top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ማኅበራዊ ፍርሃት (በአሸናፊ ካሳሁን)

Updated: Jun 9, 2019


ፍርሃት

ማኅበራዊ ፍርሃት ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ለመናገር ወይም አንድን ድርጊት ለመፈጸም በተዳጋጋሚ የሚፈጠር በብዙ ግለሰቦች ላይ የሚስተዋል ምክኒያታዊ ያልሆነ ፍርሃት ነው፡፡ ይህ የጭንቀት ዓይነት ያለባቸው ግለሰቦች ብዙ ጊዜ ንግግር ያለበት ተግባር አጥብቀው ይሸሻሉ ምክኒያቱም አይደለም ንግግር አድርገው ገና ለማድረግ ሲያስቡ የሚሰማቸው የፍርሃት ወይም የጭንቀት ስሜት ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ፡፡ ከህጻናት በስተቀር ማኅበራዊ ፍርሃት ያለባቸው ሰዎች ፍርሃታቸው ምክኒያታዊ እንዳልሆነ ይረዳሉ ምንም እንኳን ይህ ከፈርሃታቸው ባይታደጋቸውም፡፡


ከታች የተዘረዘሩት የማኅበራዊ ፍርሃት ተጠቂዎች ላይ የሚስተዋሉ ተደጋጋሚ ምልክቶች ናቸው፡-

  1. ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ንግግር ለማድረግ አጥብቆ መፍራት

  2. አዲስ ሰው ጋር ለመገናኘት ተደጋጋሞ የሚከሰት ፍርሃት

  3. ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ንግግር ለማድረግ በሚያስቡበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ይተቹኛል ብሎ ማሰብ

  4. ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ንግግር ሲያደርጉ በላብ በጠመቅ ወይም ልዋረድ እችላለሁ ብሎ በፍርሃት ማሰብ

  5. ብዙ ሰው ባለበበት ቦታ ንግግር ለማድረግ የሆነ ያልሆነ ምክኒያት በመደርደር እራስን ማቀብ

  6. እንደ ካፌ፣ ሬስቶራንት፣ ቤተ-መጻሕፍትና ሌሌች ብዙ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሰዎች እኔን እየተመለከቱኝ ነው ብሎ መሳቀቅ

  7. ብዙ ሰው ባለበት ቦታ ምግብ በሚመገቡት ጊዜ ትንታ ወይም መታነቅ እንዲሁም ምግቡ ሊዝረከርክብኝ ይችላል ብሎ መፍራት

  8. ከእነዚህ ጋር ተዛምዶ የሚከሰት እንደ የልብ ምት መጨመር፣ ላብ ላብ ማለት፣ የሰውነት መንቀጥቀጥና የመሳሰሉት ፍርሃት ወለድ አካላዊ ለውጦች ናቸው፡፡

መፍትሄ

  1. ጡንቻን ማዝናናት መለማመድ፡- ከውስጥ ከሆድ መተንፈስ በመለማመድ ጭንቀቱ የሚፈጥረውን የረብሻ ስሜት መቀነስ፡፡ ይህ በጣም ቀላልና የትም ቦታ ሊለማመዱት የሚችሉት ዘዴ ነው፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ (እስከ 10 ሴኮንድ) ወደ ውስጥ በመተንፈስ ትንፋሽህን መያዝ ከዚያም መልቀቅ፡፡ እንደገና ወደ ውስጥ ትንፋሽን በመያዝ አሁንም ወደ ውጪ መተንፈስ፡፡በተደጋጋሚ ይህን በማድረግ የጭንቀት ስሜቱን ማቅለል ይቻላል፡፡ ይህን ዘዴ ጭንቀቱ ቀለል እሰከሚልድረስ መከወን ይቻላል፡፡ ይህን ዘዴ በተግባር ካውንስሊግ በሰራሁባቸው ግዜያት ከደንበኞቼ ጋር የሞከርኩት ሲሆን እጅግ በጣም ውጤታማ ነው፡፡

