• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

መፈጸም ያሉብንን ነገሮች እያስተላለፍን ከማስረፈድ ልማድ የምነወጣበት 11 መንገዶች:-ዴድላይንዎ ደርሷል። ቢሆንም ስራዎን እንደመፈጸም የማይረቡ ነገሮች እያደረጉ ነው። ፌስቡክ ይከፍታሉ፣ ፊልም ያያሉ፣ ኢንተርኔት ውስጥ ይዞራሉ ወዘተ። መስራት ወይም ማጥናት እንዳለብዎ እያወቁም አያቆሙም። ሁላችንም ስለነገር ማዘግየት በራሳችን እናውቃለን። ስናዘገይ ነጻ ግዜአችንን በከንቱ እናጠፋለን፣ መፈጸም ያሉብንን ነገሮች እስኪረፍድ እንተዋለን። ከረፈድ በኋላ ደግሞ ጭንቀት ውስጥ እንገባለን። አስቀድመን ለምን አልጀመርንም እያልን እራሳችንን እንወቅሳለን። ይህ ችግር በከፍተኛ ደረጃ የተጠናወታቸው ለአመታት ይህን ልማድ እንደዙር ሲደጋግሙ ይቆያሉ። ነገሮችን የሚያስረፍድ፣ መከናወን ያለበትን የሚያቆይ፣ ስነፍ፣ ከስራ የሚደበቅ ሁሉ መገለጫችን ይሆናሉ። ይህ ችግር ውስጣችንን እየበላ በህይወታችን ማሳካት ከሚገቡን ነገሮች አርቆ ያስቀምጠናል። ይህ ልማድ እድሜዎን እስኪጨርስ አይጠብቁ። በዚህ ጽሁፍ ሰዎች ከዚህ ልማዳቸው የወጡባቸውን መንገዶች እናያለን።

1) ስራዎን በትንንሹ ይከፋፍሉ

ነገሮችን ይምናዘገይበት አንዱ ምክንያት ጉዳዩን ለመፈጸም በጣም ከባድ መስሎ ስለሚታየን ነው። በዚህ ግዜ የመጀምርያው ክንውናችን መሆን ያለበት ስራውን በትንሹ መከፋፈል ነው። ከዛም በአንድ ግዜ አንዱን ብቻ መፈጸም ነው ያለብን። አሁንም እራስዎ ሲሰንፍ ካገኙት የሰሩትን ክፍፍል ይበልጥ ያስፉት። ስራዎቹ በጣም ሲያንሱ ለራስዎ “ኢች ብቻ ናት የቀረችኝ” ብለው ማሰብ ይጀምራሉ።

2) በአካባቢዎ ያለውን ነገር ይቀይሩ

የተለያዩ ቦታ እና ሁኔታዎች በምርታማነትዎ ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ። የስራ ገበታዎን እና ክፍልዎን አጢነው ይመልከቱ። ስራ እንዲሰሩ ይገፋፍዎታል ወይስ ጠቅልለው ተኙ ነው የሚሉዎት? ለስራ ካልጋበዘዎት የስራ አካባቢዎን መቀየር ይረዳዎታል። ከዚህ በፊት ይመችዎት የነበረው የስራ ገበታ ከግዜ በኋላ ሊሰለችዎት ስለሚችል ቢሮዎትን መለዋወጥ ይረዳዎታል።

3) ምን መቼ ማለቅ እንዳለበት እቅድ ያውጡ

አንድ ዴድላይን ለሟሟላት መጣር ለእራስዎ የስንፍና ፈቃድ የመስጠት ያህል ነው። ምክንያቱም ግዜ ያለን ይመስለንና ግዜውን ዝም ብሎ ለማሳለፍ ምክንያት ይሆነናል። መስራት ያለብዎትን ፕሮጀክት ከከፋፈሉ በኋላ ለእያንዳንዱ ዴድላይን ያዘጋጁ። ግዜ አከፋፈልዎን አጢነው ያውጡ። አንዱን አለማሳካት ማለት የሌላኛውን እቅድ የሚያስተጓጉል እንዲሆን አድርገው። የዛኔ የግዜ ግምትዎ ስራዎ ከሚያስፈልገው ግዜ ጋር እንዲጣጣም አደረጉ ማለት ነው። በፍጥነት ስራ እንዲጀምሩ ይረዳዎታል። ከቻሉ ወርሃዊ፣ ሳምንታዊ እና ቀናዊ የስራ ክፍፍል አውጥተው ቢቀንሳቀሱ ይበልጥ ይረዳዎታል።

4) የስንፍና ማቆሚያዎችዎን ያጥፉ

ስንፍና ከተጠናወትዎት አንዱ ምክንያት ለመስነፍ ስለቀለልዎት ነው። ስልክዎ ላይ የሚያዘናጉ አፕሊኬሽኖች ካሉ አጥፏቸው። በተደጋጋሚ የሚያዩት ቪድዩ ካለ ጨክነው አጥፉት። ቻት ማድረግ ከሆነ ችግርዎ መልእክት በደረስዎት ቁጥር እንዳይጮህ አድርጉ። በአካባቢዎ ያሉ መዘናጊያዎችን ያስወግዱ። የማህበራዊ ሚድያ የሚከፍቱበት የተወሰነ ሰአት አዘጋጁ። ከዛ ሰአት ውጪ አይክፈቱ።

