top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም" (በእሙ ኢሳን)

Updated: Aug 25, 2019"ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም"

ድሮ ድሮ አበው ሲተርቱ ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም ይሉ ነበር ። እንደ እኔ…እንደ እኔ የተቀሩትን ጣቶች ከሚያበላሽ የገማው ጣት ይቆረጥ ባይ ነኝ።

ውድ ወገኖቼ አንዱ ጣት ተቆርጦ የተቀሩት ጣቶች ሰላም የሚሆኑ ከሆነ ያ… የገማው ጣት ይቆረጥ። ምናልባት የአንዱ ጣት መቆረጥ የእጁን የእለት ተዕለት ተግባር ላያውከው ይችላል። ነገር ግን የአንዱ ጣት መጉደል ሌሎቹ ሙሉ ጣት እንዳይባሉ ያደርጋቸው ይሆናል። የእኔ ስጋት ግን የአንዱ ጣት መቆረጥ ሳይሆን ሄዶ ሄዶ ጣቶቹን የያዘው ግንድ ማለትም እጁን እንዳይገዘግዘው ስጋት አለኝ። የእኛም ሃገር ሁኔታ እንደዚሁ ነው። ግንዱ ኢትዮጵያ ሃገራችን ስትሆን ጣቶቹ ደግሞ በብሔር ብሔረሰቦች ይመሰላለሉ።

ዛሬ ዛሬ በዘር ተከፋፍለን አንድ ለአንዱ ጌጥ መሆን ሲገባው የጠላትነት መንፈስ በመላው ሃገራችን ተንሰራፍቶ ይገኛል።

ውድ ወገኖቼ ሆይ፡-

በዘርስ ለመከፋፋል የተሻለው ዘር የምንለው የቱ ነው?

ያንዱንስ ዘር የሚወክለው የትኛው ነው?

የተሻለው ዘርስ የቱ ነው?

ምርጥ ዘር ለመባል መስፈርቱ ምንድን ነው? ወይስ እናውቅልሃለን ባዮቹ አንተ በህዝብ ቁጥር ስለምትበዛ አንተ ነህ። አንተኛው ደግሞ ምንትስ ስለሆንክ ምርጥ ዘር ነህ እያሉ ስለሚሰብኩ ነውን? ውድ ኢትዮጵያን ወገኖቼ የሰው ልጅ የዘር ጉዳይ ልክ ስንዴ ዘርቶ ስንዴ እንደማብቀል አይደለም። ምክንያቱም ደግሞ ለምሳሌ ብንወስድ እናቱ አማራ፣ አባቱ ጉራጌ፣ አያቱ ትግሬ፣ አያቱ ደግሞ ኦሮሞ እያለ…እያለ ያለተበረዘ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላምንም። ውድ ዘመዶቼ ይህ የሁላችንም ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ቢያስ ከአንዱ ወይም ከሁለቱ ተቀይጠናል። በተጨማሪም በዘር ባይገናኝም እንኳን በሚኖርበት አካባቢ አንዱ የሌላውን ብሔር ቋንቋ እና ባህል ፈቅዶና ለምዶ የእኔ ነው ብሎ እየኖረበት ይገኛል። ስለዚህ ወደድንም ጠላን አንዳችን ካንዳችን ተዋልደናል ወይም ተጋብተናል። እንዲሁም ቋንቋውና ባህሉን ተዋህደናል። ስለዚህ እነዚያ… እናውቅልሃልን የሚሉንን የባለጊዜዎች እኩይ ውትወታቸውን ችላ ብለን እንደዚሁም ተዘፍቀንበት ካለው ከመናናቅና ከመጎሻሸም እራሳችንን አርቀን አንዳችን ላንዳች ተገን በመሆን በልዩነታችን አንዱ ላንዱ ጌጥ ሆኖ ቢኖር የተሻለ ነው እላለሁ።

አንዳንዴ እነዚያ በቀቀኖች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ይሉና የዋሁን ህዝብ በኖህ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውሃ የታደጉት ይመስል “የዛሬ አመት እንደዚህ ነበር… እኛ ባንመጣ ኖሮ” ሲሉ ይደመጣሉ። በነገራችን ላይ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ረሃብ፣ ችግርና ስደት ወይም ሰው ሰራሹ ሞት አዲስ አይደለም።

በስልሳዎቹ፣ በሰባዎቹ እንዲሁም በሰማንያዎቹ ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ልጁን ያለገበረ ኢትዮጵያዊ አይገኝም። ዛሬ…ዛሬ ለውጡ ሲመጣ ሁላችንም ካለንበት ሆነን ትዕይንቱን ለማየት በእጅጉ ጓግተን የነበረ ሲሆን ሲውል ሲያድር ግን ጸሐይዋ እየደበዘዘች ደመናው ሲጋርዳት ይስተዋላል።

ምንም እንኳን የ27 ዓመት ጥመት በ27 ቀን እንዲቃና ባንጠብቅም ከድጡ ወደማጡ እንዳይሆን በዘር የሚሰበከውን ፖለቲካ አቁመን የተሻለችን አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተጋረደ ያለውን ዳመና ገላልጦ የለውጥ ብርሃኑ ለሁሉም በእኩል እንዲደርስ ካላደረግን ያው እንደ ተለመደው “እዛው ፈላ እዛው ሞላ” ይሆናል። ስለዚህ የቀኑ ባለቤቶቹ… እነዚያ እናውቅልሃለን ባዮቹ በተቻለ ፍጥነት ብዥታውን አጥፍተው የብርሃኑን ፍካት ካላሳዩን አያያዙ ታይቶ ጭብጦው እንዳይቀማ እሰጋለሁ።

እሙ - ኢሳን

ከሪያድ ሳውዲ አረቢያ


38 views0 comments
bottom of page