top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ፈገግታ

Updated: Jun 9, 2019


ፈገግታ

“ከእንስራ ሙሉ ሀሞት ይልቅ አንዲት ጠብታ ማር ንቦችን ትስባለች”

ዴል ካርኔጊ

አንድ ሁለት ብለን ቆጥረን የማንጨርሳቸው “በእጅ የያዙት ወርቅ” የሆኑብን የግልም የጋራም ሀብት አሉ፤ በእኛም ሆነ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ለውጥ መፍጠር የሚችሉ ወርቆች፡፡ ዋጋቸውን ከአለመረዳት አንዳንዴ ግድየለሽ በመሆንም እነዚህን ወርቆች መዳብ አስመስለናቸዋል፡፡ ፈገግታ አንዱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከቤት አባወራዎች ጀምሮ እስከ ሀገር መሪዎች ድረስ በፈገግታ ድርቅ ተመትተናል፡፡ ኮስተር ማለት፣ ፊት መንሳት እንደውም የወንድነት፣ የጀግንነት፣ የጎበዝነት መገለጫም ነው፡፡ ኮስታራ ጀግና እና ፊቱ የማይፈታ መሪ ብቻ ነው ያለን፡፡ “ወንድ ልጅ ኮስተር ነው ማለት ያለበት” ሁሉ ይባላል፡፡ መሳቅ፣ መጫወት፣ ፈገግ ማለትን ከድካም ጋር አስተሳስረነዋል፡፡ የሚቀልድ ሰው ቁምነገረኛ መሆን የሚችል አይመስለንም፡፡

ጉዳይ ለማስፈፀም በየቢሮው ስንገባ “የእግዜር ሰላምታ” እንኳ በቅጡ አናቀርብም፡፡ አስተናጋጆቹም በበኩላቸው ፊታቸው ሳይፈታ ያስተናግዱናል፡፡ ኮስትር ብለን የቤት ሰራተኞቻችን እናዛለን ኮስትር ብለው በግዴታ ስሜት ብቻ ስራቸውን ይወጣሉ፡፡ ፊትን በማኮሳተር ብቻ ብዙ ማከናወን የምንችል ይመስለናል፡፡ እውነታው ግን ተቃራኒ ነው፡፡ ፊትን በመፍታት እንጂ ፊትን በማኮሳተር ማንም ጥሩ መሪ፣ ጥሩ አስተናጋጅ፣ ጥሩ ባለሀብት፣ ጥሩ ባል፣ ጥሩ ልጅ፣ ጥሩ መምህር፣ ጥሩ ሾፌር ሊሆን አይችልም፡፡ ዴል ካርኔጊ “ከእንስራ ሙሉ ሀሞት ይልቅ አንዲት ጠብታ ማር ንቦችን ትስባለች” ይላል፡፡ ከሚኮሳተሩ ይልቅ በፈገግት የሚደምቁ ገፆች ሰው ይስባሉ፡፡ ግንባራቸው ከማይፈታ ይልቅ ፈገግታ የማይለያቸው መሪዎች በህዝብ ዘንድ ይወደዳሉ፡፡

የፈገግታ መልእክቱ “እውድሻለሁ/እወድሀለሁ”፣ “አንተ/ አንቺ በሕይወቴ ውስጥ ቦታ አለሽ/አለህ”፣ “ለእኔ ልዩ ነህ/ነሽ”፣ “ስላየሁህ ደስ ብሎኛል”፣ “አከብርሀለሁ” ወዘተ ነው፡፡ ኮስታራ ገፅታ በአንፃሩ የዚህን ተቃራኒ መልእክት ያስተላልፋል፡፡ “ጥፋ ከዚህ”፣ “አሁንስ አንተን የማላይበት የት ልሂድ?”፣ “ደሞ መጣ” ወዘተ ዓይነት፡፡ በዚህ አስተሳሰብ የተቃኙ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ምን ያህል የምቾት ማጣት እና ህመም ምንጭ እንደሚሆኑ መገመት ቀላል ነው፡፡

ፈገግታ የተዘጋ የልብን በር የሚከፍት ቁልፍ ነው፡፡ ሁላችሁም እስኪ ዘወትር ፊታቸው እንደ ተቋጠረ ውሎ እንደ ተቋጠረ የሚያድር ሰዎችን በአእምሮአችሁ አስቡ፡፡ ምን ያህል ከእነዚህ ሰዎች ጋር መስራት ትፈልጋላችሁ? እነዚህ ሰዎች የብዙዎቻችን ቀዳሚ ምርጫ መሆን እንደማይችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ጥሩ ሰው ሁሉ ሊሆኑ ይችላል፡፡ ምንም እንኳ ውስጣቸው ቅን ቢሆንም የማይፈታው ፊታቸው ግን “አትድረሱብኝ” የሚል መልዕክት ስለሚያስተላልፍ እነዚህ ሰዎች በተቻለ መጠን ለመቅረብ ሳይሆን በተቻለ መጠን ለመራቅ እንሞክራለን፡፡