5) ስራ እንዲሰሩ ከሚገፋፉ ሰዎች ጋር ለመዋል ሞክሩ

ለ10 ደቂቃ ብቻ ቢል ጌትስ ወይም ኢለን መስክን ቢያነጋግሩ የስራ መነቃቃትዎ ይጨምራል። አብረናቸው ግዜ የምናሳልፋቸው ሰዎች ባህሪያችን ላይ ተጽእኖ አላቸው። እነ ቢል ጌትስን አግኝቶ ማውራት የሚቻል ባይሆንም በአቅራቢያችን ለስራ ከፍተኛ መነቃቃት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ። ከነሱ ጋር አብሮ መዋል የነሱን ባህሪ እንድንላበስ ይረዳናል።

6) እቅድ ያለው ጓደኛ ይኑርዎ

የራሱ እቅድ ያለው ጓደኛ ቢኖርዎ እቅዳችሁን ለማሳካት ሁለታችሁም ትተጋገዛላቹህ። አንዱ ሲሰንፍ ሌላኛው በመናገር እንዲቆጣጠር በማድረግ ሁለታችሁም እቅዳችሁን ለማሳካት አብራቹህ ትጥራላቹ። ሁለታችሁም ተመሳሳይ እቅድ ሊኖራቹህ አይገባም። ተመሳሳይ ቢሆን ይበልጥ ልትረዳዱ ትችላላቹህ። ከስህተቶቻችሁ ይበልጥ ትማራላቹ። ባይሆንም ግን በየግዜው ስለ አላማዎ እና ስራዎ በግልጽ የሚያወሩት ሰው ማግኘት በጣም ጠቃሚ ነው።

7) ስለ እቅድዎ ለሌላ ሰው ይንገሩ

ስለ እቅድዎ ለሚያቁት ሰው ሁሉ መናገር ተጠያቂነት ስሜት ያሳድርብዎታል። የቅርብ ዘመዶች እና ጓደኛዎች “እንዴት ሆነልህ/ሽ” ብለው መጠየቃቸው ስለማይቀር ላለመሸማቀቅ ሲሉም ቢሆን የተወሰነ ክንውን ለመፈጸም ይበረታታሉ። በፌስቡክ ገጽዎ ላይ ስለ እቅድዎ ለጓደኞችዎ በሙሉ መግለጽ እቅድዎን ለማከናዎን ይበልጥ ይገፋዎታል።

8) እቅድዎን ያሳካ ሰው ፈልጉ

ምንድን ነው ማሳካት የሚፈልጉት? እሱን ያሳኩ ሰዎች እነማን ናችው? ፈልገው ያግኟቸው። ግንኙነት ይፍጠሩ። የእቅድዎን ስኬት ፍሬ የሚያጣጥሙ ሰዎች ማወቅ ለራስዎ ከፍተኛ መነቃቃት ይሰጥዎታል።

9) እቅድዎን በየግዜው ያሻሽሉ

አንዳንድ ግዜ የስንፍና መንሻው እቅድ ሲያወጡ የፈጠሩት ስህተት ነው። እቅድዎን ለማሳካት መፈጸም አለብኝ ብለው ያስቀመጡት ክንውን እቅድዎን ለማሳካት ላይረዳዎት ይችላል። እሱን ሲረዱ ክንውኑን ለመቀየር እንዳይፈሩ። የመጨረሻ እቅድዎን በተለያየ ምክንያት መቀየር ከፈለጉ ግዜ ሰተው ያስቡ። ከግዜ በኋላ በሃሳብዎ ከጸኑ እንዲሁም ለእቅድዎ መቀየር አሳማኝ ምክንያት ካለዎት በፍጥነት ቀይረው አዲሱን እቅድ ለማሳካት በፍጥነት ይንቀሳቀሱ። አዲሱ እቅድዎን ለማሳካት የሚያስፈልግዎትን ክንውኖች አውጥተው ይንቀሳቀሱ።

10) ነገሮችን አያወሳስቡ

እቅድዎን ለማሳካት ትክክለኛውን ግዜ እየጠበቁ ነው? በዚህም በዛም ምክንያት ጥሩ ግዜ አይደለም ብለው ያስባሉ? ከሆነ ይህንን ሃሳብ በፍጥነት ይጣሉ። ሁሌም ወደ እቅድዎ ላለማምራት የሆነ ምክንያት ይኖራል። ትክክለኛው ግዜ እስኪመጣ ብለው የሚጠብቁ ከሆነ እቅድዎን መቼም አያሳኩትም። አንድን ነገር ችግር በሌለበት ግዜ እፈጽማለሁ ብሎ ማሰብ እንዲሁም የምፈጽመው ነገር ችግር ሊኖረው አይገባም ብሎ ማሰብ ቀንደኛ ላለመጀመር ይምንጠቀምባቸው ምክንያቶች ናቸው።

11) ዝም ብለው ያከናውኑት

መጨረሻ ላይ ዝም ብለው መስራት ያስፈልግዎታል። ምንም ያህል እቅድ ቢያወጡ፣ ቢያስቡ፣ ቢያወጡ ቢያወርዱ ከስራው ይሚታደግዎ ነገር የለም። ምንም ክንውን ማፈጸም ካልጀመሩ ወደ እቅድዎ አንድ እርምጃም አይንቀሳቀሱም። ምንም አይፈጠርም። ሁሌ ሰዎች በሁኔታቸው ይማረራሉ። ግን በዛውም ልክ ምንም ወደ እቅዳቸው የሚወስዳቸው ስራ ሲሰሩ አይታዩም። በስንፍና ወደ ስኬት መሄድ እንደማይቻል ህይወት ትነግረናለች። ምንም ሆነ ምን መፈጸም ይሚፈልጉት ነገር ተነስቶ ማድረግ መጀመር ነው።


799 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean