቁራኛ መላቀቅ አለባቸው፡፡ ማሰብ ያለባቸው ለችግሮቹ መፍትሄዎች ብቻ ነው፡፡

ከሰከኑ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መፍጠር ሌላው መንገድ ነው፡፡ መረጋጋትና ስክነት ከጎደላቸው ሰዎች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ካሉ፣ ግንኙነቶቹ የሰከነውን የኛን አይምሮ ወዳለመረጋጋትና ወዳለመስከን ይወስዱታል፡፡ ችግሮቻቸው ወደኛ ይገባሉና፡፡

ከብዙ ጥቂቶቹን አነሳን፡፡ ስለዚህ አሁንም ምርጫው እጃችን ላይ ነው፡፡ ምርጫችን ደግሞ ከሰላም ውጪ አይደለም ሰላማችን ስክነትን አንፈልጋት፡፡

እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ልብ ማለት አለብን፡፡ ይኸውም ስክነት በማጣት ምክንያት ሰላም ከደፈረሰና ጉዳቶችን ካስተናገድን በኋላ ለመስከን አይሁን ጉዟችን፡፡ ሰላማችን ሳይደፈርሰ፣ ጉዳቶችን ሳናስተናግድ ስክነን መገኘት ይሁን እንጂ ምርጫችን፡፡

ሰላም ለሁላችን፣ ሰላም ለአገራችን!!


59 views0 comments
bottom of page