• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሚያሳስበን ችግሩ ሳይሆን ችግሩን የምናይበት መንገድ ቢሆንስ? (በሚስጥረ አደራው)

Updated: Jun 9, 2019የሚያሳስበን ችግሩ ሳይሆን ችግሩን የምናይበት መንገድ ቢሆንስ?

ምንም እንኳን ስለመልካም አስተሳሰብ እና ስለ ቀና ኑሮ ደጋግመን ብንደሰኩርም አንድ መዋጥ ያለብን እውነት ግን አለ። ይህም ህይወት ነጭ እና ጥቁር አይደለችም። የጠበቅናቸው የማይከሰቱባት ያልጠበቅናቸው የሚከሰቱባት የማትተነበይ እንጂ። ችግር የማይደርስበት ኑሮ፤ ከመከራ ከሃዘን የራቀ ህይወት ለማንም አልተሰጠም። ማንም ሰው ሁሉ ተሳክቶለት እና ሞልቶለት የሚኖር አይኖርም (ምንም እንኳን ከላይ በምናያቸው ነገሮች ሁሉ ነገር የተሳካላቸው ሰዎች ያሉ ቢመስሉንም)። አነሰም በዛ እያንዳችን የምናምርርባቸው ነገሮች በህይወታችን ውስጥ አሉ።

ኤካርት ቶሌ የተባለ ጸሃፊ፤መማረር ማለት ያለውን እውነታ መቀበል አለመቻል ነው ይላል። የምናማርረው ኑሮዋችን እኛ በፈለግነው መንገድ ስላልሄደ አልያም እንዲከሰቱ የማንፈልጋቸው ነገሮች ስለተከሰቱ ነው። እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ እራሳችንን የምናወጣባቸው መፍትሄዎች አሉ። ለዚህች አጭር ጽሁፍ “The power of Now” ከተሰኘው መጻህፉ ላይ ያገኘኋቸውን ሶስት ነጥቦች ሰፋ አድርጌ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ።

1-) Remove yourself from the situation– አንዳንዴ ችግር ብለን የምንወስዳቸው ወይም የምጨነቅባቸው ነገሮች ከኛ ውጪ በሆኑ ነገሮች የሚከሰቱ ናቸው ። የሰው ልጅ ደግሞ እራሱን ከመለውጥ ባለፈ የሌላውን ሰው አስተሳሰብ እና ማንነት ለመለወጥ አይቻለውም። ስለዚህ የምንማረርባቸው ነገሮች ከኛ የመነጩ ካልሆኑ ፤ከሁኔታው አልያም ከአካባቢው እራሳችንን በማራቅ ሰላማችንን ማግኘት እንችላለን። በዙሪያችን ያሉ ነገሮች የሚያደርሱብንን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባንችልም፤ ሁኔታዎቹ ግን ሰላም እና ደስታችንን እንዳያናውጡ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።

2) Change it– የማንፈልገውን ነገር ለመለወጥ መጣር- ብዙዎቻችን ስለችግሮቻችን ቀን እና ማታ እናወርለን ነገ ግን ለምፍትሄ የሚሆን ጊዜ የለንም። ለምሳሌ ስራ በማጣቱ የሚማረር ወጣት ቀን እና ማታ ስለስራ አጥነት ቢይወራ ምንም መፍትሄ የለውም። ከሱ የሚጠበቀው ሳይታክት ማመልከቻዎቹን ማሰራጨት ፤ ክህሎቶቹን ማዳበር እና ስራ ሊያገኝባቸው የሚችልባቸውን መንገዶች ማጤን ነው። ስለኑሮዋችን ብናማርር፤ ሌሎችን ብንወቅስ፤ እንዲህ ቢሆን ኖር እያልን በሃዘን ብንብሰከሰክ፤ ሁኔታውን ለመለወጥ ሙከራ እስካላደርግን ድረስ ምንም ጠብ የሚል ነገር የለም።

