top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ተመራመር ይገኛል ቁምነገር ለምን ተባለ?አባቶቻችን 'ተመራመር፥ ይገኛል ቁምነገር ብለው ነበር፡፡ እኛም ለመሻሻል በሚበጁ ነገሮች ላይ መመራመር ይጠበቅብናል፡፡ መመራመሩ የግድ አውሮፕላን ለመስራት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እያንዳንዳችን የተለያየ ተሰጥኦና ችሎታ አለን፡፡ ለማደግና ለመሻሻል ሲባል ማንኛውንም ነገር ጠለቅ ብሎ ማየቱ ለመሻሻል ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ የምናስበውን ሃሳብና የምንሰራውን ስራ በአግባቡ ለማሻሻል መጣር እራሱ መመራመር ነው፡፡ አስተሳሰባችንና አሰራራችን ጥራት እንዲኖረው መጣርና እራሳችንን ለለውጥ ማዘጋጀት እራሱ የመመራመር ክፍል ነው፡፡ ያለውንና የነበረውን ነገር ለማሻሻል መጣር እራሱ መመራመር ነው፡፡ እኛ ግን እነዚህ ነገሮች በደንብ ስለማናስብባቸውና አቅለን ስለምናያቸው ለብዙ ዘመናት ሳይለወጡ እንዳሉ ቆመዋል፡፡

ሰው እንኳን ሰላም ስንል 'ሰላም' የምትለዋን ቃል በዜማ ማለቱና አለማለቱ ልዩነት አለው፡፡ ፈገግ ብሎ ሞቅና ጠበቅ ያለ ሰላምታ መስጠትና ፊትን አጥቁሮ ጋራ ጋራውን እያዩ ሰላምታ ማቅረብ ልዩነት አለው፡፡ ለዘመናት እንዳደረግነው ሁሉ፥ ሁል ጊዜ ባለንበት መሄድ የለብንም፡፡ አዲስ ምግብ ቤቶችና ሆቴሎች ተከፍተው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ምግቡ የማይጥምና አገልግሎቱም የማይስብ መሆን የለበትም፡፡ ንፅህናና አገልግሎቱም መጨመር እንጂ መቀነስ የለበትም፡፡ ደንበኞችን ለማርካትና ለማስደሰት የምግብ ቤቱ አገልግሎትና ንጽህና መጨመር እንጂ መቀነስ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ለማደግና ለመሻሻል ደንበኞችንም ለመሳብና ለማስደሰት ሲባል ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው ማሰቡና መመራመሩ የሚጠቅመው፡፡

ለስራ ታታሪዎች ጥቂቶቻችን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ጊዜና ጉልበታችንን እንዲሁም ዕውቀታችንን በመጠቀም ብቻ በቀላሉ የሚሻሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ ጠለቅ ብለን በማሰብ በተገቢው መንገድ ለማትረፍና ደንበኞችንም ለማስደሰት መለወጥና መመራመር የግድ ነው፡፡ ነጋዴወችም ከሆንን ደንበኞችን አታለን በከፍተኛ ዋጋ ዕቃ ከመሸጥ ይልቅ ደንበኞች የሚፈልጉትንና የሚወዱትን ነገር ከሌለን ሌላ ሱቅ ወይም ቦታ ማሳየት መቻል አለብን፡፡ በፈገግታ ደንበኞችን አስተናግደን ጥሩ አገልግሎት ከሰጠናቸው ወደእኛው ዘንድ ሌላ ጊዜ እንደሚመለሱ ማዋቁ በጣም ይጠቅማል፡፡ ደንበኞች በሚሰጣቸው አገልግሎት በረኩ ጊዜ ለሚያውቋቸውም የመንገራቸው እድል ሰፊ ነው፡፡

ስራንም በተመለከተ አንድ ሰው የሚሰራውን ስራ በርካታ ሆነን ስራው እንዴት እንደሚሰራ ማውራት አያስፈልገንም፡፡ መጨረሻም ላይ ስራው ሳይሰራ ይቀራል ወይም ይዘገያል፡፡ ይህንን በተለያዩ አጋጣሚወችና ቦታዎች ታዝቤአለሁ፡፡ ስራን በተመለከተ 'ሃኪሞች ሲመካከሩ በሽተኛ ይሞታል' እንደሚባለው እንዳንሆን ቆፍጠን ብሎ ላጥ ላጥ እያደረጉ በጊዜውና በቦታው ስራን መስራት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ማለት ታዲያ ብዙወቻችን በቀላሉ መሰራት ያለበትን ስራ ማክበድና በወሬ ብቻ መተንተን አያስፈልገንም፡፡ አስተዋጾኦም ሳናደርግ የሰሩትን ሰዎችና የተሰራውን ውጤት በገንቢነቱ ሳይሆን በአፍራሽነቱ ብቻ ጉድፈት ማውጣት ተገቢም አይደለም፡፡ ለቁምነገርና ለስራ የበለጠ ብንጥር ለኢትዮጵያና ለራሳችን ክብርና ዕድገት እጅግ ይጠቅማል፡፡ የሚያስከብረን ስራችንና ባህሪያችን እንጂ ነፃነታችን አይደለም፡፡ በነጻነታቸው መኩራት የሚገባቸው የጥንቶቹ አባቶቻችን እንጂ እኛ አይደለንም፡፡

ምንጭ - ታታሪው


10 views0 comments
bottom of page