ፈገግታ የሀብት ምንጭ ነው፡፡ በቅጡ ፈገግ ማለት የሚችሉ አስተናጋጆች ፊታቸው ከማይፈታ አስተናጋጆች የበለጠ “ቲፕ” ያገኛሉ፡፡ ዩኒቨርስቲ ሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ አንድ ፎቶ ኮፒ ያደርግልን የነበረ ልጅ አስታውሳለሁ፡፡ ሁልጊዜ ፊቱ በፈገግታ የተሞላ ነው፡፡ አንድም ቀን እንኳ አዝኖ የሚያውቅ አይመስላችሁም፡፡ እሱ ባይኖር እንኳ እስኪመጣ ጠብቀን ኮፒ እናደርጋለን፡፡ ሌላ የሚያስተናግድ ሰው ጠፍቶ አይደለም፤ ሌሎች ኮፒ ቤቶችም ሞልተዋል፡፡ ብዙ ኮፒ ቤቶች ቢኖሩም ከፈገግታ ጋር የሚያስተናግዱት ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ፈገግታ ገበያ ያደራል፡፡ ይህንን ቅርብ ጊዜ አግኝቼው ሌላ ሰው መስሏል፡፡ ቻይና እየተመላለሰ እንደሚነግድ አጫወተኝ፡፡ መኪና ይዟል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ በብዙ መልኩ ተቀይሯል፡፡ አሁንም ግን ያልተቀየረው የፊቱ ፈገግታ ነው፡፡

ሌላ ማሳያ አሁንም ማንሳት እንችላለን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጉዳይ በማስፈፀም ረገድ የሚስተካከላቸው የለም፡፡ ሰው ስለሚያውቁ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ ሁለት እንደዚህ አይነት ሰዎችን እኔ በግሌ አውቃለሁ፡፡ በቃ እነሱ ጠይቀው ማንም “አይቻልም” አይልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ታዲያ “ግንባር አለው/አላት”፣ ባስ ሲል ደግሞ “የሆነ ነገር አለው/አላት” ማለት የተለመደ ነው፡፡ ግንባር የሌለው ማን አለ? ሁላችንም ግንባር አለን፡፡ አንድ አንዶቻችን እንደውም በሰው መስፈሪያ በጣም ውብ ግንባር ሁሉ ሊኖረን ይችላል፡፡ ሁላችንም የሌለን ፈገግታ ነው፡፡ እነዚህ “ድንጋይ ዳቦ ነው” ብለው ማሳመን የሚችሉ፣ እንደው የሚያገኛቸው ሰው በሙሉ ቀና ቀና መልስ የሚመልስላቸው ሰዎች አንዱ ትልቁ የጋራ መለያቸው ፈገግታቸው ነው፡፡ “አይሆንም ብያለሁ አይሆንም” ብሎ የዘጋውን “ፋይል” በፈገግታ ቁልፍ ይከፍቱታል፡፡ እርግጥ ነው “ቁልፉ ፈገግታ ብቻ ነው” እያልኩ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ዋና ቁልፍ ፈገግት ነው፡፡

ፈገግታ፣ ደስታ እና አንጎል

ደስታየፈገግታምንጭነው፡፡በአንፃሩፈገግታም የደስታ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ፈገግታ አንጎላችን ውስጥ የሚገኙ “ኒውሮኖችን” ስለሚያነቃቃ እና ደስታችንን እና ጤናችንን ለማሻሻል ይረዳል፡፡ ፈገግታ “Neuropeptides” የሚባሉ ጥቃቅን ሞሎኪውሎች አንጎላችን ውስጥ እንዲለቀቁ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ሞሎኪውሎች በሌላ በኩል አንጎል ውስጥ የሚገኙ “ኒውሮኖች” በሚገባ መልካም ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ ውጥረትን (Stress) ይቀንሳል፡፡ “Neuropeptide” ስንደሰት፣ ስንከፋ፣ ስንናደድ ወዘተ መልእክት ከአንጎላችን ወደ አካላችን ያስተላልፋሉ፡፡ ውስጣችን አስደሳች ስሜት የሚያቀጣጥሉት ዶፓሚን፣ ኢንዶርፊን፣ ሴሮቶኒን ወዘተ የሚባሉ “ኔውሮትራንስሚተርስ” ፈገግታ ፊታችንን በሚያጥለቀልቅበት ወቅት በብዛት ይመነጫሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሰውነታችን ዘና ይላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የልብ ምታችን እና የደም ግፊታችን የተረጋጋ እና የተስተካከለ ይሆናል፡፡

