top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የህይወታችንን 50 እጅ አካባቢ ቤት ውስጥ እንቆያለን! "የምንተነፍሰው የቤት ውስጥ አየርስ?"



የህይወታችንን 50 እጅ አካባቢ ቤት ውስጥ እንቆያለን! "የምንተነፍሰው የቤት ውስጥ አየርስ?"

በደንብ ላናስተውል እንችል ይሆናል እንጂ 50 እጅ አካባቢ የሚሆነውን የህይወታችንን ጊዜ ቤት ውስጥ እንቆያለን። ለምሳሌ በስራ ወይም በትምህርት ምክንያት ለስምንት ሰአቶች ያህል እና አራት ሰዓቶች አካባቢ በዚህም በዛም ውጭ ልናሳልፍ እንችላለን። ቀሪወቹ 12 ሰዓቶች ደግሞ ለምሳሌ ስምንቱ ለእንቅልፍ ከሆኑ ቀሪወቹ አራቱ ሰዓቶች ቤት ውስጥ ለሚደረጉ የተለያዩ እንቅስቃሴወች እናውላቸዋለን። ይህንን ነገር ያነሳሁት የህይወታችንን ግማሽ አካባቢ የሚሆነውን ጊዜ ቤት ውስጥ እንደምንቆይ ለማሳየት ነው። በተጨማሪ ደግሞ ውጭ እንደምናገኘው አይነት አየር ቤት ውስጥ ማግኘት ከባድ መሆኑንም ለማሳየት ነው። የምንስበው አየር ልክ እንደምንበላው ምግብ ለጤንነታችን በጣም ወሳኝ ነው።

የቤት ውስጥ አየርን በቀላሉ እንደት ማሻሻል እንደሚቻል የሞከርኩትንና ያገኘሁትን ልምድ ለማካፈልና ለማሳሰብ ነው። ምናልባት ማሳሰቢያዎቹን ሙሉ በሙሉ የማድረግ አጋጣሚ ከሌለውና አንድ ክፍል ውስጥ እንኳን ቢኖርም ባለቤቱ እራሱ ተመሳሳይ እርምጃ ማዳበር ይችላል። የመኖሪያ ቤት ስፋት የተለያየ ቢሆንም የተሻለ አየር ቤት ውስጥ ለማግኘት ግን መሰረተ ሃሳቡ አንድ አይነት ነው። የተለየ ምክንያት ኖሮት ከቤት ውስጥ ይልቅ ውጭ በብዛት የሚቆይ ሰው አይጠፋምና ይህ ማሳሰቢያ ላይመለከተው ይችላል።

ይህ ማሳሰቢያ የቤት ውስጥ አየርን ለማሻሽል ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል። ምናልባት ከዛሬ ጀምሮ ደስ እያለዎት ጥሩ የቤት ወስጥ አየር መተንፈስና መሳብ ይጀምሩ ይሆናል። ማን ያውቃል? አንዳንድ ቤቶች የአየር ማንሸራሸሪያ ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም በቀላሉ ቤት ውስጥ ንጹህ አየር እንዲበዛ ማድረግ ይቻላል። ቤት ውስጥ ንጹህ አየር ለማግኘት፤ ንጽህናን መጠበቅና በራፍ ወይም መስኮት ብርግድ አድርጎ ከፍቶ የውጭ አየር ማስገባት ዋናወቹ እርምጃወች ናቸው። የውጭ አየር ማስገባት (በጥሩ አማርኛ ማናፈስ ይባላል) ና ንጽህናን በተመለከተ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃወች የሚከተሉት ናቸው፤

  • ኩሽና አካባቢ ያለ ቆሻሻ፤ ሽታ ከመፍጠሩ በፊት መጣል።

  • መጸዳጃና መታጠቢያ ቤትን በተከታታይ ማጽዳት።

  • የሚታጠቡ ልብሶችን እስከሚታጠቡ ድረስ ከተቻለ በማስቀመጫ በረንዳ ላይ ማስቀመጥ። ወይም አየር አፍኖ በሚይዝ ማስቀመጫ ማስቀመጥ። ቆሽሸው ለመታጠብ የተዘጋጁ ልብሶች ከጠበቅነው በላይ የቤትን ጠረን ይበክላሉ።

  • አልጋ ልብስ ላይ የሚያስቸግር አቧራ በአይን የማይታዩ ነፍሳቶች ናቸው። አልጋ ልብሱ በ95 ዲግሪ (ከ65 ዲግሪ በላይ) ከታጠበ ነፍሳቶቹ ስለሚሞቱ የአልጋ ልብስ አቧራ እጅግ በጣም ይቀንሳል።

  • ሳሎን፣ መኝታ ቤትና ኩሽና በሚያስፈልገው ጊዜ ማጽዳት።

  • እቤት ውስጥ ሳያስፈልግ ብዙ ኮተት አለማብዛት። ኮተት በጨመረ ቁጥር ቆሻሻ ወይም አቧራ ይከተላል።

  • ሻማ ለሮማንቲክ እራት፣ ቤት ለማሞቅ፣ ለአመት በዓል ወዘተ ደስ ቢልም ሻማው የሚቃጠለው በኬሚካል ድጋፍ ስለሆነ የቤት ውስጥ አየር ያበላሻል። ብዙ ሰው ሻማ ይወዳል ግን ሻማ እንደተወዳጅነቱም ጉዳት አለው። ሻማ የቱን ያህል የቤት አየር እንደሚያበላሽ ለማወቅ ሽታውን ልብ ማለት ነው። በተለይ በማጥፊያም ይሁን ተጠንቅቀው ሲያጠፉት ይታወቃል። ይህን ስል ደግሞ ሻማ እንዳለ እርግፍ አርጎ መተው ሳይሆን በልክ መጠቀም ይሻላል ለማለት ነው።

  • ጫማ ከሸተተ ወደ ቤትም መትረፉ ስለማይቀር እግርን በየቀኑ በደንብ መታጠብና ካልሲ በየቀኑ መቀየር።

  • አንዳንድ ሰወች ሽቶ የመሳሰለ ቤታቸው ውስጥ ይነፋሉ። ሽቶ የቤቱን አየር ማበላሸትና ሌላ አይነት ሽታ ይፈጥራል እንጂ አይረዳም። በዚህ ፋንታ ይልቅ በራፍ ወይም መስኮት በደንብ ብርግድ አርጎ ከፍቶ በንጹህ አየር ቤቱን ማናፈስ የበለጠ ተፈጥሯዊ ነው። ማናፈስ የምግብ ሽታንም ይቀንሳል። ቤቱ ውስጥ ያለው አየር ጥሩ መሆኑን ለማወቅ ከውጭ ወደ ቤት ሲገቡ ልብ ካሉ ይታወቃል።

ምንጭ - ታታሪው


25 views0 comments
bottom of page