top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሚጥል በሽታ – epilepsy



የሚጥል በሽታ – epilepsy

በሃገራችን በብዛት እንደሚታሰበው የክፉ መንፈስ ሳይሆን፣ የአእምሮአችን ህዋሳት ከትክክለኛው ስርአት በተለየና በበዛ መልኩ ሲነቃቁ የሚከሰት በሽታ ነው። አንድ ሰው የሚጥል በሽታ አለበት ለማለት ምልክቶቹ ቢያንስ ሁለት ጊዜ መከሰት ይኖርባቸዋል። በሽታው መታከም የሚችል ችግር ማሆኑን አውቆ ታማሚን ወደ ህክምና ቦታ ማምጣት ብልህነት ነው።

የሚጥል በሽታ ምልክቶቹ ምንድናቸው?

የበሽታው አገላለጽ ከበሽታው አይነት ሊለያይ ይችላል። በብዛት የሚታየው የበሽታው አይነት ጠቅላላ ሰውነትን የሚያንዘፈዝፍ ሲሆን በዚህ ጊዜ ታማሚዎች ራሳቸውን ይስታሉ። ታማሚው ከዚህም በተጨማሪ አይን ወደላይ ሲሰቅል እና አረፋ ሲደፍቅ ይታያል። በአንዳንድ የበሽታው አይነቶች ላይ ምልክቱ ከመታየቱ በፊት ራስ ምታት፣ የልብ የመምታት ስሜት፣ የእይታ ብዥታ ሊታዩት ይችላሉ። ይህም ከ አንድ እስከ ሁለት ደቂቃ ሊቆይ ይችላል። ታማሚዎቹ ከነቁ በኋላ የሁነውን ነገር ለማወቅ እና ለማስታወስ ይሳናቸዋል። ለተከታይ ደቂቃዎችም ሽንትና ሰገራቸውን መቆጣጠር ይሳናቸዋል።

ለበሽታው እንዴት ልጋለጥ እችላለሁ?

ለአብዛኛው የሚጥል በሽታ ተጠቂዎች የበሽታውን መነሻ ለማወቅ ይቸግራል። ነገር ግን የሚከተሉት ችግሮች ለበሽታው መከሰት የራሳቸውን አስተዋጾ ያበረክታሉ።

  • በቅርብ የቤተሰብ አባላት ላይ ተመመሳሳይ በሽታ መኖር

  • በእናት የእርግዝና ወራት የተከሰቱ ችግሮች

  • በጭንቅላት ላይ የደረሰ ጉዳት ወይም አደጋ

  • ወደ ጭንቅላት የተሰራጨ ካንሰር

  • የደም ውስጥ ስኳር መጠን ማነስ

  • የአደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነት

  • ተደራቢ በሽታዎች፡ ለምሣሌ፦ የጭንቅላት ወባ

የበሽታው መዘዞች

በሽታው በተደጋጋሚ በሚከሰትበት ወቅት ሌሎች ችግሮችን አያይዞ ያመጣል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡

  • ከ30 ደቂቃ በላይ የሚቆይ ማንቀጥቀጥ

  • መገለልና መድሎ

  • የግጭት አደጋዎች

  • የአእምሮ ዘገምተኝነት

  • ድንገተኛ ሞት

እነዚህን አስከፊ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ለመቆጣጠር ምልክቶቹ በታዩበት ጊዜ በአፋጣኝ አቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል።

የሚጥል በሽታ ህክምና ምንድነው?

የተለያዩ የላብራቶሪ ምርመራዎች ከተደረጉ በኋላ የኢኢጂ እና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ የኤም አር አይ ምርመራዎች የደረጋሉ። እነዚህ ምርመራዎች ለሐኪሙ የችግሩን መንስኤ እንዲረዳና ከዚህም ተነስቶ ትክክለኛውን መድሃኒት ለማዘዝ ያስችሉታል። ከዚህም በተጨማሪ በሽታውን የሚያባብሱትንና የሚያስነሱትን መንስኤዎች በመረዳት ማስወገድ ያስፈልጋል። የሚሰጠው መድሃኒት እንደየበሽታው አይነት የሚለያይ በመሆኑ ምርመራዎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው።

መድሃኒት መውሰድ ከጀመርክ የመድሃኒቱን ስራ ከሚያስትጓጉሉ ነገሮች እና ለአደጋ ከሚያጋልጡ ባህሪዎች መጠበቅ ይኖርብሃል። እነዚህም፡

  • አልኮል መጠጥ

  • አደንዛዥ ዕጽ ለምሣሌ፦ ጫት

  • ከፍተኛ ቦታዎች

  • ዋና … ናቸው።

በበሽታው ህክምና ጥሩ ልውጥ ለማግኘት ከተፈለገ ሐኪም ጋር ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። በቀጠሮ ቀን በመሄድ በሽታው ያሳየውን መሻሻል መገምገም ይኖርበታል።

በበሽታው የተያዘ ማንኛውም ሰው በትምህርት ራሱን ማሳደግ፣ ማግባት፣ መውልድ እና ቤተሰብ መመስረት ይችላል።

የሚጥል በሽታ ያለበትን ሰው እንዴት ልረዳው እችላለሁ?

በሃገራችን ውስጥ የሚዘውተሩት ባህላዊ መንገዶች ማለትም ክብሪት መጫርም ሆነ ውሃ መርጨት፣ ለህመምተኛው የሚሰጡት ጥቅም የለም። እነዝህ መንገዶች የሚጠቅሙ የሚመስለን ችግሩ ሲከሰት የሚፈጀው ጥቂት ደቂቃ በመሆኑ ነው።

በመጀመሪያ መረጋጋት ያስፈልጋል። ከዚያም በአፋጣኝ የህክምና ሰጪ አካላት ጋር (ለምሳሌ፡ ቀይ መስቀል) በመደወል እገዛ እንዲደረግ ማስታወቅ ይኖርብሃል። በመቀጠልም ህመምተኛው የወደቀበት ስፍራ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ድንጋይ፣ የመስታወት ስባሪ የመሳሰሉ ነገሮችን ከአካባቢው በማራቅ ህመምተኛውን ከተጨማሪ አደጋዎች መጠበቅ ትችላለህ። ልብሱን በመከፋፈትም ጭንቀቱን መቀነስ ትችላለህ። ከዚያም ወደጎን በማስተኛት ወደአፍ የሚገቡ ነገሮችን እንዳይውጥ መከላከል ይቻላል። ይህንን በመድረግ የመታነቅ ችግር እንዳይገጥመው ትከላከላለህ። ምላሱም ወደ ውስጥ ገብቶ መተንፈስ እንዳስቸገረው ከተመለከትክ ፣ ምላሱን በማስወጣት ሰላሙን ላትመልስላት ትችላለህ።

የተጠሩት የጤና ባለሙያዎች በአካባቢው ሲደርሱ የተመለከትከውን በሙሉ በአግባቡ በመግለጽ ለመዳን ያለውን ተስፋ መጨመር ትችላለህ።

source : addishealth


39 views0 comments
bottom of page