“ኢንዶርፊን” የሚባሉት “ኔውሮትራንስሚተሮች” በበኩላቸው የህመም ማስታገሻናቸው፡፡ ህመም ሲያጋጥመን የምንውጣቸውየህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳታቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ፈገግታ የሚያመነጨው “ኢንዶርፊን” በሌላ በኩል ግን ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሮአዊ የሆነ የህመም ማስታገሻ ነው፡፡ ታማሚዎችሰው አጠገባቸው ሆኖ ሲያጫውታቸው፣ ፈገግ ሲሉ፣ ሲስቁ “አይ ደህና ነህ እኮ! ያመመህ አትመስልም እንደውም”ብለን የምናውቅበት ጊዜ ሁሉ ይኖራል፡፡

ፈገግታ የሚያመነጨው ሌላኛው “ኒውሮትራንስሚተር” “ሴሮቶኒን” ፍቱን የድብርት መድኃኒት ነው፡፡ የመድኃኒት ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸው “Anti-depressants” አንጎላችን ውስጥ ገብተው የሴሮቶኒንን መጠን ነው ከፍ የሚያደርጉት፡፡ ፈገግታ በአንፃሩ ያለ ምንም የጎንዮሽ ጉዳት እና የሀኪም ትዕዛዝ የድብርት ሰሜትን ከውስጥ ጠራርጎ ያስወጣል፡፡

ፈገግታ እና አካላችን

ፈገግታ ውበትን ይጨምራል፡፡ ፎቶ አንሺዎች “ትንሽ ፈገግጋ… ትንሽ… አዎ…እንደሱ” ያላሉት ማን አለ?የፈገግታን ምስጢር ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡ ፈገግታ ፊታችሁ ላይ ሲታይ ሰዎች በጥሩሁኔታ ያስተናግዷችኋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት ዋና ምክንያት የጥናት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት “ፈገግ በምንልበት ወቅት ሰዎች ማራኪ፣ እምነት የሚጣልበት፣ ዘና ማለት የሚችል እና ቅን ሰው ነው/ናት” ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም ስኮትላንድ አበርደን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከፈገግታ ጋር የተያያዘ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች ለፈገግታ እና ውበት ደረጃ ያወጡ ሲሆን ብዙዎቹ ዓይን ዓይንን (Eye Contact) የሚያዩ እና ፈገግታ የሚሉ ሰዎች ሰዎች የተሻለ ማራኪ እንደሆኑ ተናግረው ነበር፡፡

ፈገግታ እና አከባቢያችን

ፈገግታ ተላላፊ ስሜት መሆኑን ቀደም ሲል ገልፀናል፡፡ ስዊድን ውስጥ በተካሄደ ሌላ ጥናት አጥኚዎች የተወሰኑ ሰዎችን ሰብስበው ፈገግ ያለ፣ የተቆጣ፣ የፈራ እና የተኮሳተረ ሰው ፊት ስዕል አሳይተዋቸው ነበር፡፡ ፈገግ ያሉ ሰዎችን ስዕል እየተመለከቱ ኮስተር ለማለት ተቸግረው ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚጠቁመው ፈገግ ያለ ፊትን እየተመለከቱ ኮስተር ማለት ከባድ ነው፡፡ ፈገግታ ስንመለከት እኛም መልሰን ፈገግ እንድንል የሚያደርግ የአንጎላችን ክፍል አለ፡፡ ፈገግታ የእኛን ብቻ ሳይሆን የሌሎችን የተናደዱ፣ ያዘኑ፣ ሰዎችን ስሜት ይቀይራል፡፡ ልጅ ያላችሁ መቼም ይህ አጋጥሟችሁ ይሆናል፡፡ አንድ በንዴት የሚያጦፍ ስራ ልጃችሁ ይሰራና “ቆይ ባልሰራለትን” ዝታችሁ፣ ከአሁን አሁን መጣ እያላችሁ ትጠባበቁና ቤት ሲገባ ያንን አንጀት የሚባላ ፈገግታ ወይም ሳቁን ያሳያችኋል፡፡ እሳት የነበረው ስሜታችሁ በአንድ ጊዜ ቀዝቅዞ ውሀ ይሆናል፡፡ ከዛ ያ ሁሉ ዛቻ ይረሳና “ለምን እንደዚህ አደረክ አቡሽዬ” የሚል ለስላሳ የፍቅር ቃል ከአንደበታችሁ ይወጣል፡፡

ፈገግት እንግዲህ እነዚህ እና ከእነዚህም ውጪ ሌሎች ብዙ ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡ እኛንም ሆነ በዙሪያችን የሚገኙ ሰዎችን ያስደስታል፡፡ በመሆኑም ትንሽ ትልቅ ወዘተ የሚል ከፋፋይ ሀሳብ ውስጥ ሳንገባ ፈገግታችንን ለራሳችንም ለሰዎችም እንለግስ የዛሬው መልእክቴ ነው፡፡

ቸር እንሰንብት!

(በነጋሽ አበበ©ዘ-ሳይኮሎጂስት)


82 views0 comments
bottom of page