3) Accept it totally– በልጅነቴ የሰማሁት ጸሎት እስካሁን ድረስም አብሮኝ አለ። ለኔ ትልቅ ትርጉም ስላለው ችግሮች ሲገጥሙኝ ሁሌም አስታውሰዋለው። ጸሎቱ እንዲህ የሚል ነው “በህይወቴ ልለውጣቸው የምችላቸውን ነገሮች እንድለውጥ ብርታቱን ስጠኝ፤ ልለውጣቸው የማልችላቸውን ነገሮች እንድቀበል ጽናቱን ስጠኝ፤ እናም በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንዳስተውል ጠቢብነቱን አድለኝ” ይላል። አዎ ልንለውጣቸው የምንችላቸው ነገሮች ላይ ጉልበት እና ጊዜያችንን በጭንቀት ከማሳለፍ ይልቅ መፍትሄው ላይ ማተኮር ይኖርብናል። በሌላ በኩል ከኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮችን መለወጥ ካልቻልን ተቀብለናቸው መኖርን መልመድ አለብን።

ከላይ የሰፈሩት መፍትሄዎች እንዳሉ ሆነው ችግሮቻችንን ይበልጥ ግልጽ በሆነ እና ቀለል ባለ መልኩ እንድናይ የሚረዳንን አንድ ትልቅ ነጥብ ላክል እሻለው። ይኸውም ችግሮችን የምናይበትን መንገድ በተመለከተ ነው።በብዛት የሚያሳስበን ችግሩ ሳይሆን ችግሩን የምናይበት መንገድ ነው። አይምሮዋችን እንደ እሳት ነው ለበጎ ነገር ከተጠቀምንበት ህልውናችን ፤ለመጥፎ ነገር ከተጠቀምንበት ደግሞ መጥፊያችን ይሆናል። ብዙዎቻችን ይህንን ነገር ሰለማናስትወለው የራሳችንን መንገድ እራሳችን እንዘጋለን።

እውቁ የሳይኮሎጂ ሰው ዶ/ር ኖርማን ቪንሰንት ፒል እንዲህ ይላል “የሚያሳስበን ችግሩ ሳይሆን ችግሩን የምናይበት መንገድ ነው- “how you think about the problem is more important that the problem itself” dr norman vincent peal- ምንኛውም አይነት ችግር ሲገጥመን ከችግሩ በላይ እኛን የሚጎዳን ችግሩን የምንመለከትበት መንገድ ነው። ለማሳሌ አንድን ህጻን ልጅ ከሰፈር ሱቅ አንድ የሆነ እቃ ገዝቶ እንዲመጣ ላክነው። ይህ ህጻን ለእቃው መግዣ የሰጠነውን አስር ብር ጣለው እንበል። ታዲያ ህጻኑን የሚያስለቅሰው እና የሚያሳስበው የአስር ብሩ መጥፋት ወይም እቃው አለመግዛት ሳይሆን በአይምሮ የሚሳለው የወላጆቹ ቁጣ ነው። አይምሮ መጥፎ ነገሮችን ሲያስብ እጅግ አጋኖ ነው፤ በዚህ የህጻን ልጅ ህሊና ውስጥም የሚሳለው የወላጆቹ አስፈሪ ገጽታ፤ ግርፊያው እውን እንደሆነ ሁሉ ህጻኑን ስቅስቅ አስደርጎ ሊያስለቅሰው ይችላል። የኛም ህይወት ከዚህ ብዙ አይርቅም። የሆነ ችግር ሲገጥመን የሚያስጨንቀን እና የሚያስስበን ከችግሩ በላይ ችግሩን የምናይበት መንገድ ነው። ስለዚህ ዋናው መፍትሄ ከችግሩ ጋር ሊመጡም ላይመጡም የሚችሉ መላምቶችን እያሰብን እራሳችንን ገና ለገና ባልሆነው ነገር ከማስጨነቅ ይልቅ ስለ እውነተኛው ችግር በግልጽ ከራሳችን ጋር መፍትሄ መፈልግ ነው።

በመጨረሻ ማስታወስ ያለብን ነገር ብረት ከራሱ ዝገት የበለጠ የሚጎዳው ነገር የለም። እኛም እደዛው ከውስጣችን ዝገት፤ ከአስተሳሰብቻችን ዝገት የበለጠ የሚሰብረን ችግር የለም። ህይወት ቀላል ትሆናልች ብለን እራሳችንን ማዘናጋት የለብንም፤ ይበልጥ ከፍ ለማለት በጣር ቁጥር፤ የህይወት ፈተናም ይከብዳል፤ ችግሮች ይበልጥ ይከሰታሉ። ሁሌም ግን ለችግሮቻችን ትክክለኛውን እይታ ከያዝን የማይታለፍ ፈተና፤ የማይፈታ ችግር አይኖርም።

(በሚስጥረ አደራው)

15 views0 comments