  2. የአስተሳሰብ ለውጥ፡- ብዙ ጊዜ ማኅበራዊ ፍርሃት እንዲከሰት የሚያደርጉ ከበስተጀርባ ያሉ አሉታዊ አመለካከቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ለራስ የሚሰጥ ዝቅተኛ ግምት አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ፍርሃት መከሰት አስተዋጽኦ የሚያበረከቱ ምክኒያታዊ ያልሆኑ አሉታዊ አስተሳሰቦችን ነቅሶ በመለየትና በአዎንታዊ አመለካከት መተካት፡፡

  3. መለማመድ፡- ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ መናገር ስለሚያስፈራን ንግግር የምንሸሽ ከሆነ የፍርሃቱ መጠን እንዲጨምር መፍቀድ ነው፡፡ ከሸሻችሁት በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው መቼም ቢሆን ከዚህ ችግር እንደማትገላገሉ ነው፡፡ ስለዚህ እራስን ቀስ በቀስ ማለማመድ ዋነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ለምሳሌ ለተማሪዎች የምታቀርቡት ንግግር/Presentation ካለ፣ መጀመሪያ ብቻችሁን ማንም በሌለበት ነገር ግን ብዙ ሰው ክፍሉ ውስጥ እንዳለ በምናብ በማሰብ ማቅረብ፡፡ ከዚያም የተወሰነ ሰው በተለይም የምናውቃቸው ጓደኞች ወይም የቤተሰብ አባላት ፊት ለፊት ማቅረብ፡፡ በመጨረሻም ዋናውን ንግግር ማቅረብ ነው፡፡ ይህ የስራ ቅጥር ቃለ መጠይቅና ሌሌች ሁኔታዎች ላይም ያገለግላል፡፡

  4. ስራ ላይ ማተኮር፡- ብዙ ጊዜ የማኅበራዊ ፍርሃት ተጠቂዎች ከሚሰሩት ስራ ይልቅ ሌሎች ሰዎች ስለሚሰጧቸው አስተያየትና ምላሽ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ከስራው ይልቅ አድማጭ ተመልካች ላይ የምናተኩር ከሆነ መጀመሪያ በተገቢው ስራን መስራት እንችልም ምክኒያቱም ቀልባችን ሌሌች ሰዎች ላይ ነውና፡፡ ሲቀጥ ልሌሎች ሰዎች ላይ ስናተኩር የበለጠ ስለፍርሃት ስሜታችን ላይ እንድናተኩርና የበለጠ አሉታዊ ሃሳቦች እንዲፈጠሩ ይገፋፋል፡፡

  5. የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና መውስድ፡- እንደ ዓይንን እየተመለከቱ ማውራት፣ ፈገግታ፣ የንግግር ፍሰትን መጠበቅና የመሰሳሰሉት ልምምዶች በንግግርና በሌሎች ማህበራዊ ተግባቦት ላይ ውጤታማነታችንን ሲለሚጨምሩ ለወደፊት የበለጠ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ መናገርና ሌሌች ተግባሮችን ለመፈጸም አወንታዊ ማበረታቻዎች ናቸው፡፡

የሰው ልጅና ስሜት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንደመሆናቸው፣ በፍርሃት ስሜት ወይም በጭንቀት የሞተ ማንም የለም፡፡ ነገር ግን የዕለት ተዕለት ህይዎታችን በደስታ እንዳንመራ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማኅበራዊ ፍርሃትም እንደዚሁ በህይወታችን ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽኖ ይኖራል፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ማፈላለግ አንድ ነገር ሲሆን ለምን ይህ ተከሰተብኝ ብሎ እራስን መኮነንና ጥፋተኛ ማድረግ አይገባም ምክኒያቱም ምንጩ ከዘር እስከ አስተዳዳግ ሁኔታ እንዲሁም መጥፎ የህይወት አጋጣሚ ብዙ ስለሆነ፡፡ ሰላም!

(በአሸናፊ ካሳሁን)

35 views0 comments
bottom of page